>
5:31 pm - Tuesday November 12, 1805

ለምን ይሆን የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ክሽፈት የገጠመው ? (ደረጀ መላኩ)

ለምን ይሆን የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ክሽፈት የገጠመው ?

ደረጀ መላኩ

Tilahungesses@gmail.com

በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የወረደውን ጥላቻ በተመለከተ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ አኳያግራ መጋባት ይታያል፡፡ ወይም አይተው እንደላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት መስራቾች፣ የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ አካሎች፣ በትግራይ ህዳር 3 2021 ( እ.ኤ.አ.) የተቀሰቀሰውን ጦርነት በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ወገንተኝነት ይታይበታል፡፡ ጦርነቱ ሊጀመር የቻለው የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 3 ቀን 2021 የሰሜን ኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጠበቅ በትግራይ ክልል የሰፈረውን የሰሜን እዝ ላይ ፍርሃት የተቀላቀለበት ጥቃት በማድረሱ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ተጠሪዎች ትክክለኛውን ምክንያት በአደባባይ ለመናገር መንፈሳዊ ወኔ ከድቷቸዋል፡፡

 እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2018 በኢትዮጵያ ምድር በነበረው ህዝባዊ አመጽ ምክንያት የተነሳ በወያኔ ፊትአውራሪነት ይመራ የነበረው ለውጥ ለማምጣት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ያንዬ ኢህአዲግ ዛሬ የብልጽግና ፓርቲ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2018 ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ይህ ምርጫ በሀገሪቱ የፖለቲካ አውድ ላይ የራሱን ለውጥም አምጥቷል፡፡ የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከእስር መለቀቅ፣ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር እርቅ ማወረዷ፣ የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ወዘተ ወዘተ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ከማእከላዊ መንግስቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ሻከረ፣ የፖለቲካ ክፍተቶች መፈጠር ጀመሩ፣የፖለቲካ መቀመጫቸውን ከአዲሰ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ለመቀየር ተገደዱ፡፡ ከማእከላዊ መንግስት ጋር የሚያደርጉት ትብብር እየቀነሰ ቢመጣም፣በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የቀጠሉ ቢሆንም የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት አለም አቀፍ እውቅና ያልተሰጠው ራስገዝ ክልል ለመመስረት ጥድፊያ ላይ የሚገኝ ሆኗል፡፡ ለአብነት ያህል የኮቪዲ ወረርሽ በሽታ በነበረበት አስደንጋጭ ግዜ በክልሉ የምርጫ ውድድር በማከሄዱ የተነሳ የበለጠ ከፌዴራል ማእከላዊ መንግስቱ ጋር መቃቃር እንዲፈጠር ግድ ብሏል፡፡

ባለፉት ለ27 አመታት ኢትዮጵያን በገዛው የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ቆይቶ የነበረው የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለፉት ሶስት አመታት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ በመመሸግ በህግ ወጥ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የጦር እቅድ ሲያወጣ የከረመ ቡድን ነው፡፡ በዚሁ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የጦርነት እሳት በማቀጣጠላቸው የተነሳ የፌዴራል መንግስቱ ህግ ለማስከበር ሲል ወደ ጦርነት መዶሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ የሚል ስያሜ እንዲሰጠው ከመወሰኑ ባሻግር በቅርቡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 28 2021 የፌዴራል ማእከላዊ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ ማቆም ውሳኔ ማድረጉን ተከትሎ የወያኔ አረመኔ ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሲቪልና ሰላማዊ ዜጎች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፡፡ ምንም እንኳን ይሁንና የወያኔ ታጣቂዎች በነቢብም በገቢርም በሲቪል ዜጎች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውም ቢታወቅም፣ የተባበረችው አሜሪካ እና የምእራቡ አለም በርካታ መንግስታት አይተው እንዳላዩ፣ሰምተው አንደ አልሰሙ ሆነው ታይተው ነበር፡፡ እነርሱ ፍጹም በረቀቀ ዘዴ የፌዴራል ማእከላዊ መንግስቱ ላይ የተለያዩ የማእቀብ እርምጃዎችን መውሰድ ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ እነርሱ ፍዳውን ከሚያየው የኢትዮጵያ ህዝብ ይልቅ ተቆርቋሪነታቸው ለአሸባሪው ቡድን ነው፡፡ በእውነቱ የአለም ሁኔታ ያሳዝናል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አጋሮቿን በማሰለፍ በጸጥታው ምክር ቤት በኩል ኢትዮጵያን ለማጥቃት ለበርካታ ጊዜያቶች ብትሞክርም አልተሳካላትም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢኮኖሚ ማእቀብ ጥላባታለች፡፡ ለአብነት ያህል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደሃ እናቶችንና ልጃገረዶችን ተጠቃሚ አድርጎ ከነበረው አጉዋ የንግድ ትስስር ኢትዮጵያን አግዳታለች፡፡ excluding Ethiopia from the African Growth and Opportunity Act, AGOA pact, which was mainly helpful to the thousands of Ethiopian poor women and girls. 

በቅርቡ የምእራቡ አለም ከኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆነ እርምጃ ወስዷል፡፡ ይህም በሌላ መንገድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል በኩል ኢትዮጵያን ለመጉዳት የጥቃት ሰበዙን መዟል፡፡ ኢትዮጵያና አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከቅርብ ግዜ ወዲህ የፖለቲካ አላማ ማራመጃ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ይህም ብቻ በተባበረችው አሜሪካ አስተባባሪነት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለማስፈን የብይነ መንግስታቱ ድርጅት እንደ መሳሪያ እየሆነ ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተጀመረው ‹‹በቃ›› የተሰኘው እንቅስንቃሴ በመላው አለም ተቀባይነት እያገኘ የመጣው፡፡ ይህ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ምእራባውያንም ሆኑ ሌሎች ሀገሮች ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው የሚያሳስብ ከመሆኑ ባሻግር 1.3 ቢሊዮን ህዝብ ያላት አፍሪካ በብይነ መንግስታቱ ድርጅት በቂ የሆነ ተወካይ እንዲኖራትም የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር የተቋቋመው ይህ አለም አቀፍ ተቋም በየግዜው ፈተናውን ሲወድቅ ይስተዋላል፡፡ ለምን ? ህሊና የፈጠረባችሁ በየአካባቢችሁ ተወያዩበት::

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብት ካውንስል ልዩ ሴሽን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 17 2021 በአደረገው ስብሰባ በወሰነው መሰረት በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ያሉትን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጣራት በሚል አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ኤክስፐርት አቋቁሟል፡፡ የብይነ መንግስታቱ ውሳኔ በ21 ሀገሮች ድጋፍ አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በ15 ሀገሮች ተቃውሞና 11 ሀገራት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ በውሳኔው መሰረት አዲሱ የሰብአዊ መብት ካውንስል ሶስት የሰብአዊ መብት ኤክስፐርት አባላት አሉት፡፡ እነኚህ ኤክስፐርቶች  በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በሁለቱም ወገኖች ተፈጸሙ የሚሏቸውን የሰብአዊ መብት  ጥሰቶችን ለማጣራት፣የሰብአዊ እርዳታና ስደተኞችን በተመለከተ ለማጣራት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በጄኔቫ የብይነ መንግስታቱ ማህበር የሰብአዊ መብት ካውንስል ያሳለፈውን ውሳኔ  አለመቀበሏ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንኑ ውሳኔ ያልተቀበለችው እንደው ዝም ብላ አለነበረም፡፡ ምክንያት ነበራት፡፡  የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል የትግራይ አሸባሪ ቡድን የፈጸመውን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል፣የንብረት ዘረፋ፣የጦር ወንጀል በተመለከተ፣እንዲሁም ህጻናትን በጦር ሜዳ አሰልፎ በእሳት ውስጥ ሲማግድ ወዘተ ወዘተ ምንም አይነት ተቃውሞ ባለማሰማቱ  ኢትዮጵያ ውሳኔውን ያልተቀበለችው፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ፍላጎቷ ለተወሰነው ውሳኔ ተባባሪ እንደማትሆንም አሳስባለች፡፡ ደግሞ ኢትዮጵያ አንዲት ሉአላዊት ሀገር መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሌሎች የባእድ ሀገራትን ፍላጎት ለማሟላት የተሰጠው ውሳኔ ፍትሃዊ አልነበረም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ በእውነትና ሞራል ላይ ቆሞ የተፈጸመውን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጣራት ቢሞከር የአባት ነበር፡፡ ሮይተርስ በመባል የሚታወቀው አለም አቀፍ የዜና አውታር የኢትዮጵያን ውሳኔ እንደዘገበው ከሆነ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ስም በራሷ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩትን ሀገራት እንዲሁም አንድን ወገን ብቻ ለማጥቃት የታለመውን ውሳኔ አልቀበልም ብላ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል ልዩ ሴሽን የወሰነውን ውሳኔ ላለመቀበል የተገደደችበት አንዱና ዋነኛው መሰረታዊ ምክንያት የነበረው ግን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከግንቦት 16 እስከ ነሃሴ 30 2021 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን (the Office of the United Nations High Commissioner for Human Rights (OHCHR) ) በጋራ በመሆን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ምርመራ በማድረጋቸው ነበር፡፡ ይህ በ150 ገጾች የተቀነበበው ጥልቅ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ እንዲሆን የተደረገው ህዳር 3 2021 (እ.ኤ.አ.) ነበር፡፡ ሪፖርቱ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሸፈነ ከመሆኑ ባሻግር ህጋዊ ማስረጃዎችንም አቅርቧል፡፡ ተጠያቂ ያደረጋቸው አካላትም የመንግስት ሃይሎች፣የኤርትራ ወታሮች እና የትግራይ ልዩ ሀይል አባላትን ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ተጨማሪ የምርመራ ስራዎች መካሄድ እንዳለባው ምክረ ሃሳቡን አቅርቦ ነበር፡፡

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኘው የወያኔ አሸባሪ ቡድን በወረራ ከያዛቸው አፋርና አማራ ክልል በርካታ አከባቢዎች ተሸንፎ ከሸሸ በኋላ  የጄኔቫውን ውሳኔ እንደሚቀበል፣ለብይነ መንግስታቱ ድርጅት  የሰብአዊ መብት ካውንስል የመስክ ምርመራ ስራ ተባባሪ እንደሚሆን በአፈቀላጤው በኩል አስታውቆ ነበር፡፡ ይህ ወንጀለኛ ቡድን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያወጡትን የሰብአዊ መብት ጥሰት የምርመራ ውጤት እንደማይቀበል ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል ልዩ ሴሽን በርካታ ሃሳቦችን ለአደባባይ ውይይት ያቀርባል፡፡ ለአብነት ያህል የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ፈቃድ እንዳለው፣ ውጤታማ ምርመራ ማድረግ እንደሚችል፣ገለልተኛ አንደሆነ እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ምክንያታዊ የሆነ ግምገማ ለማድረግ ውይይት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል አመሰራረትና የስራ ደንቦች

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል ዋነኛው የብይነ መንግስታቱ ድርጅት አካል ሲሆን የሚያጠናውም የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎችን ነው፡፡ የተመሰረተው ደግሞ በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ 60/251 የነበረ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር በ2006 ላይ ደግሞ የብይነ መንግስታቱን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለመተካት ችሏል፡፡ 47ቱ አባላቱ የሚመረጡት በጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን የስራ ጊዜያቸው ደግሞ ሶስት አመት ነው፡፡  ይህ ድርጅት በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአለም ላይ የሰብአዊ መብት እንዲጠበቅና የስብአዊ መብት ቅቡልነት እንዲኖረው ወይም የማስፋፋት ስልጣን አለው፡፡ በዚህ የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መቀመጫዎች የሚመደቡት( ኮሚሽኑ የተደራጀው) ለክፍለ አህጉራዊ ቡድኖች ነው፡፡ (አፍሪካ፣ኤሽያ፣ላቲን አሜሪካ፣ካሪቢያን፣ምስራቅ አውሮፓ፣ምእራብ አውሮፓ )

The allocation of seats is organized along regional groups – Africa, Asia, Latin America and the Caribbean (GRULAC), East Europe and the Western Europe and Others Group (WEOG

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካውንስሉ መደበኛ ሴሽን እና ልዩ ሴሽን በማዘጋጀት ህጋዊ ስራ ሲያከናውን ነበር የቆየው፡፡ የመደበኛ ሴሽን በአመት ለሶስት ግዜያት ያህል የሚካሄድ ሲሆን( መጋቢት፣ሰኔ እና መስከረም ወራት)፣ አጀንዳዎቹም ከአባል ሀገራት የሚቀርቡ እና የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት የጠቀበላቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡

የብይነ መንግሰታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል የሚያቀርባቸው፡-

  • አመታዊ የሰብአዊ መብት ሪፖርት
  • የሰብአዊ መብት ካውንስሉ አባል ሀገራት ጋር ልዩ ውይይት ማድረግ 
  • በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄድ
  • አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች በተመለከተ፣በተለይም የየሀጋራቱን የስብአዊ መብት ሁኔታ በተመለከተ የየሀገራቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብአዊ መብት ተከላካይ ድርጅቶችን ማዳመጥ፣መወያየት
  • አስቸኳይ ሰብአዊ መብት ሁኔታን መመርመር

የሰብአዊ መብቱ ካውንስል ስልጣንና ተግባራት

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል ስልጣኑ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና ነጻነቶችን ፕሮሞት ማድረግ፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመርና ሪፖርት ማውጣት፣ምክረ ሃሳብ የመስጠት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር በሀገራት መሃከል አለም አቀፍ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ለቀረቡ ጥያቄዎች ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰብአዊ መብት አኳያ አለም አቀፍ እውቅና   ያላቸው እና በሰብአዊ መብት ትምህርት ዘርፍ የላቀ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ከባድና አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸውን ሀገራት የሰብአዊ መብት ሁኔታ በተመለከተ ምሁራዊ እና ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲያቀርቡ አለም አቀፍ የውይይት መድረክ ያዘገጃል፡፡ እነኚሁ ባለሙያዎች በግለሰብ ደረጃ ያሉ ኤክስፐርት፣ወይም በቡድን የታቀፉ ኤክስፐርቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ይሄው የሰብአዊ መብት ካውንስል የብይነ መንግስታቱን አባል ሀገራት አመታዊ የሰብአዊ መብት ሪኮርድ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይመረምራል፡፡

The Council also manages the Universal Periodic Review, a process through which each UN Member State’s overall human rights record is reviewed.

ከዚህ በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ የሚቀረቡ አቤቱታዎችን ይቀበላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎች ጥልቅ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስለመሆናቸውና ተጨባጭ ማስረጃ ስለመቅረቡ በብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች አለም አቀፍ ድንጋጌዎች ኤክስፐርቶች መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

የብይነ መንግሰታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል የ15 አመት የስራ ልምድ

አብዛኞቹ የሰብአዊ መብት አዋቂዎችና ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በ15 አመቱ የስራ ሂደቱ አንዳንድ ውጤቶችን ማስመዝገቡ እሙን ነው፡፡ ለአብነት ያህል በየአመቱ የየሀገራቱን የሰብአዊ መብት ሪኮርድ የሚፈትሸው ክለሳ የተሳካ ነበር፡፡

The Universal Periodic Review (UPR) has functioned well as a review mechanism

ዩኒቨርሳል ፔሬዲክ ርቪው ምን ማለት ነው ?

ይህም ማለት የብይነ መንግስታቱ አባል ሀገራት ሁሉ አመታዊ የሰብአዊ መብት ሪኮርዳቸው ምን እንደሚመስል ክለሳ የሚደረግበት ወይም የሚፈትሽበት ሂደት ወይም ክርክር ነው፡፡ ( ለአብነት ያህል የአንድን ሀገር አመታዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በተመለከተ የሀገሩ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌላ መንግስታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብት ተከላካይ ድርጅት የራሳቸውን አመታዊ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያን አመታዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሪኮርድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በየአመቱ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ዩኒቨርሳል ፔሬዲክ ሪቪው የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2008 ላይ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል በቅርብ ግዜ በተፈጠረለት እድል በተሰጠው ስልጣን  የግል ደህንነት መብትና  በሴቶች ላይ ምንም አይነት አድሎ እንዳይፈጸምባቸው ይከራከራል፡፡ በሌላ አነጋገር የግል ደህንነትን እና የሴቶችን መብት የማያከብሩ ሀገራት ካሉ ተከታትሎ የምርመራ ሪፖርት በማውጣት መብቶቹ ዳግም እንዳይጣሱ ምክረ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡ ይህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ካውንስል እንደ ኮትዲቯር፣ስሪላንከና ሰሜን ኮሪያ የመሳሳሉት ሀገራት የሰብአዊ መብት ጥሰት በየግዜው እንደሚፈጽሙ ሪፖርት አውጥቶ ነበር፡፡ 

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል በብዙ መልኩ የሚተች ድርጅት ነው፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ የአለም ክፍሎች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፈጻሚዎችን አይቶ እንዳላያ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ በመታየቱ ነው፡፡ አንዳንዶቹን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርካታ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁኔታዎች ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ በቀላሉ ሊከሉ የሚችሉ ድንገተኛ የሰብአዊ ቀውሶች ትኩረት አልተሰጣቸውም ፡፡ በየሀገሩ የሰብአዊ ጥሰት መብት ፈጻሚዎች እና አስፈጻሚዎች ተጠያቂ መሆን አልቻሉም፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ምድር አስከፊ የሰብአዊ መብት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ጨካኞች ገና ሙሉ በሙሉ በፍትህ አደባባይ እንዲቀርቡ አልተደረገም፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ የወያኔ አሸባሪ  ቡድን አባላትና ገዢዎቻቸው፣ ኦነግ ሸኔ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ቡድን አባላትና ገዢዎቻቸው በፍትህ አደባባይ እንዲቆሙ የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል ምንም አይነት ጥረት ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ ካውንስሉ ሰምቶ እንዳልሰማ፣አይቶ እንዳላየ ሆኗል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብአዊ መብቶች ካውንስሉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ያቀረቡትን በርካታ ምክረ ሃሳብና ውሳኔዎች ገቢራዊ ማድረግ አልተቻለውም ወይም የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ገቢራዊ አልሆኑም፡፡  የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በራሱ አደጋ ላይ እየወደቀ ይገኛል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መግለጫዎችና ሪፖርቶች፣በርካታ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጉባኤዎች መካሄዳቸው፣የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል ቄጥራቸው በዛ ያሉ ኤክስፐርቶች ስላሉት ብቻውን የሰብአዊ መብትን ከማስከበር አኳያ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡

ብዙ ግዜ እንደሚነገረው የሰብአዊ መብት ካውንስሉ ጠንካራ ውሳኔ ማሳለፍ እና ውጤታማ መሆን የሚቻለው የብይነ መንግስታቱ አባል ሀገራት ነጻነቱ እንዳይገፈፍ መወሰን ሲቻላቸው ይመስለኛል፡፡ ካውንስሉ በተሰጠው ሃላፊነት በመርህና ህግ መመራት ካልቻለ ሀያላን ሀገራት በቀላሉ ሊጠቀሙበት ከመቻላቸው ባሻግር የአንዳንድ ሀገራት የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚች ነጥብ ላይ የተባበረችው አሜሪካን ልምድ ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ በተለይም ፕሬዜዴንት ባራክ ኦባማ ስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ይህ የሰብአዊ መብት ካውንስል እንዳይመሰረት ፍላጎቷ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የተባበረችው አሜሪካ ለብይነ መንግስታቱ የምታደርገውን ከፍተኛ የገንዘብ ልገሳ ጋሻና መከታ በማድረግ በሰብአዊ መብቱ ካንስል ላይ ተጽእኖ መፈጠሯ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡( የተባበረችው አሜሪካ የሰብአዊ መብቱ ካውንስል አባል ሀገር እንዳልተመረጠች ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡) 

የተባበረችው አሜሪካ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለራሷ ፖለቲካ መጠቀሟ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበረችው አሜሪካ በሌሎች ሀገራት የሰብአዊ መብትን ከማስጠበቅ አኳያ ተከታታይ አቋም ስትይዝ አይስተዋልም፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ለ27 አመታት ያህል የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ የተባበረችው አሜሪካ ዝምታን መርጣ ነበር፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ደግሞ የማእከላዊ መንግስቱ ፈጸመ የምትለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተለያዩ ግዜያት ያወገዘች ሲሆን ፣ የወያኔ አሸባሪ ቡድን አባላትና ኦነግ ሸኔ በመባል የሚታወቁት ታጣቂዎች የሚፈጽሙትን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማውገዝ መንፈሳዊ ወኔ ከድቷት ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አልሰማሁም፣ አላየሁም ማለቱን ቀጥላበታለች፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በተባበረችው አሜሪካ ተጽእኖ ስር መውደቁ እሙን ነው፡፡ የተባበረችወን አሜሪካ ፖሊሲ ለማስፈጸምም እንደ ጥሩ መድረክ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ያለማቋረጥ፣ያለመሰልቸት የተለያዩ ትብብሮችን በማድረግ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ ስራ ላይ ተግዳሮት ትፈጥራለች፡፡ የርሷን ፖሊሲ የሚደግፉ ሀገራትንም በሰብአዊ መብት ካውንስሉ ውስጥ አባል እንዲሆኑ ለማድረግ እጇ ረዥም ነው፡፡

ካውንስሉ በኢትዮጵያ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ስህተቱ ምን ነበር ?

የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ልዩ ሰብሰባ የጠራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና (EHRC )በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (OHCHR) ጋር አንድ ላይ በመጣመር በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያደረጉትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ሙሉ እውቀትና እውቅና በመስጠት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ( እንደ ግንቦት 16 እስከ ነሃሴ 30 2021 እ.ኤ.አ. የተካሄደውን ማለቴ ነው) ሁሉም አክተሮች የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰት መርምረው ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡ በግዜው የኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን ሪፖርት እንደሚቀበለው አስታውቆ ነበር፡፡ የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል ቀደም ብሎ የወጣውን ሪፖርት በተመለከተ ጥርጣሬ የለውም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፎ ነበር፡፡ ስለሆነም ሌላው የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ወኪል የሰብአዊ መብት ካውንስል ማለቴ ነው በድጋሚ በትግራይ ክልል ብቻ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲደረግ መወሰኑ ፍትሃዊ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በህሊና ሚዛን ላይ ተቀምጠው ለማጣራት ቢወስኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከበሬታን ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

የኢትዮጵያን አቋም ያዳመጠውና ከአሁን ቀደም የተደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ የተቀበለው የሰብአዊ መብት ካውንስሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችንና ወንጀለኞችን ለማወቅ መረጃ ለመስብሰብ ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡፤ ሆኖም ግን ይሁንና  ይህ ውሳኔ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ቀደም ብሎ የተካሄደውን የምርመራ ስራ ውድቅ ለማድረግ ማሰቡን ነው፡፡ ሌላ በድጋሚ በአንድ አካባቢ ብቻ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ለማድረግ መወሰን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳያ ነው፡፡ እነርሱ የሰብአዊ መብትን በገቢርም በነቢብም በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን የፈለጉ አይመስልም፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ መንግስትን ለማስጨነቅ ያሰቡ ይመስላል፡፡ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ የተባበረችው አሜሪካ ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሟላት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ ይህ በጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ግዜ እንደነበረው ጫና፣ እንዲሁም የተባበረችው አሜሪካ የኢኮኖሚ ማእቀብ ባሻግር ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ የፖለቲካ ጫና እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

በሌላ የሳንቲሙ ገጽ ባለው የሰብአዊ መብት ዲሰኮርስ( discourse) ማለቴ ነው፡፡ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች የመብት አስከባሪዎች ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በኢትዮጵያ ምድር የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን መርምሮ ለማጣራት ብቃት አላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም በመጀመሪያ ነጻነቱ ሊሰጣቸው ግድ ይላል፡፡ በአለም አቀፍ ባህላዊ ህግ መሰረት የሀገራት ሉአላዊነት መከበር አለበት፡፡ በአንድ ሀገር ላይ የተፈጸሙ የሰብአሰዊ መብት ጥሰቶች ጥልቅና ከባድ ከሆኑ በዛች ሀገር ጋባዥነት አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅት ወይም የተባበሩት መንገስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል ገብቶ በገለልተኝነት መንፈስ ማጣራት እንደሚችል ይወስናል፡፡ ስለሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ከኢትዮጵያ መንግስት እገዛ ሳይጠይቅ በራሱ መወሰኑ አግባብ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ትኩረቱን በአንድ ክልል ላይ ሳያደርግ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሥለተከሰቱት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ትኩረት ቢያደርግ ኖሮ ከውጭ ተመልካቾች አኳያ ድጋፍ ሊያስገኝለት ይቻለው ነበር፡፡

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል ኢትዮጵያ ከሰብአዊ መብት አኳያ ያላትን ህጋዊ መብት ጥሷል ወይም ያሳለፈው ውሳኔ በስህተት የታጀለ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይተቀሳሉ፡፡

  • ከኢትዮጵያ መንግስት የእገዛ ጥያቄ አልቀረበለትም ነበር፡፡ ( የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመመርመር ማለቴ ነው፡፡) መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል እንዲላክለት እገዛ አልጠየቀም ነበር፡፡ ግጭቱ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የተካሄደ በመሆኑ ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት አግዙኝ ሳይል ካውንስሉ በራሱመንገድ፣ለራሱ ፍላጎት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመግባት መወሰኑ ህጋዊ አልነበረም፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ለማድረግ ከመወሰን ባሻግር ከትግራይ ክልል ውጭ ስለተፈጸሙ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ማንነት ትንፍሽ ያላለው ካውንስሉ በትግራይ ብቻ በድጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ለማድረግ መወሰኑ ፍትሃ አይመስለኝም፡፡
  • ኢትዮጵያ የራሷን እድል በራሷ የመወሰን መብት ለመወሰን ያላት ሉአላዊት ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስል የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጥስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
  • ምንም እንኳን በተባበሩት መንግስታት የብሔራዊ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ቀደም ባሉት ወራቶች በጋራ ምርመራ ማካሄዳቸው  የታወቀ ቢሆንም ፣ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በድጋሚ ምርመራ ለማካሄድ መወሰኑ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት እንዳሳሳቱት ማሳያ ነው፡፡

ልክ እንደ የጸጥታው ምክር ቤት ሁሉ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት ላይ ገለልተኛ አቋም መያዝ አልተቻለውም፡፡ የጸጥታው ምክር ቤት የወያኔ አሸባሪ ቡድን በጦር ሜዳ የሽንፈት ጽዋ በሚጎነጭበት ግዜ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ውይይት ያደርግ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የወያኔ አሸባሪ ቡድን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በርካታ የገጠር ቀበሌዎችንና ከተሞችን ተቆጣጥሮ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም አንድም ቀን የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጠርቶ አያውቅም፡፡ በእውነቱ የኢትዮጵያ እድሏ ያሳዝናል፡፡ ለማናቸውም ይህ እውነት በሌሎች የብይነ መንግስታቱ ልዩ ወኪሎች በሆኑት እንደ ዩኔስኮ በመሳሰሉት ድርጅቶች ታይቷል፡፡ ዩኔስኮ ( UNESCO ) በአለም ቅርስነት የተመዘገበችው ላሊበላ ከተማ በአሸባሪው ወያኔ ቁጥጥር ስር በወደቀችበት ግዜ ድምጹን ማሰማት አልፈለገም ነበር፡፡ የአለም የጤና ድርጅትም የሆስፒታል መሳሪያዎች፣መድሃኒቶች ሲዘተረፉ፣ሲወድሙ ዝምታን በመምረጡ ተመሳሳይ ስህተት ፈጽሟል፡፡ ስለሆነም የብይነ መንግስታቱ የሰብአዊ መብት ካውንስልን የተለየ የሚያደርገው አይመስለኝም፡፡ የሰብአዊ መብት ካውንስሉ የሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ፣ የሠብአዊ መብቶች ትምህርትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ማድረግ ሲገባው ከፍተኛ ገንዘብ ለሚመድቡለት የምእራቡ አለም በተለይም ለተባበረችው አሜሪካ አለማ ማስፈጸሚያ መዋሉ ዛሬ ባይሆን ነገ የሚያስጠይቅ ነው፡፡

Filed in: Amharic