የባልደራስ አመራሮች ከፈረንሳይና ጀርመን አምባሳደሮች ጋር ስለወለጋው የአማራ ፍጅት ተወያዩ….!!!
በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሽ (Remi Mrechaux) እና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሴፋን አውር (Stephan Auer) ከባልደራስ ፕሬዘደንት እስክንድር ነጋ እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ሰለሞን ተሰማ ጋር የአንድ ሰዓት ተኩል ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የባልደራስ አመራሮች በአራት ርዕስ ከፋፍለው በሰጡት ማብራሪያ፣
1ኛ/ የባልደራስ አመራሮች እስር፣ በምርጫ 2013 ዓ.ም የገዢውን ፓርቲ አሸናፊነት ለማረጋገጥ የተፈፀመ መሆኑን፣
2ኛ/ የህወሓት ትግል መንግሥት ለመለወጥ ሳይሆን ሀገር ለማፍረስ መሆኑን፣ ከህወሓት ጋር ግንባር የፈጠረው ኦነግ/ሸኔ የዘር ማጥፋት (Ethnic cleansing/ Genocide) እየፈፀመ መሆኑን እና የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ባለሥልጣናት ከሸኔ ጋር እየተባበሩ መሆኑን፣
3ኛ/ አገራዊ የምክክር መድረኩ ከወዲሁ የመክሸፍ ምልክት እየታየበት መሆኑን፣ ይህም ለመሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን እየደረደረ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የባልደራስ አመራሮች፣ ከኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ፈረንሳይና ጀርመንን ጨምሮ፣ ይጠበቃል ያሉትን አራት ነጥቦችን አስቀምጠዋል፡-
1. የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድር መቅረብ የለበትም ብለው አቋም እንዲወስዱና ይህንንም ለህወሓት እንዲያሳውቁ፣
2. ህወሓት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትጥቅ መፍታት አለበት ብለው አቋም እንዲወስዱ
3. ኦነግ/ሸኔን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ
4. ገዢው ፓርቲ በብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ያስቀደመው ቅድመ ሁኔታን (ስለ ህገ መንግሥቱ አልደራደርም ያለውን) እንዲያነሳ ምክር ሊሰጡት ይገባል ብለዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በበኩላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው ከፓርቲው አመራሮች ምላሽ ተሰቷቸዋል፡፡