>

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከ70 ቀናት  የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ዛሬም ቀነ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀበት....!!! (ተራራ ሚድያ)

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከ70 ቀናት  የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ዛሬም ቀነ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀበት….!!!
ተራራ ሚድያ

*…. ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ  በዛሬዉ ዕለት  ፍርድ ቤት ቀርቦ  ለየካቲት 17 ቀን  ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠዉ በአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ  ስር እንዲታሰር አድርጎት የነበረዉ የኦሮሚያ ፖሊስ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ተነስቶ   ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ   ከእስር ይፈታል በሚል  ቢጠበቅም ፖሊስ በድጋሜ  ምርመራ መጀመሩን ቤተሰቦቹ አስታዉቀዋል፡፡
 ላለፉት 70 ቀናት በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በእስር ላይ የነበረው የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት  በዛሬዉ ዕለት ፍርድ ቤት እንደቀረበና ፖሊስ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይስጠኝ ሲል የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ  የ 7ቀን የጊዜ ቀጠሮ   ፈቅዶለታል፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ  በኦሮሚያ ልዩ ዞን የገላን ከተማ ወረዳ  ፍርድ ቤት  ባለፈዉ  ታህሳስ 21/2014 ዓ.ም   የቀረበ ቢሆንም  ፖሊስ “ምርመራዬን አጠናቅቂያለሁ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ አያስፈልገኝም የምርመራ መዝገቡም ይዘጋ ሲል ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ  የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የምርመራ መዝገቡን ዘግቶ ጉዳዩም ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተላለፍ መወሰኑ የሚታወስ ነው።
የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ባለፈዉ ማክሰኞ ማንሳቱ የሚታወስ ሲሆን  ይሁን እንጅ    ፖሊስ ጉዳዩን ዳግም ወደ መደበኛዉ  የምርመራ መዝገብ እንደወሰደዉ ታዉቋል፡፡
የአቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በ48 ሰዓታት ዉስጥ ከእስር የማይለቀቅ ከሆነ ወደ ፍርድ መቅርብ እንዳለበት ህጉ የሚደነግግ በመሆኑ  በዛሬዉ እለት ከጠዋቱ  5 ሰዓት ገደማ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን ከተማ ወረዳ  ፍርድ ቤት  ቀርቦ ፖሊስ  ለተጨማሪ ምርመራ    7 ቀን  የተፈቀደለት ሲሆን ጋዜጠኛ ታምራት የዋስትና መብቴ ይጠበቅልኝ ሲል ቢጠይቅም   በቀጣይ ቀጠሮ  መጠየቅ ትችላለህ የሚል መልስ እንደተሰጠዉም ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡
በዛሬዉ ችሎት ላይ የታምራት ነገራ ጠበቃ ሳይገኝ ችሎቱ እንደተከናወነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመሆኑም ጋዜጠኛ  ታምራት ነገራ  ለየካቲት 17 /2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ  ተሰቶታል፡፡
የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከአዲስአበባ ፖሊስ ተላልፎ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ፖሊስ መምሪያ  እንደታሰረ ይታወሳል፡፡
ጋዜጠኛው ከቤቱ እንደተወሰደ የመጀመሪያዎቹ 7 ቀናት የት እንዳለ ሳይታወቅ ቆይቶ ከ7ቀን በኋላ  ፍርድ ቤት መቅረቡ አይዘነጋም ።
 ታህሳስ 01/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:30 ገደማ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ  ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ ነበር የተወሰደዉ
Filed in: Amharic