>

የባልደራስ አመራሮች ከስዊድን አምባሳደር ጋር በነበራቸው ውይይት የጦርነቱ ምንጭ ህገ-መንግሥቱ መሆኑን ገለጹ...!!! (ጌጥዬ ያለው)

የባልደራስ አመራሮች ከስዊድን አምባሳደር ጋር በነበራቸው ውይይት የጦርነቱ ምንጭ ህገ-መንግሥቱ መሆኑን ገለጹ…!!!

ጌጥዬ ያለው


በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄነሪክ ሉንድኩስት (Hans Henric Lundquist)  ከባልደራስ ፕሬዘደንት እስክንድር ነጋ እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ሰለሞን ተሰማ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት አደረጉ፡፡

በውይይቱ ወቅት የባልደራስ አመራሮች በሰጡት ማብራሪያ፣ ገዢው ፓርቲ ምርጫ 2013ን በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዳላሸነፈ አጽንኦት ሰጥተው ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ካለቀ በኋላ ጉዳዩ እንደ አዲስ መነሳቱ እንደማይቀርም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እንደሚታወቀው፣ የገዢው ፓርቲ አገሪቱ ውስጥ ባሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁሉ ከ98 ከመቶ በላይ መቀመጫ ይዟል፡፡ “ውጤቱ በራሱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳልተደረገ ያሳያል፡፡ በዚህ ደረጃ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ ማሸነፍ የሚችል ፓርቲ ካለማ፣ ብሔራዊ መግባባት እንዳለ ስለሚያመላክት፣ ብሔራዊ ምክክሩ ለምን አስፈለገ?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ምርጫው ፍትሃዊ ያልነበረ ቢሆንም፣ ቅድሚያ የሚሰጠው አገራዊ ጉዳይ ግን የሰሜኑ ጦርነት እና በኦሮሚያ እየተፈፀመ ያለው ጭፍጨፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አግባብ፣ የስዊድን መንግሥት ህወሓት አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተረድቶ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ግልጽ ድጋፉን እንዲያሰማ ጠይቀዋል፡፡ እንዲሁም፣ በኦሮሚያ ክልል በሸኔ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር በቅንጅት እየተፈፀመ የሚገኘው የአማራ ፍጅት፣ የጄኖሳይድ አደጋ የጋረጠ በመሆኑ፣ ኦነግ/ሸኔና ተባባሪዎቹ በስዊድን መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ ቦኮሃራም በሽብርተኛነት እንዲፈረጅ ጠይቀዋል፡፡ እንዲሁም፣ በቅርቡ ከወለጋ እና ከምዕራብ ሸዋ ለተፈናቀሉት እርዳታ እንዲደርሳቸው ተማጽነዋል፡፡

የአገራዊ ምክክሩን በሚመለከት፣ ሂደቱ ጥሩ እንዳልሆነ ምልክቶች  እየታዩ መሆኑን፣ በቅርቡ ገዢው ፓርቲ፣ “ህገ መንግሥቱ ለድርድር አይቀርብም” ያለው ምክክሩን ትርጉም እያሳጣው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “በአገራችን ያለው ጦርነት ምንጭ ህገ መንግሥቱ ነው፡፡ ስለ ጦርነቱ ምንጭ ካልተነጋገርን ስለምን ልንነጋገር ነው?” ብለዋል፡፡

Filed in: Amharic