>

ዐብይ አሕመድን ይጸየፉታል እንጅ አይጠሉትም (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አሕመድን ይጸየፉታል እንጅ አይጠሉትም

መስፍን አረጋ


ዋና የሕልውና አደጋ የተጋረጠበት የአማራ ሕዝብ፣ ዋና ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በዋናው የሕልውናው ጠላቱ ላይ ነው፡፡  ዋናው የሕልውና ጠላቱ ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆን ዐብይ አሕመድ ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ ደግሞ ዋናውን የሕልውና ጠላቱን ዐብይ አሕመድን ከጫንቃው ላይ ካወረደ፣ ዐብይ አሕመድ ያዘላቸው ኦነግና ወያኔ ከዐብይ አሕመድ ጋር አብረው ስለሚፈጠፈጡ፣ ባንድ ዲንጋ ሦስት ወፍ ይመታል፡፡  

ቅራቅር ላይ አከርካሪው ተሰብሮ የነበረው ወያኔ፣ በብርሃን ፍጥነት አንሰራርቶ የአማራን ምድር ባድማ ለማድረግ የቻለው በዐብይ አሕመድ ወሳኝ እገዛ ነው፡፡  ከሃምሳ ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የእድሜ ዘመኑ ድል ማድረግ ይቅርና አንድም ጊዜ በቅጡ ተዋግቶ የማያውቀው ኦነግ፣ ወለጋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ፣ ሰሜን ሸዋን አጋይቶ፣ አዲሳባ ገባሁ አልገባሁ እያለ ለማስፈራራት የበቃው፣ ዐብይ አሕመድ ስልጣን ከያዘ በኋላ ትጥቁን ፣ ስንቁን ስላሟላለት ነው፡፡  ራሱ ዐብይ አሕመድም እኔን ብትነኩ ባንድ ጀምበር መቶ ሺወቻችሁ ትታረዳላቸሁ በማለት ትንሽም ሳይሰቀጥጠው በትዕቢት መንፈስ ለመዛት የበቃው፣ አደራጅቶና አስታጥቆ በተጠንቀቅ ባስቀመጠው አራጅ ሠራዊቱ ሙሉ በሙሉ ስለተማመነ ነው፡፡    

የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላት ወያኔና ኦነግ ሳይሆኑ ዐብይ አሕመድ በመሆኑ፣ የአማራ ሕዝብ በዋናነት ማትኮር ያለበት በዋና ጠላቱ በዐብይ አሕመድ ላይ መሆኑን የሚገልጹ ጦማሮችን ደጋግሜ በመጦመሬ ምክኒያት፣ ዐብይ አሕመድን ትጠላዋለህ የሚሉ ከሳሾች፣ ወይም ደግሞ የዐብይ አሕመድ ጥላቻ ሊገልህ ነው የሚሉ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች አጋጥመውኛል፡፡  እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በዐብይ አሕመድ አፍዝ አደንግዝ የደነዘዙ የዋሆች፣ ይልቁንም ደግሞ ዐብይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርፎ፣ የበላውን በልቶ ሲጠግብ በሚወረውርላቸው ፍርፋሪ የተገዙ የሌባ ተካፋይ ልክስክሶች ናቸው፡፡

ዐብይ አሕመድን ግን ይጸየፉታል እንጅ አይጠሉትም፡፡  መጥላትና መጸየፍ እየቅል ናቸው፡፡  አሸባሪን ይጠሉታል፣ አጭበርባሪን ይጸየፉታል፡፡ ትዕቢተኛን ይጠሉታል፣ ጉረኛን ይጸየፉታል፡፡  የምትጠላው በጥቂቱም ቢሆን የምታከብረውን ነው፡፡  

ዐብይ አሕመድ ደግሞ የሚከበርበት ምንም ጎን የሌለው፣ ክሂሎቱ ዐይኑን በጨው አጥቦ ምንም ሳያፍር መዋሸትና ማጭበርበር ብቻ የሆነ፣ ቀትረ ቀላል ወራዳ ነው፡፡  አወ፣ ዐብይ አሕመድ አጸያፊ ሰው ነው፡፡  በዚያ ላይ ደግሞ እጅግ ሲበዛ ፈሪ በመሆኑ ምክኒያት ጭካኔው ወደር የሌለው አረመኔ ነው፡፡  ምንም አያመጡም ብሎ የሚያስባቸው ሰወች እንደ ከብት ቢታረዱ፣ ሕጻናት በእሳት ቢንጨረጨሩ፣ ማሕጸናት ቢዘረከቱ ለይስሙላ እንኳን አዝኛለሁ የማይል የሰይጣን ቁራጭ ዳቢሎስ (devil) ነው፡፡  ይጎዱኛል ብሎ የሚያስባቸው ሰወች ደግሞ ትንሽ ፊታቸውን ካዞሩበት እግራቸው ሥር ወድቆ ለመለማመጥ ወፍ የማይቀድመው አሸርጋጅ ነው፡፡  ቆፍጠን ሲሉበት እየተጥመለመለ፣ ዘና ሲሉለት የሚናደፍ አሲል እባብ ነው፡፡  በደካማ ጎን ተጥመልምሎ የሚገባ ሸለመጥማጥ፣ ያመኑትን በደንደሳቸው የሚጥል ጮሌ ፈረስ ነው፡፡

የዐብይ አሕመድን የባሕሪ አስጸያፊነት ከመለስ ዜናዊ የባሕሪ አስጠሊነት ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡

መለስ ዜናዊ በአማራ ምድር ላይ አልፎ ዐራት ኪሎን ለመቆጣጠር የቻለው የአማራ ሕዝብ ስለፈቀደለት ብቻና ብቻ ቢሆንም፣ ትግራይን ለመቆጣጠር የቻለው ግን ባብዛኛው በራሱ ተጋድሎ ነበር፡፡  ዐራት ኪሎን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ ላወረደው መቅሰፍት ዋናው ተጠያቂ ራሱ የአማራ ሕዝብ ነው፡፡ ተጠያቂ የሆነበት ምክኒያት ደግሞ ደርግን ጎዳሁ ብሎ፣ መሠረታዊ ጠላቴ ነህ ብሎ ማኒፌስቶ የጻፈበትን የሕልውና ጠላቱን በቀጥታና በተዛዋሪ በመርዳቱ ነው፡፡  በደርግ ላይ የነበረውን ቅሬታ ለጊዜው ወደ ጎን ትቶ፣ የሕልውናውን ጠላት ወያኔን እተፈጠረበት እደደቢት ላይ በመቅበር የሕልውናውን አደጋ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካስወገደ በኋላ፣ ፊቱን ያስተዳደር በደል ወደሚያደርስበት ወደ ደርግ ማዞር ሲችል፣ በተቃራኒው ግን ደርግን ይብላ ብሎ ወደ ዐራት ኪሎ ባሳለፈው በደደቢቱ ጅብ እሱ እራሱ ተበላ፡፡ 

በሌላ በኩል ግን ዐብይ አሕመድ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘመተው እንደ መለስ ዜናዊ አማራ ጠላቴ ነው ብሎ በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጆ ሳይሆን፣ የአማራን ቋንቋ እየተናገረ አማራን መስሎና ተመሳስሎ ነው፡፡  ይህ ደግሞ የወራዳነት መለያ ባሕሪ ነው፡፡  ጦርነት ሳያውጅ ጦርነት የሚከፍት ወራዳ ብቻ ነው፡፡  ጦርነት ሳያውጅ ጦርነት የከፈተ ወራዳ፣ በድንገት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ ባልተዘጋጀው ባላንጣው ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያደርሳል፡፡  ዐብይ አሕመድም በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ይሄንኑ ነው፡፡  

ታሪክ በተደጋጋሚ የሚመሰክረው ደግሞ በድንገት ጦርነት የከፈተ ወራዳ ባጭር ጊዜ ውስጥ ድል አድርጎ፣ ድሉን ሕጋዊ መልክ ካላስያዘው በስተቀር፣ ከዋለና ካደረ መሸነፉ አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡  ይህን እውነታ ደግሞ ዐብይ አሕመድ ባያውቀውም ኦነጋዊ አማካሪወቹ እነ ሌንጮ ለታ በደንብ ያውቁታል፡፡  ዐብይ አሕመድ አማራን አዘናግቶ በአማራ ሕዝብ ላይ በድንገት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ያገኘውን ከፍተኛ ድል ከወያኔ ጋር በመደራደር ቋሚ ለማድረግ የሚሯሯጠውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡  

ዐብይ አሕመድ በአማራ ሕዝብ ላይ የረጨው አፍዝ አደንግዝ በፍጥነት እየከሸፈ እንደሆነና፣ አብዛኛው የአማራ ሕዝብ፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ከአፍዝ አደንግዙ ጨርሶ እንደተላቀቀ አውቋል፡፡  ከንግዲህ በኋሏ ኢትዮጵያ ሆዴ፣ ኢትዮጵያ ልቤ እያለ ማጭበርበር እንደማይችል ተገንዝቧል፡፡  የማጭበርበር ትሪኮቹን ሁሉንም ሟጦ ጨርሷል፡፡  ከማጭበርበር ውጭ ሌላ ምንም ስለማያውቅ ደግሞ የሚያረገው ጠፍቶት ግራ ተጋብቷል፡፡  በሽመልስ አብዲሳ አንደበት በመናገር ሰብረነዋል ብሎ የተበተበት አማራ ተጠናክሮ እየመጣበት እንደሆነና ጊዜ እንደሌለው ተረድቷል፡፡  ስለዚህም፣ በአማራ ሕዝብ ላይ እስካሁን ካደረሰው የባሰ ጥፋት ለማድረስ የሚሞክረው ተስፋ እየቆረጠ ባለበት ባሁኑ ወቅት ነው፡፡  

ለአማራ ሕዝብ የሚበጀው ደግሞ ተስፋ እየቆረጠ ያለ ጠላት ተስፋ ሳያስቆርጠው፣ ለዐብይ አሕመድ ሜንጨኛ አጸፋውን ለመስጠት ነፍጡን መወልወል ነው፡፡  የአማራን ነፍጥ ቀማ ብሎ ደንገጡሩን ተመስገን ጡሩነህን ከላከ ደግሞ ነፍጤን የምትወስደው ሬሳየን ተራምደህ ነው ብሎ እቅጩን መንገር ነው፡፡  

ጨዋነት የሚሠራው ጨዋነትን ለሚያውቅ እንጅ፣ ፈሪነት ለሚመስላቸው ለዐብይ አሕመድ ዓይነቶች፣ ባጠቃላይ ደግሞ ለኦነጎችና ለወያኔወች አይሠራም፡፡  ወያኔወችና ኦነጎች ጀግኖች ወይም ልሂቆች የሚሏቸውን ሁሉንም ብትመለከቷቸው፣ ባልተገራ አፋቸው ኢትዮጵያን፣ አማራን፣ ተዋሕዶንና፣ አጼ ምኒሊክን የሚያበሻቅጡ ናቸው፡፡  በወያኔና በኦነግ ዘንድ ይበልጥ ጀግና የሚያሰኘው ይበልጥ ስድ አፍ መሆን ነው፡፡  የአማራን ሕዝብ ቆማጣ፣ የአማራን ልሂቆች ጥፍራም ማለት የጀግንነት መግለጫ ነው፡፡   

የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጥፋት ወያኔንና ኦነግን በማያውቁት ቋንቋ በጨዋነት ለማናገር መሞከሩ ነው፡፡  እነሱ ደግሞ ለአምሳ ዓመታት ቢነገራቸው ሊገባቸው ያልቻለው ቋንቋውን ስለማያውቁት ስለሆነ አይፈረድባቸውም፡፡  የአማራ ሕዝብ ወያኔና ኦነግ እንዲሰሙት ከፈለገ፣ ማናገር ያለበት ለነሱ በሚገባቸው በኃይል ቋንቋ ብቻ ነው፡፡  የኦነግንና የወያኔን አካፋወች ደግሞ ምንም ሳያድበሰብስ አካፋ ማለት አለበት፡፡  

ሌላው የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጥፋት መቸም ሊወዱት የማይችሉትን ኦነጎችና ወያኔወች እንዲወዱት አጉል መጣጣሩ ነው፡፡  ውዴታ ቸሬታ፣ ከበሬታ ግዴታ ነው፡፡  ሰውን እንዲያከብር እንጅ እንዲወድ ማስገደድ አይቻልም፡፡  ማስገደድ ይቅርና ማስተማርም አይቻልም፡፡ እኔ እበልጥሃለሁ በማለት ሊርቅህ የሚሸሽን ሰው፣ እኩል ነን እያልከ ብትከተለው በበለጠ ፍጥነት ይሸሽሃል፡፡  እኔ እበልጠሃለሁ ብለህ በተቃራኒ አቅጣጫ ከሄድክ ግን ቢያንስ ባለበት ይቆማል፡፡  የመለማመጥ ትርፉ መከራን ማርዘም፣ ፍዳን ማብዛት፣ አበሳን ማባስ ብቻ ነው፡፡  

የአማራ ሕዝብ ማድረግ የሚችለው ወያኔና ኦነግ ከማክበር አልፈው እንዲፈሩት እንጅ እንዲወዱት አይደለም፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ወያኔና ኦነግ እየሄዱበት ያለው መንገድ ይበልጥ የሚጎዳው እነሱን መሆኑን ባፋጣኝና በተግባር በደንብ አድርጎ በማሳየት እንጅ፣ ሲጨፈጭፉት እባካችሁ አትጨፍጭፉኝ እያለ በመለማመጥ አይደለም፡፡  ሲዘልፉት ደግሞ ምንም ሳያቅማማ አጸፋውን መወርወር የግድ ነው፣ አለበለዚያ የፈራ ስለሚመስላቸው አያቆሙምና፡፡ 

ዐብይ አሕመድ ወራዳ ስለሆነ የሚያከብረው የሚያዋርዱትን ነው፡፡  አሻጋሪ ብሎ ባሞገሰው በአማራ ሕዝብ ላይ ተጨማልቆ፣ አጭበርባሪ እያለ የሚሞሸልቀውን ወያኔን የሚያፈቅረው፣ ክብር የማይወድለት፣ ክብረቢስ ወራዳ ስለሆነ ነው፡፡  አልጋ ሲሉት ዐመድ የመረጠው ደግሞ ተፈጥሮው ስለሆነና ዱላ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡

  EMAIL:  mesfin.arega@gmail.com

 

Filed in: Amharic