>

* የመቀሌው ውጊያ " (ሀይማኖት ተፈራ)

* የመቀሌው ውጊያ “

ሀይማኖት ተፈራ

 

ጣሊያኖች የአምባላጌው ጦርነት በኢትዮጵያኖች አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሽንፈታቸውን አምነው መቀበል አልቻሉም።
ጄነራል ባራቲየሪ በወገኖቹ በኩል ትችት እና ነቀፌታ ስለበዛበት ሽንፈቱን በቀላሉ አምኖ መቀበል አልቻለም። በሌላ ወገን ጠቅላይ ሚንስትሩ ክሪስፒ በላከለት ቴሌግራም እንዲህ ብሎታል “መንግስት በሠውም በመሳሪያም የጠየቅከውን ልኮልሃል ሃገሪቱ አንድ ድል ትጠብቃለች እኔም ራሴ እጠብቃለሁ ይሄም ድል አንድ ጊዜ ለዘለቄታው የሃበሻን ጉዳይ የሚደመድም መሆን አለበት በምታደርገው ነገር ተጠንቀቅ የራስህና የኢጣልያ ክብር አለበት”
ጄነራል ባራቲየሪ  የመቀሌ ከተማ ለአላጌና ለአሸንጌ፤ ለአዲግራትና ለአስመራ አማካይ ቦታ መሆኑን አስቀድሞ አይቶ ስለነበር ሟቹ ማጆር ቶዞሊን በስፍራው ምሽግ እንዲገነባ አዞት ነበር። ማጆር ቶዞሊ ወደ አምባላጌ ያለፈ ጊዜም የምሽጉን ስራ ጋልያኖ ከአርሞንዲ ጋር በመተባበር ዳር አድርሶታል። በወቅቱ የእንዳእየሱስ ገዳም ለምሽጉ ስራ እንቅፋት ስለሆነባቸው ታቦቱን አስወጥተው በቤተክርስቲያኒቱ ህንፃ ላይ የኢጣልያን ባንዲራ ሰቅለው በውስጡና በደጃፉ ደግሞ መድፍና ጠመንጃ ጠመዱበት።
በራስ መኮንን የሚመራው ጦር የአላጌን ምሽግ ከደመሠሠ በኋላ ለእርዳታ የመጣውን የጄነራል አርሞንዲን ጦር እያባረረ መቀሌ ምሽግ አቅራቢያ ደረሠ። ከደረሠም በኋላ ግን ራስ መኮንን እንደሁልጊዜው እምነታቸው ጣልያንን በሠላም ከሃገር አስወጣለሁ በሚል ለጄነራል ባራቲየሪ ደብዳቤ ላኩለት። ምንም እንኳን ራስ መኮንን እርቁን በጣም ይፈልጉት የነበረ ቢሆንም በኢጣሊያኖች ወገን ደግሞ በተቃራኒው የእርቁን ንግግር ጊዜ ለመግዣ፣ምሽግ ማጠንከሪያ፣ በራሶቹና በመኳንንቱ መካከል ስለጦርነቱ ያለውን ስሜት ለማወቂያ እድሉ ካጋጠመም ሃሳብ ማስቀየሪያ ብሎም ያለውን የመሳሪያና የወታደር ቁጥር ማወቂያ እንዲሁም የወታደሩን ስሜት ለማወቅ ነበር የተጠቀሙበት።
ራስ መኮንን ለኢጣልያ ጦር አዛዥ ደግመው እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላኩለት “እኔ ባንተ የሚታዘዘውን ትንሽ ምሽግ ለመውጋት አልመጣሁም እኛ ብዙ ስለሆንን ያንተን መድፎች አንፈራም አላጌን ልታስታውስ ይገባል። በከንቱ ደም አናፍስስ እኔ እስከ ምጥዋ ድረስ ሸኚ ልስጥህ ጓዝህንም እዛው ድረስ ልልክልህ እችላለሁ” የእርሱ መልስ ግን ፍጹም ንቀትና ጥጋብ የተሞላበት ነበር። ሲመልስም “ከስፍራዬ አልነቃነቅም ጓዜንና ምሽጉን መውሰድ የፈለግህ እንደሆነ ናና ውሰድ። በመድፍ በትር እቀበልሃለሁ” በማለት ነበር። የጋሊያኖ መልስ በአላጌ ጦርነት ዋዜማ ማጆር ቶዞሊ ከመለሠው ጋር ይመሳሰላል ይሄም ጣልያኖች ከስህተታቸው እንደማይማሩ ያሳያል።
የንጉሱ ጦር መቀሌ ከደረሠ በኋላ ከምሽጉ በምዕራብ በኩል በደብሪ የሸዋ ጦር፤ በምስራቅ በኩል የንጉሥ ተክለኃይማኖትና የራስ መንገሻ የሐንስ ጦር፤ በጋምቤላ በኩል የራስ መንገሻ አቲከም፣ የራስ ወሌ፣ የደጃች ወልዴ ጦር፤ ወደ ጨለቆት በሚወስደው መንገድ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ጦር፣ የራስ መኮንንና የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር ሰፈረ።
ሆኖም ግን እቃ በሚወርድበት ጊዜ አንድ በቅሎ ወደ ኢጣልያኖች ሠፈር ፈረጠጠ አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ኢጣልያኖች ተኩስ ከፈቱ። ተኩሱም ሊቆም ስላልቻለ ሊቀ መኳስ አባተና በጅሮንድ ባልቻ ታዘው የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ መሸ። ሊቀመኳስ አባተ በስተግራ በጅሮንድ ባልቻ በቀኝ ምሽግ ሠርተው መድፍና መትረየሳቸውን ጠመዱ።
አነጣጥሮ በመተኮስ የሚታወቁት ሊቀ መኳስ አባተ በርቀት መነፅራቸው ቢያዩ ጣልያኖች እንዳእየሱስ ገዳምን ታቦቱን አስወጥተው በግራና በቀኝ መድፍ ጠምደውበት ተመለከቱ ከዛም አነጣጥረው ቢተኩሱ የመድፉ ጥይት በመስኮት ገብቶ የሌላውን መድፍ እግር ሠበረው ጣልያኖችም ይሄን ባዩ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያውያን ወገን ጥይት እንደበረዶ አዘነቡባቸው።
 ይቀጥላል ……..
Filed in: Amharic