>

ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ እና የዋልያ መጻሕፍት ውይይት ትዝብት ( ዮሴፍ ፍስሀ)

ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ እና የዋልያ መጻሕፍት ውይይት ትዝብት 
ዮሴፍ ፍስሀ

-በ12/06/2014 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” በተሰኘው መጽሐፍ በዋልያ የመጻሕፍት ውይይት መድረክ ተጋብዞ ለውይይት መጥቶ ነበር፡፡ ከተሳታፊያን የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተውበታል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጠያቂ ጥያቄ ከመጽሐፉ ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ስለ መጽሐፉ ለመወያየት መጥተን ሌላ ነገረር በማንሳት የውስጥ ስሜታቸውን ሲጠይቁ የሚውሉ የመድረኩን ዓላማ የማይረዱ ብዙ ጠያቂዎችን ታዝበናል፡፡  ዋልያ የመጽሐፍ ውይይት መድረክ ላይ በአግባቡ አንብበው ጥያቄ የሚጠይቁ በጣም ውስን ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የመድረኩን አላማ ብንረዳ መልካም ነው፡፡ ይህን መድረክ በአንዳርጋቸው መጽሐፍ ላይ ወሳኝ የሚባሉ ጥያቄዎችና ትችቶች ሊነሱበት ሊቀርቡበት ይገባ ነበር፡፡ እድል አግኝቸ መጠየቅና መተቸት ባልችልም በጣም የገረመኝና የታዘብኩት ግን አቶ አንዳርጋቸው ከዚህ በፊት ስለ መጽሐፉ አግባብ በሆነ መልክ የቀረበበትን ትችት ከመቀበል ይልቅ ስለ መጽሐፉ በማንአለብኝነት የሰጠው ማብራሪያ ነው፡፡ የውይይቱ ዓላማ የገጽታ ግንባታ ይመስል ነበር፡፡ ውይይቱን ለታዘበ ለመሆኑ “ያ ትውልድ” ከተባሉት መካከል እቡይነትን ልብሱ ያላደረገ በትእቢት ያልተወጠረ ማን ይሆን ያሰኛል? አቶ አንዳርጋቸው በመጽሐፌ ጉዳይ “አንዳችም የሚያደናግር ነገር የለበትም”፣ “ከኢትዮጵያ የታሪክ ፕሮፌሰሮች የተሻለ የታሪክ መጽሐፍ ጽፌያለሁ”፣“በታሪክ አጻጻፍ አረዳዴ የተሻልኩ ነኝ” በሚል የትእቢትና ትክክል ነኝ ሐሳቦችን ሲያንጸባርቅ ነበር፡፡ የታሪክ አረዳድ ችግሩን በመጽሐፉ  እንዳነበብነውና እንደተረዳነው እንደነገረን አሁንም ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ከሐሳቤ አልነቃነቅም ባይ ነው፡፡ ዓላማው አሁንም ከዚህ በፊትም እንደተናገረው “ለማንጫጫት” ይመስላል፡፡ ግን “ማንጫጫት” ሙያ አይደለም፡፡
-በዋልያ መጽሐፍ ውይይት መድረክ በመጽሐፉ በግልጽ የጻፋቸውን ስህተቶቹን በሐሰት ለማስተባበል የሄደበት ርቀት አሳፋሪና አሳዛኝ ነበር፡፡  ፊንፊኔን በአዲስ አበባ በሚል የተቀየረ አስመስሎ ያቀረበውን ኦነጋዊ ትርክት ለምሳሌ“ፊንፊኔ የሚለው የአካባቢው ስም አዲስ አበባ ወደሚል ስም የተቀየረው  በእቴጌ ጣይቱ ብጡል ነው፡፡” (ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር፣ ገጽ 59) ፈጽሞ ስህተት መሆኑን መቀበል አልፈለገም፡፡ በግልጽ የጻፈውን ነገር “ለማለት የፈለኩትን ስላልተረዳችሁኝ ነው” በማለት ያጭበረብራል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሐሳቡ ይቸከል መብቱ ነው፡፡ ተቸከለ ማለት ግን ትክክል ነው የሚያስብለው አይመስለኝም፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፕ/ር ሃብታሙ መንግሥቴ የጻፈልን “በረራ ቀዳሚት አዲስ አበባ” የሚለውን መጽሐፍን ተደንቄበታለሁ አንብቤያለሁ ካለ ፊንፊኔ አዲስ አበባ እንዳልሆነች ተገንዝቦ ተሳስቻለሁ ማለት በተገባው ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በዋልያ መጽሐፍ ውይይት ላይ ከዚህ በፊት የተነሳበትን ተገቢ ጥያቄዎች ተረድቶ ተሳስቸ አሳስቻለሁ አደናግሬያለሁ በማለት ከመጸጸትና ስህተቱን ከማመን ይልቅ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ለማስተባበል ሲጋጋጥ ነበር ያስተዋልነው፡፡
-በመጽሐፉም በዋልያ ውይይት እንዳስተዋልኩት በግብዝነት “መግባቢያ” በሚለው ሥር “…ምንም ሳይጎትተኝ እውነትን ብቻ ሙጥኝ ብዬ ….ሁሉም ተቀምጦበት በነበረበት ቦታ ላይ የሚያውቀውን እውነት ብቻ ተመርኩዞ መጻፍ አለበት፡፡ እኔም በዚህ መጽሐፍ እያደረኩ ያለሁት ይህንን ነው፡፡ ….ለመጭው ትውልድ ሳይዛባ የማቅረቡን ኃላፊነት መወጣት መሻቴ ነው ይህን መጽሐፍ የወለደው…” በማለት ጽፎ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው “እውነትን ብቻ ሙጥኝ ብዬ ሀቅ” የሚለው ታሪክን በማዛነፍ የማያውቀውን እና ያላለፈበትን የደብተራ ትምህርትና እውቀት ማንጓጠጥ መዝለፍን ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ግን በጭፍን ማንጓጠጥ ሐቅና እውነት ሊሆን አይችልም፡፡  ለምሳሌ ያህል ለመሆን አቶ አንዳርጋቸው 1950ዎቹ ምንም አይነት ዘመናዊ ትምህርት ያልቀመሱት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ(1885-1962 ዓ.ም.) የተባሉ ደብተራ ከዲማ አብነት ትምህርት ቤት ወጥተው ጣልያን ሀገር ድረስ የተማሩትን ካቶሊኩን ዶ/ር አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍን ገለባና ባዶ እንዳደረጉለት ያውቃል? “መድሎተ አሚን” የተሰኘ መጽሐፍ እንደጻፉ ያውቃል? መኖሩን ቢያውቅስ ደብተራዎች ከመሳደብ የዘለለ ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሌለው አንዳርጋቸው ጽጌ “መድሎተ አሚን” የተሰኘውን መጽሐፍ ቢያነበው መረዳት ይችላል ይገባዋል?
– እንደ አቶ አንዳርጋቸው  ጽጌ አይነት የደብተራዎችን ሥራ አንብቦ የማይገባውና መገንዘብ የማይችል ሰው በምንም ምክንያት እውቀታቸውንና ትምህርታቸውን የማናናቅ የማጠልሸት “አነብናቢ”፣ “በጨለማው ዘመን በነበረው የደብተራ የእውቀት ባህል ተተብትቦ…” የማለት ሞራል ሊኖረው አይገባም ነበር፡፡ ደብተራዎች ማለት ዶክትሬት አገኘንበት የሚሉትን ጽሑፍ ገለባና ምክንያት አልባ የሚያደርጉ የሰላ ጭንቅላት ያላቸው እንደሆነ መረዳት መልካም ነው፡፡ ደብተራዎች ማለት የክርክርና ሙግት ደርዝ በብልት በብልቱ የሚያውቁ ማለት እንደሆነም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በደብተራው የተጻፈው “መድሎተ አሚን” ከሃይማኖት ትምህርት በተጨማሪ ሙግትና ክርክር ምን መምሰል እንዳለበት የምንማርበት ድንቅ ደብተራ የደከመበት መጽሐፍ ነው፡፡ ደብተራዎች አሰላስለው ተመራምረው የተቀኙትን ቅኔ መረዳት ትችላለህ? በማለት አንዳርጋቸው ጽጌን አልጠይቀውም፡፡ ምክንያቱም የግዕዝ ተነሽ ወዳቂ በትንሹ አያውቅምና፡፡ በሌላኛው መጽሐፉ እንደታዘብነው 66 መጽሐፍ ቅዱስ እና ሰማኒያ አንድ የሚባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ ማወቅ አልቻለም፡፡ በእቡይነት ደብተራን ከማናናቅ ጠጋ ብሉ ቢጠይቃቸው እንኳን ስለ ሰማኒያ አሐዱ ሌላም ትምህርት በነገሩትና ባስረዱት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ዘመንም ደብተራን የሚያንቋሽሹ የድንቁርና መገለጫ በማስመሰል በየመጻሕፍቱ የሚለቀልቁ የግዕዝ ተነሽ ወዳቂ የማያውቁ ማንኛውም ፖለቲከኛ ነኝ ባዮች ዲግሪያቸውን ሰብስበን ብንጋግራቸው ያለማጋነን መቸውንም ደብተራ በአማን ነጸረ  የጻፈውን “ጽንዐ ተዋሕዶን” የመሰለ መጽሐፍን ሊያምጡና ሊወልዱ አይችሉም፡፡ እንኳን ማማጥና መውለድ መጽሐፉን አንብበው የሚገባቸው አይመስለኝም፡፡ በተለይ “ያ ትውልድ” ከሚባሉት መካከል ምንም የቤ/ን ትምህርት ፍንጭ ሳይኖረው አካበድክ የሚል ካለ አካብዳለሁ ከፈለክ አንብብና ይገባህ እንደሆነ አረጋግጥ እልሀለሁ፡፡ ደብተራ ማለት በያ ትውልድ የትምህርት ደረጃ ሊገባቸው የማይችልንና መገንዘብ የማይችሉትን መጽሐፍን የሚጽፉ ማለት ነው፡፡ በደብተራዎች እንኮራለን ያኮሩናል፡፡ ደብተራነት ይለምልም፡፡
-ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ(ዶ/ር) “መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 3 ” በተሰኘው መጽሐፉ ስለ አንደርጋቸው ጽጌ እና መሰሎቹ የሚከተለውን ብሎ ነበር “ቤተ ክርስቲያኒቷን ምኗንም ሳያውቁ የሚንቁ፣ከእውቀታቸው እጅግ በጣም ጥቂቱን ያህል እንኳ የማያውቁትን የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና መሪጌቶች እንደ እነርሱ የማርክሲዝም ሌኒንንዝም ባዶ ሽምደዳና የቃላት ጋጋታ እየመሰላቸው “አነብናቢ ደብተራ” እያሉ መሳደቢያ ለማድረግ የሞከሩ፣ይህን ጭፍን አላዋቂነታቸውንም ሳያፍሩ በመጽሐፍ የጻፉ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ ሰዎች የዚያን ዘመኑ የአእምሮ ማንጠፍ ሥራ ተጠቂዎችና ማሳያዎች ናቸው፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ “ነጻነትን የማያውቁ ነፃ አውጭ”-አንዳርጋቸውና መሰሎቹ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስሟን እንጅ አስተምህሮዋን እና ትምህርቷን በአጠቃላይ ውስጧን ምንም ሳያውቁ የሚንቁና የሚጠሉ፣በባዶው የሞሉ በሽታ የሰከሩ የዚያን ዘመን ትውልድ ማሳያዎች ሆነው የተረፉ “ቅርሶች” ናቸው፡፡ እድሜ ሰጥቷቸው ይህን ያህል ዘመን ሲኖሩ እንኳን ከስህተታቸው አለመማራቸው ከመጀመሪያው አእምሮው ታጥቦ የተበላሸን ሰው እድሜ እንኳን ሊፈውሰው የማይችል መሆኑን ያሳያል፡፡ በርግጥ ከዚያን ዘመን የልጅነትና የባዶነት እብደታቸው የባነኑና ራሳቸውን በጸጸት የሚመለከቱ፣በአገራቸውና በትውልድ ላይ ያደረሱትን ጥፋት እንዳልተፈጸመ አድርጎ ለመመለስ ባያስችላቸውም ለግላቸው የተመለሱና ንስሐ የገቡም አልፎ አልፎ አልጠፉም፡፡ (መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 3፣ ገጽ 196)  ዲ/ን ያረጋል በትክክል የአቶ አንዳርጋቸውን መንፈስ ገልጾታል፡፡
-አቶ አንዳርጋቸው በየመጽሐፉ ደብተራዎችን ሲያንጓጥጥና ሲሳደብ የሚገልጹ ለምሳሌ ያህል እንጥቀስ
1. ታላላቅ ነገሥታት ሳይቀሩ ይህንን አይነቱ ህልም እና ምኞት እንዲሳካላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት እና በምልጃ ሲያስጨንቁት እንደኖሩ የሚያሳዩ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከዚህም ውጭ ከደብተራ ፣ከጠንቋይ፣ከአጋንንት ጎታች፣ ከኮከብ ቆጣሪ እና ከአስማተኛ ዘንድ ሳይቀር እርዳታ መጠየቅ በስፋት የተስማማ ልምድ ነበር፡፡(ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ፣ 2010 ዓ፣ም፣ገጽ-53)
2. ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ፣ ገጽ- 84፣85፣86 ..ይመልከቱ
3. በሀገራችን ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የደብተራ የእውቀት ባህል እና የጉልተኛ ማህበራዊ እሴቶች በግራው የፖለቲካው ማንነት ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ (ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ፣ገጽ-282)
4. የደብተራ እና የጉልተኛ  ኋላቀር አመለካከት እና ድርጊት ለመሸፈን…… (ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ፣ገጽ-284)
5. በጨለማው ዘመን በነበረው የደብተራ የእውቀት ባህል ተተብትቦ፣ ከአብርሆት ተጣልቶ በመኖር ብቻ የሚገለጽ አውዳሚነት አይደለም፡፡ (ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ፣ገጽ-299)
6. መተተኞች…. (ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ-125 127 እና 135)
7. አብዛኛው ተማሪ ትምህርቱን እንደ ደብተራ በቃሉ የሚያጠና በቃሉ የሚገለብጥና የሚደግም ነበር፡፡ራሱ ፈጣሪ ፈልሳፊ ተመራማሪና ጠያቂ የሆነ በማወቅ ጥማት የተቃጠለ ትውልድ ለመፍጠር አልነበረም፡፡ (ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር፣ ገጽ-135)
-እውነታው አንዳርጋቸው በዋልያ ዛሬ ራሱን በራሱ እያንቆለጳጰሰ ስለ መጽሐፉ እንደነገረን አይደለም፡፡ የደገመልን ቀድሞ በመጽሐፉ የነገረንን አሳሳች ሐሳብ ነው፡፡ አንዳንድ ሐሳቦችን በተጨማሪ ከመጽሐፉ  ለማንሳት ያህል
1.) በመጽሐፉ ገጽ 25 ስለ በቢቢሲ ሰማሁት በሚለን በታሪክ የነበረው ክርክር ማለትም ጸሐፊው የራሱን ምናብ በመጠቀም ስለዘመኑ ታሪክ እንደጻፈ እንዲሁም ታሪክ እንደ ደረቅ እንጨት ያቀረባቸውን ሰዎች እኔ ሥጋና ደም ያላቸው አድርጌ አቅርቤያለሁ በማለት ነግሮናል፡፡ የአንዳርጋቸው የታሪክ አረዳድ ችግር የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ምናብ መካተት አለበት አጥንት ከሆነው ታሪክ ላይ ሥጋ ጣል ማድረግ አለበት በሚለው ምሁር ክርክር ስለተመሰጠና ስላመነበት በመጽሐፉ በተለይ ስለ ቤተሰቡም ሆነ ኢህአፓ የነገረን የትኛው ሥጋና ደም ምናብ አጥንትና ሥጋ እንደሆነ ለአንባቢያንም ሆነ ለወደፊቱ ለሚመራመሩ የታሪክ እጥኝዎች መጽሐፉን የታሪክ ምንጭ ለማድረግ ሥጋውን  ከአጥንቱ ምናቡንና ልብ ወለዱን  ከእውነታው ለመለየት በጣም አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ይመስለኛል፡፡
2.) ገጽ 255 -256 ላይ “ …የመኢሶን አባል የነበረችውን ዶ/ር ንግሥት አዳነን ያነሳል፡፡ …ሦስቱም የአቶ አዳነ ልጆች አጥንት የት እንደወደቁ አይታወቅም፡፡”
-ዶ/ር አማረ ተግባሩ በጻፈልን “ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ገጽ 193  ኃይሌ ፊዳ፣ ዶ/ር ንግሥት አዳነ …ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጋር እንደተቀበሩ ያስረዳናል፡፡ በተጨማሪ አቶ ታምራት ጀንበሬ በጻፈልን “ቀዳማዊ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ “በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 299—300 ስናነብ የምናገኘው ዶ/ር ንግሥት አዳነ ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጋር የተገደሉትና የተቀበሩት አዲስ አበባ በከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ክልል በሚገኘው ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ቤት ሐምሌ 7 1971 ዓ.ም. እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ አቶ አንዳርጋቸው “የአቶ አዳነ ልጆች አጥንት የት እንደወደቁ አይታወቅም” የሚለው ትክክል አይደለም፡፡ የታሪክ ምንጮች እንደሚያስረዱን ቢያንስ የዶ/ር ንግሥት አዳነ አጥንት የት እንደወደቀ ይታወቃል፡፡
3.) ገጽ 65 ላ “ግዕዝ ዘመን አቆጣጠር” በማለት የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ለማለት የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ለመሆኑ የግዕዝ ዘመን አቆጣጠር የሚባል አለ? የቤተክርስቲያን ስለሆነ የኢትዮጵያ ለማለት አይመጥንም ለማለት የፈጠረው ይሆን? በነገራችን ላይ ተስፋየ ገብረ አብ አንድ መጽሐፉ ላይ የግዕዝ ዘመን አቆጣጠር በማለት ሲገልጽ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ተስፋየ ገብረ አብ ተጽእኖ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ምን ያህል ይሆን?
-ለማንኛውም እኔም አግባብነት ያለው ትችት እንደሆነ ያመንኩበት የተማርኩበት እና የተስማማሁበት በአንዳርጋቸው ጽጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” መጽሐፍ ላይ የሰላ ትችት ያቀረቡትን የሁለት ምሁራን አስተማሪ ጽሑፍና ውይይት ልጋብዛችሁ
1.) በዶ/ር መሰለ ተሬቻ -ሊንኩት ተከትለው ያንብቡ
2.) በአቶ አቻምየለህ ታምሩ -ሊንኩን ይከተሉና ያድምጡ
-ስለ አቶ አንዳርጋቸው መጽሐፍ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ተያያዠ ጉዳይ ላይ ያነሳውን ሐሳብ ባለንበት ብንወያይበት መልካም ነው፡፡
Filed in: Amharic