>

"ከስልጣን ክፍፍል ውጭ በቆሰሉ ታሪኮቻችን ህክምና ላይ እንደራደራለን....!!!" ጠ/ ሚ አብይ አህመድ

 

“ከስልጣን ክፍፍል ውጭ በቆሰሉ ታሪኮቻችን ህክምና ላይ እንደራደራለን….!!!”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

 

ሃሚድ አወል


ችግርን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት መንግስት በሩ ክፍት መሆኑን ለፓርላማ አባላት ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 15 ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከህወሓት ጋር እስካሁን የተጀመረ ድርድር አለመኖሩን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከድርድር ጋር በተያያዘ ለጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። አቶ ክርስቲያን፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና እሳቸው “አሸባሪ” ሲሉ በጠሩት ህወሓት መካከል ድርድር እየተካሄደ ስለመሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለጸ መሆኑን ጠቁመው “ድርድሩ ምን ያህል እውነት ነው?” የሚል ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም፤ እስከዚህ ደቂቃ ድረስ” የሚል ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥተዋል።  አብይ አክለውም “ስለድርድር ብዙ ሲወራ እሰማለሁ ግን እስካሁን ድርድር አልተደረገም። አልተደረገም ማለት ግን እስከነአካቴው ድርድር የሚባል ነገር አይኖርም ማለት አይደለም” ሲሉ ድርድር ሊደረግ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።

አብይ “የሰላም አማራጭ ካለ፣ TPLF [ህወሓት] ቀልብ ከገዛ፣ በጦርነት እንደማያዋጣው እንደማያሸንፍ ከተገነዘበ፤ እኛ በደስታ ነው የምናየው” ሲሉ መንግስታቸው ለድርድር ያለውን ዝግጁነት ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከህወሓት ጋር የተጀመረ ድርድር እንደሌለ በዛሬው የፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ቢናገሩም፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ግን በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል ንግግሮች መኖራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።

ምክትል ጸሐፊዋ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ “ንግግሮች ቀጥለዋል። ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው አንፃር አነስተኛ ግጭቶች ናቸው የሚታዩት። በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ” ሲሉ በፌደራል መንግስቱ እና በአማጽያኑ መካከል ንግግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ከፈጀው የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፖለቲካዊ ጉዳዮች ማብራሪያ ውስጥ፤ የድርድር እና አገራዊ ምክክርን የተመለከተው ገለጻ የወሰደው 13 ደቂቃ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ከህወሓት ጋር ጦርነት የገጠመው “ኢትዮጵያን ለማጽናት” መሆኑን ለፓርላማ አባላት በድጋሚ አስታውሰዋል።

ድርድርን በተመለከተ ደግሞ “ኢትዮጵያን ለማጽናት ህይወታችንን ገንዘባችንን የምንገብር ከሆነ፤ ኢትዮጵያን ለማጽናት ስሜታችንን አምቀን መነጋገር የሚቻል ከሆነ ደግሞ በደስታ ማየት ጥሩ ነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር በገለጻቸው “ድርድር እና ውይይት” የሚሉትን ቃላት የተጠቀሙት ወደፊት ይካሄዳል ለተባለው “አካታች ብሔራዊ ምክክር” ነው።

ይህን ምክክር የሚመራው በትላንትው ዕለት 11 ኮሚሽነሮች በፓርላማ የተሾሙለት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። አብይ ፓርቲያቸው ብልጽግና የሚመራው የፌደራል መንግስት ሁለት ጉዳዮችን ለድርድር አጀንዳነት እንደማያቀርብ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

መንግስት ለድርድር የማያቀርበው የመጀመሪያው ጉዳይ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠቀሰው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም” ነው። “የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ከሆነ፤ ትንሽ ነው ትልቅ አንልም፤ አንደራደርም” ያሉት አብይ “የኢትዮጵያን ጥቅም እስካስከበረ ድረስ ግን ለመስማት ለመነጋገር ችግር የለብንም” ብለዋል።

“የስልጣን ክፍፍል” ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለድርድር አይቀርብም ያሉት አጀንዳ ነው። በሌሎች ሀገራት ስልጣን ክፍፍልን አጀንዳ ያደረጉ ውይይቶች እንደነበሩ የጠቆሙት አብይ፤ ፓርቲያቸው በ“ስልጣን ክፍፍል” ላይ ያለውን አቋም ለፓርላማ አባላቱ በአጽንኦት አስረድተዋል።

“ስልጣን ክፍፍል የዚህ ድርድር አካል አይደለም፤ በምርጫ አልቋል። ለሚቀጥሉት አራት አመት ተኩል የኢትዮጵያ መሪ ብልጽግና ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንደራደርም። የምንደራደረው በቆሰሉ ታሪኮች ህክምና ላይ እና በምንገነባት ነገ ላይ ነው” ሲሉ የስልጣን ጉዳይ የድርድር አጀንዳ አለመሆኑን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Filed in: Amharic