>
5:18 pm - Wednesday June 16, 1126

"ሽኔ እና መንግስት ያፈናቀሏቸው እናቶች፤ የጸለዩላችሁ እናቶች እያለቀሱባችሁ ነው....!!!" (ያሬድ ሀይለማርያም)

“ሽኔ እና መንግስት ያፈናቀሏቸው እናቶች፤ የጸለዩላችሁ እናቶች እያለቀሱባችሁ ነው….!!!”
ያሬድ ሀይለማርያም

ይሄን መንፈስ የሚያደቅ እና እንቅልፍ የሚነሳ ፎቶ ትላንት ጠዋት ነው ያየሁት። ሙሉቀን በአይምሮዮ ውስጥ ሲመላለስ ውሎ አደረ። እኝህ እናት ከሁለት አመት በፊት ልጆቻቸው ታግተውባቸው እስካሁን የት እንደደረሱ ከማይታወቀው የደንቢዶሎ ተማሪዎች መካከል የአንዷ ተማሪ እናት ናቸው። ብዙ እናቶች ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚኖሩበት ቀያቸው ኦነግ-ሽኔ የተሰኘው ታጣቂ ቡድን አፈናቅሏቸው እና ገሚሱንም ልጆቻቸውን አግዶባቸው ደም እንባ እያለቀሱ ነው። የሽኔን ጭካኔ ሸሽተውና የሚታደገኝ መንግስት አለ ብለው ሰሞንን በርካታ ተፈናቃዮች ሰሞኑን ወደ ሸገር ቢመጡም መንግስት ሊንከባከባቸው ሲገባ ወደ አሩሲ እንዲመለሱ ተደረገ። እዛም የሚቀበላቸው አካል አጡ። መልሰው ወደ አዲስ አበባ መጡ። አዲስ አበባ ዳግም ፊት ነሳቻቸው። በፖሊስ ተገደውም ወደ ደብረ ብርሃን ተሸኙ። ደብረ ብርሃን ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈናቅለው በመጡ ብዙ ሺዎች አፍንጫዮ ድረስ ጢም ብያለሁና ቦታ የለኝም ብላ መልሳ ወደ አዲስ አበባ ሸኘቻቸው። ከአዲስ አበባ አሁንም በፖሊስ ተገደው ወደ መጡበት አሩሲ ተባረሩ። ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ አሩሲም አንቀበላችሁም ተባሉ። ከእኚህ እናት ጋር በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት፣ ሴቶችና አባወራዎችም አሉ።
ኦነግ-ሽኔ እና መንግስት አገር አልባ ያደረጓቸው እናት መሄጃ ሲያጡና ግራ ቢገባቸው አምርረው ወደ ፈጣሪያቸው ሲያነቡ የተነሱት ፎቶ ነው።
+ ይህ ፎቶ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ከበቂ በላይ ገላጭ ነው።
+ ይህ ፎቶ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ውስጥ በሰላም  መኖር ብቻ ሳይሆን ስደተኛ ወይም ተፈናቃይ ሆነው እንኳ መጠለያ አግኝተው መኖር ያልቻሉ ወገኖች ስቃይ ማሳያ ነው።
– ይህ ፎቶ ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጸልዩልኛል ያሏቸው የኢትዮጵያ እናቶች ዛሬ ደም እንባ እያለቀሱባቸው መሆኑን ማሳያ ነው።
– ይህ ፎቶ የኢትዮጵያ መከራ ከሸክም በላይ መሆኑን፣ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍል ሥርዓት አልበኝነት መንገሱን፣ ዜጎች የኑሮ ዋስትና ያጡና የሚሸሸጉበት ጥግ አጥተው ወደፈጣሪ እያለቀሱ መሆኑን ማሳያ ነው።
– ይህ ፎቶ መንግስት ዜጎችን ከነኦነግ ሽኔ እና መሰል ታጣቂዎች መታደግና ለደህንነታቸውም ጥበቃ ማድረግ አለመቻሉን ወይም ጉዳዮ ደንታ ያልሰጠው መሆኑን ማሳያ ነው።
– ይህ ፎቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ገለጻቸው የሳሏት ኢትዮጵያ እና መሬት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ የመሬትና የሰማይ እርቀት ያህል እንደማይተዋወቁም ማሳያ ነው።
ይህን እንቅልፍ የሚነሳ ፎቶ ሳይ ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ከመሞታቸው ጥቂት ሳምንታት በፊት የነገሩኝ ነገር ትዝ አለኝ።  አብይ አይምሮ ውስጥ ያለችውን እና መሬት ላይ ያለውን የኢትዮጽያ ጉዳይ የገለጹበት መንገድ የሚገርም ነበር። እንዲህ ብለው ነበር፤ ‘አብይ በአይምሮው ውስጥ እያየና እያለመ የሚጓዘው የዛሬ ሰላሳ አመት የምትኖረውን ኢትዮጵያን ነው። እሱ ባልከፋ፤ ግን እግሩ ስር ያለውን ትልቅ ገደል ግን እያየ አይመስልም። ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ገደል ነች። ጉርጓድ ውስጥ ገብቶ እንዳይሰነቀር እና እሱም፣ ህልሙም፣ አገሪቱም ገደል እንዳይገቡ ቢጠነቀቅ ጥሩ ነበር።’ በሚል ነበር የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በፖርላማ ውሏቸው ባደረጉት ንግግር ብዙ የፎረሹት ነገር ቢኖርም ሽኔን የሳሉበት መንገድ ግን የቆሙበትን የጉድጓድ ጫፍ ያለማስተዋል ይመስላል። ሽኔን ሲያጣጥሉ ትዝ ያለኝ እንዲሁ ፖርላማው ፊት ቀርበው  ‘ህውሃት አየር ላይ የተበተነ ዱቄት ነው። አየር ላይ የተበተነ ዱቄት መልሶ ዱቄት መሆን አይችልም።’ ያሉት ነገር ነው።
 ጠቅላዮ በኦነግ ሽኔ ከተሳደዱት እና መሸሸጊያ ካጡት ዜጎች ይልቅ ወንጪ ላይ የጀመሩት አገር የማስዋቢያ ፕሮጀክት በሽኔ መስተጓጎሉ እጅግ ያሳሰባቸው ይመስላል። በጦርነቱ ምክንያት በአማራና አፋር ክልል ከፈረሱት ትምህርት ቤቶች ይልቅ ጎርጎራ ላይ የሚገነቡት አገርን የማስዋቢያ ፕሮጀክት እንዲሁ እንቅልፍ እንደነሳቸው ከተደጋጋሚ ንግግራቸው መረዳት ይቻላል። የፕሮፌሰር መስፍን ንግግር ይሄኔ ድቅን ይልብሀል። ጠቅላዮ የሚናፍቋት የበለጸገች ኢትዮጵያ፤ ዛሬ በጦርነት፣ በርሀብ፣ በጎንዮሽ ጥቃትና ጭፍጨፋ፣ በብልሹ አስተዳደር፣ መረን በለቀቁ እና ጭቃኔ በተላበሱ ታጣቂ ቡድኖች ማዋከብ፣ በተፈናቃዮች እና የስደተኞች መከራ ተጠርንፋለች። እነዚህን ጉርጓዶች ለመሻገር መጀመሪያ አይንን ገልጦ ማየትና ጉርጓድ መኖሩን አምኖ መቀበል፣ ከዛም እንዴት ጉርጓዱን በጥንቃቄ መሻገር እንደሚቻል ማስላት የግድ ይላል። ጠቅላዩ ብዙ ጊዜ የአገሪቱን ችግሮች በአቧራና ዱቄት እየመሰሉ ሲያቃልሉት አያለሁ። የበቀደሙ የፖርላማው ንግግራቸው ግን አቧራው አይናቸውን የደፈነው ይመስላል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ትላንት የጸለዩልዎት የኢትዮጵያ እናቶች ዛሬ እያለቀሱብዎት ነው። አይንዎትን የጋረደዎትን አቧራና ዱቄት ይጥረጉ። አይንዎትን ይግለጡ፣ ከቀጣዮ እርምጃዎ በፊት እግርዎት ስር ያለውን ገደል ያስተውሉ። በታሪካዊ አጋጣም እጅዎት ላይ የወደቀችው ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ይዛ አብራዎት ጉርጓድ ውስጥ እንዳትሰነቀር ለማድረግ እድሉ ስላለዎት በጊዜ እንዲጠቀሙበት እግዚያብሄር ይርዳዎት።
Filed in: Amharic