>

የሻለቃው እብደት....!!! (አበበ ሀረገወይን)

የሻለቃው እብደት….!!!

አበበ ሀረገወይን

በደርግ ዘመን አብዮቱ ከፈነዳበት ጊዜ ብዙም ሳይቆይ ከጎጃም ለጉዳይ አዲስ አበባ መጥቼ ነበር። መንሥቱ ኃይለማሪያም 60ዎቹን ገሎ ባጠገቡ የነበሩትን ጄነራሎችና ኮሎኔሎች በየምክንያቱ ገሎ እፎይ እንዳይል ኢህአፓ “የከተማ ቴሮሪዝም” ወይም በደርግ አጠራር ነጭ ሽብር ግድያ እየተጧጧፈ ነበር። እኔም ባጋጣሚ ፒያሳ ከጓደኞቼ ጋር ራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብለን አንድ የፎቶግራፍ ሱቅ የሚያይ ሰው አንድ የሰሌን ባርኔጣ ያደረገ እድሜው 20 አካባቢ የሆነ ወጣት ሰውዬውን አንተ አቃጣሪ እያለ ፣ እባክህ ለልጆቼ ስትል ማረኝ ቢለው ደጋግሞ እየተሳደበ በጥይት በሳስቶ ገደለው። ነገር ግን እሱም ሊያመልጥ አልቻለም። ከየሱቁ ጠመንጃ ረሽና ሽጉጥ የያዙ ሰዎች ሲያሯሩጡት በድልድዩ አጠገብ ወደ ወንዙ ሊገባ ሲሞክር ከየአቅጣጫው በተከፈተ ተኩስ ተመቶ ወደ ወንዙ እየተንከባለለ ገባ።
ይህ በሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቡና ጠጥቼ ስናክ በልቼ እሄዳለሁ ብዬ መስቀል አደባባይ የሚገኘው ራንዴቩ ቁጭ ብዬ ስጠብቅ አደባባዩ ዙሪያ ብዙ የታጠቁ ወታደሮችና መትረየስ የጠመዱ ጂፖች አየሁ። አሁን አውቶቡስ የሚደረደርበት ቦታ ታች የሚታየው በብረት የተሰራ ሰገነት ነበር። ትንሽ ቆይቶ መንግሥቱ ኃይለማሪያም በብዙ መኪና ታጅቦ መጣ።  ወዲያው የቴሎቪዥን የሬዲዮ እንዲሁም በሌዎንቺና ጓዶች ተጭነው መጡ። ወታደሮች ራንዴቩ የተቀመጥነውን ክላሽ እየደገኑ ከዚህ ሂዱ አሉን። እኔ ከዚያ ተነስቼ አጠገቡ ወደሚገኝ የጉዞ ወኪል የሆነ የዘመዴ ቢሮ ገባሁ። ትንሽ ቆይቼ ጉዱን አያለሁ ብዬ ወደ አደባባዩ ከለል ብዬ የማይበት ቦታ ቆምኩ። ጓድ መንግሥቱ እንደተለመደው ማጓራት ጀምሯል።  እንደተለመደው ኢምፔርሪያልዝምን አሜሪካን ኢህአፖን ኢዲዩን ማውገዝ ጀመረ። ከኋላው እነ ኃይሌ ፊዳና ከአውሮፓ አብረዋቸው የመጡ የመኢሶን መስራቾች ተደርድረው ነበር። በጠርሙስ የተሞላውን የእንጨት ሳጥን አይቼው ነበር። ነገር ግን ደም ይሆን ቀይ ቀለም የተሞሉ ጠርሙሶች መሆኑን ያወኩት በኋላ ነው።  ከመጮህ ብዛት ድምጹ መሰባበር የጀመረው መንግሥቱ እጁን አፉ ላይ እያደረገ አልፎ አልፎ ይስል ነበር። ወዲያውም ሞት ለኢምፔሪያልዝም ፣ ሞት ላሜሪካ ፣ ሞት ለኢዲዩ ብሎ ጠርሙሶቹን ሲወረውር እየተፈረከሱ ቀዩ ወደ ሰማይ ይረጭ ነበር። የሚገርመው ግን የኢህአፓ ጠርሙስ ከወደቀ በኋላ ሳይሰበር ነጥሮ ጢብ ጢብ ብሎ ሳይሰበር ሜዳው ላይ ከብለል አለ። መንግሥቱም በንዴት አፉን ከፍቶ ቀረ። ከጓዶች አንዱ እየሮጠ ሄዶ ሜዳውን ያጥለቀለቀው ቀይ አንገዳግዶት ጠርሙሱን አንስቶ ለመንግሥቱ ሲያቀብለው ሞት ለኢህአፖ ብሎ ተንጠራርቶ ወርውሮ ከሰከሰው። በዚያን ጊዜ ይመስለኛል ቀይ ሽብር የታወጀው።
በአለም ታሪክ መንግሥቱ ኃይለማርያም የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ጠርሙስ ወርዋሪ መሪ ነው። በዚያን ዘመን የመኢሶን መስራቾች መንግሥቱን ለጊዜው ተጠቅመው ትንሽ ቆይተው ወደ ባራክ እንመልሰዋለን ብለው አስበው ነበር። ነገር ግን ጮንጯና አይኑ የሚርገበገበው መንግሥቱ በጎን ሌሎች ለረጅም ዘመን የሚያውቃቸውና የሚያምናቸው ለቤተ መንግሥትም ቅርብ የሆኑ አማካሪዎች ነበሩት። በነሱ ምክሽ መኢሶኖችን ለምሳ ሲያስቡት ቁርስ አደረጋቸው።  ለማንኛውም ችግር የመንግሥቱ መፍትሄ የተጠረጠሩት ሰብስቦ መረሸን ነበር። በየምክንያቱ አገራችን በብዙ ድካም ያፈራቻቸውን ምሁራንና ጄነራሎና የሰለጠኑ መኮንኖች ጨፍጭፎ እስካሁን ልንወጣ ያልቻልንበትን ድንቁርናና ግድያ አግራችን ላይ ተክሎና አዳብሮ የሄደ አረመኔ ነው።
እነዚህ አይኖቼ ስንቱን ጉድ አሳዩኝ። 
ፈጣሪ ሆይ እባክህ ደህና ቀን አሳየን።
Filed in: Amharic