>

በጦርነቱ ማን ድል አደረገ?  በቀጣዩ የወያኔ ዳግም ወረራስ ማን ድል ያደርጋል? (ፊልጶስ)

በጦርነቱ ማን ድል አደረገ?  በቀጣዩ የወያኔ ዳግም ወረራስ ማን ድል ያደርጋል?

 

ፊልጶስ


ቁስላችን ሳይደርቅ፣ እንባችን ሳንጠርግ፣ ነፍስ ይማር ሳንባባልና  ከተፈናቀልንበት ሳንመለስ፣ ”በድል ያጠናቀቅነው” ጦርነትም እንደቀጠለ ፤ እንደገና  ለሌላ ለባስ ጦርነት እየተደገስን መሆናችን ሳይ፤ “በ’ርግጥ በዚህ ጦርነት ድል ያደረገናያተርፈ አካል አለ እንዴ ?”  የሚል ጥያቄ አጫረብኝ።  እየተራበና እየታረዘ ከሚጋደል ህዝብ መሃል አትራፊና ድል አድራጌ ቢኖር እንጅ፤ ያለፈው እልቂት አልበቃ ብሎ፣ መሰአዋትነቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖና የጦርነቱ ዘዋሪዎች በነጻነት እየፏለሉ፤  ለሌላ  አዲስ  እልቂት ባለተዘጋጀን።  አዎ ! ድል ያደረግና ያተረፈማ አለ።  ሥልጣኑን ያደላደለ የመሰለውማ አለ።

ለ’ኔ  የኢትዮጵያ ህዝብ ተሸንፏል።  በተለይም የትግራይ፣ የአፋር፣ የጎንደር፣ የወሎና የሸዋ ህዝብ ተሸንፍል፣ ድል ተደርጓል።  ኦሮሙማው-ብልጽግና፣ ወያኔና ባለ ዳቦ ስሙ ኦነግ- ሸኔ ደግም አሸንፈዋል፤ አትርፈዋል፤ ድል አድርገዋል። እስቲ  ድል አድራጊዎቹን ተመልከቷቸው፤ ምን ጎደለባቸው?  የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሞ አስቡት?

ከባሮ -ቲዮብ የሰማውትና እኔም ካነብብኩት ሰርቢያኖች በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ርስ-በርስ የሚያደርጉትን ጦርነት፤   እንደሚከተለው ይገልጹታል ፤

”—-ጦርነቱ  በፓለቲከኞ ይጀመራል። ቱጃሮች ጥይት፣ ጠመንጃና ምግብ ያቀብላሉ። ድሆች ልጆቻቸውን ይሰጣሉ።

ጦርነቱ ሲጠናቀቅ፣ ከጦርነቱ የተረፈውን ጥይትና ጠመንጃ ፓለቲከኞቹ  ይሰበሰቡና ስልጣናቸውን ያጠናክሩበታል፤ ቱጃሮች  ለጦርነቱ ያዋጡትን ከህዝብ ካዝና ከነወለዱ ይወስዱና ሃብት በሃብት ይሆንሉ።ድሆች ግን ልጆቻቸውን  በየመቃብሩ  ሥፍራ እየፈለጉ እያነቡ ይኖራሉ።—–”

መቼም ”ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስም ቢሆን እንወርዳለን።”’ ብሎ በሰው ልጅ ላይ ተሰምቶና ታይቶ የማያውቅን  መከራ የሚፍጽም  ኃይልንና፤  ዜጋን በማንነቱ ብቻ  እንደ በግ  የሚያርድንና የሚያሳድድን   መዋጋትና  ማስወገድ  ከማንኛውም ፍጡር የሚጠበቅ ነው። ችግሩ ያለውና የህዝብ አሳዛኝ ታሪክ ”ሃ” ብሎ የሚጀምረው፤ የፓለቲካውን መመበር የያዙት ቡድኖች  እነዚህ እኩይ ኃይሎችን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ያለመፍለጋቸው ወይምጦርነቱን የሚመሩበትና የሚሰጡት ውሳኔ፤ የህዝብን መሰዋአትነት በዜሮ መባዛታቸው ነው። ከዚህም አልፎ ከህዝብ ተደብቆ የሚደረገው የጓሮ ድርድርና በየግዜው ስለ ጠላት የሚሰጠው  ውሳኔ ፣ደሃው ህዝብ  መሰዋአት እንዲከፍልከተደረገብት ዋና ምክንያት ውጭና፤ እንዲያውም  ለአገርና ለህዝብ ጠላት የበለጠ ኃይል የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱ ነው።

ሰሞኑን ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው ጦርነቱን  አስመልክቶ  ጀኒራል ተፈራ ማሞ ለፍትህ መጽሄት የሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ስለ ብአዴንም ሆነ ስለ ኦሮሙማ -ብልጽግና  ግንኙነት አዲስ ነገር ባይኖረውም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ከወያኔ ጋርድንበር የሚካለለው ህዝብ ፤ እንዳ አለፈው ግዜ መንግሥት ነኝ በሚለውን ኃይል አሳልፋ ሊሰጠው ስለሚችል ራሱን ማስታጠቅና መዘጋጀት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መራራ ሃቅ ነው።

የብአዴን  ነገር ”አለት ዘመኑን ሙሉ ውሃ ውስጥ ይኖራል፤ ነገር ግን መቸም ቢሆን ዋና አይማርም።” እንደሚባለ ነውና ፤ ብአዴን  ህዝብ እስከተሸከመው ድረስ በተላላኪነት፤ አድርግ ከተባለ  ኢትዮጵያን ለመሸጥ ከመደራደር ወደ ኋላየማየል የምድራችን ልዩ ፍጡር መሆኑን ማንም አይጠራጠርም። አሁን ከህዝብም ሆነ እንደ ጀኒራል ተፈራ ማሞ ካሉ ሰዎች መልስ የሚሻው ጥያቄ ”መፍትሄው”  ምንድነው  የሚለው ነው።

ወያኔ ለዳግም ወረራ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው። እንደምንሰማው   ወረራውን የሚያካሄደው በህዝብ ማዕበል ነው። ስለ ድርድርም አቋሙን በግልፅ አስቀምጧል። ወልቃይትና ራያን ማግኘት አለበት።  ታዲያ በዚህ መሃል መንግሥት ነኝየሚለውን አቋም ሆነ መርህ ማወቅ አልተቻለም፤ እንዲታወቅም አይፈለግም።

ገና በመካሄድ ላይ ባለው  ጦርነት ህዝብ  ልጆቹኑና ለዘመናት ያፈረውን ንብረቱን መስዋአትነት አድርጎ ያገኘው ነገር ቢኖር ፤ “እንደገና ትወረራለህ ወይም የተጋደልክለትን ወልቃይትንና ራያን ታጣለህ።”  የሚል አንድምታ ያለው ነው።

ለዚህ ደግሞ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እጅግ  ዓይን ባወጣና ምን ታመጣላችሁ በሚል ፤ በጦርነቱ ግንባር ቀደም ሆኖ መሰዋአት  የከፈለውንና የታደገውን ልዩ-ኃይል ማዳከምና ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት  ገዥዎቻችን ተቀዳሚ ተግባራቸውአድርገውታል። ምክንያቱም ይህን ካላደረጉ እንዳለፈው ጦርነት እነሱ “ድል ” ማድረግምና አትራፊ መሆን አይችሉምና።

ስለዚህም ህዝብም ሆነ ልዩ-ኃይሉና ፋኖ እያንዳንዷን ‘ርምጃ በጥንቃቄና በጥበብ ተናበው  መራመድ መቻል አለበቸው። ህግና -ስርዓትን ከምንግዜውም በበለጠ አክብረው ማስከበር የማንነታቸው መገለጫ መሆን መቻል አለበት።

እንደሚታወቀው ብአዴን የተላላኪነት ስራውን ከመስራት ወደ ኋላ አይልም። መንግሥት ነኝ የሚለው ኦሮሙማ-ብልፅግናም ብቻውን ያለ ብአዴን ምንም የሚያደርገው ነገር የለም።  ወያኔና ኦነግ- ሸኔ እስከ አሉ ድረስ  ከምንግዜውምበበለጠ መታጠቅና መደራጀት እንጅ ፤ ትጥቅ መፍታትም ሆነ ልዩ-ኃይሉ መዳከም እንደ ሌለበት በሚገባቸው ቋንቋ ለገዥዎቻችን መነገር መቻል አለበት።  ይህ የህልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቂ ግዜም የለምና።

እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ጀኒራል ተፈራ ማሞ ያሉ ሰዎች ምንም ይሁን ምን  በብእዴን ውስጥ ሆነው ቢሰሩ  ፤ ጠለው ከመውጣታቸው የበለጠ ውጤት ያመጣሉ ብየ አምናለሁና አሁንም ጀኒራሉ ተመልሰው ኃላፊነታቸውን የሚይዘበት  መንገድ ቢፈልግ መልካም ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ታላቋን አገራችን እያሰብን ፤  ከጎሰኝነት፣ ከመንደርተኝነና ከስሜታዊነት  ራሳችን አፅድተን እስከታገልን ድርስ፤  የሚከፍለው መስዋአትነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነታችን እስከ ሆነ ድረስ ህዝብ የድል ባለቤትየማይሆንበት ምክንያት የለም።  ለዚህ ቁልፍ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ  የፀና ዓላማና መርህ ያለው አቋም ይዞ መደራጅትና ፤ ህዝብንም በያለበት ራሱን እንዲከላከል ማደራጀትና ማንቃት የድል ባለቤት ያደርጋል።

ጠላቶቻችን ኢትዮጵያንና ህዝብን ከየአቅጣጨውና ከውስጥም ከውጭም የሚያጠቁበት ምክንያት፤  ሌላ ነገር ሳይሆን ለእኩይ ዓላማቸው የፀኑ፣ የተደራጁና ለመሰዋአትነት የተዘጋጁ መሆናቸው ነው። ታዲያ እኛ ለህልውናችን፣ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነታችን ከ’ነሱ የበለጠ መደራጀት፣ መፅናትና መስዋእት መሆን እንዴት አይጠበቅብንም?  ደግሞም እናደርገዋለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

E-mail: Philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic