ሸንቁጥ አየለ
አንተ ኦሮሞ ነህ: አንተ ትግሬ ነህ: አንተ አማራ ነህ: አንተ ከምባታ ነህ: አንተ ሲዳማ ነህ አንተ ደግሞ ከዚህ ወይ ከዚያ ብሄር ነህ በማለት ቀዳሚ ማንነትህ ብሄርህ እንጅ ኢትዮጵያዊነትህ አይደልም ስለዚህ የምትይዘዉ መታወቂያ ኢትዮጵያዊነት የተፋቀበት : የብሄር ማንነትህ የተለጠፈበት ነዉ ሲል በዘረኝነት: በአምባገነነትና በማንነት ቀዉስ ዉስጥ የገባዉ ወያኔ አወጀ::
የብሄር ማንነት ሰጠሁህ ተብሎ በግድ የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ የተጫነበት ህዝብ ግን ማንነትም : ሀገርም ብሎም መጻኢ እድልም የሌለዉ ሆነና ቁጭ አለ:: ኢትዮጵያዊነቱን ነጥቀዉ የጎሳ ማንነት ሰጠንህም ቢሉትም እዉነታዉ የጎሳ ማንነትም ሆነ ሀገራዊ ማንነት የሌለዉ ህዝብ እንዲሆን ተመቻችቶ ተቀመጠ::
ከ87 ብሄረሰቦች በላይ ያሉባት ኢትዮጵያ በሰባት ብሄረሰቦች ስም በክልል ተሸንሽና እንደ ቀልድ ከ80 በላይ የሚሆነዉ ብሄረሰብ ሀገርም: ክልልም ማንንነትም የሌለዉ ፍጡር ሆነ:: እንዴት ቢሉ ጋምቤላ ክልል የሚኖር አገዉ አገሩ ኢትዮጵያም ወይም ጋምቤላም አይደለም:: ኦሮሚያ ክልል የሚኖር አማራ ሀገሩ ኦሮሚያም ወይም ኢትዮጵያም አይደለም:: ደቡብ ክልል የሚኖር ጉራጌ ሀገሩ ኢትዮጵያም ደቡብም አይደለም:: እንዲህ እያለ ሲቆጠር ከኢትዮጵያዊነትም ከብሄር ክልሉም ተቆርጦ የተነጠለዉ ኢትዮጵያዊ እጅግ ብዙ ሆኖ ይገኛል::
ክልል በተባለዉ ዉስጥ ደግሞ መብት የለዉም:: የክልል ዜጋም አይደልም:: የሀገር ዜጋም አይደለም:: የሀገር ዜጋ ላለመሆኑ ማረጋገጫዉ በፈለጉ ሰዓት የክክል ባለቤት ነን የሚሉ ወንድሞቹ ገፍተዉ ያባርሩታ:: የክልል ባለቤት ላለመሆኑ ማረጋገጫዉ ደግሞ ከስሙ እስከ ህገመንግስታዊ መብቱ ብሎም ሰበአዊ መብቱ በዚያ ክልል ዉስጥ የተነፈገ ነዉ::
ክልል አለን የሚሉት አማራ : ኦሮሚያ : ሶማሊያ : አፋር ክልሎች ደግሞ ክልሉ ለለበጣ እና ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ በስማቸዉ ተለጠፈላቸዉ እንጅ በክልሉ ህግ ዉስጥ የሚያበጁት ወይም የሚፈጽሙት ጉዳይ የለም:: ህግ ያልሆነ ህግ እንደ ደራሽ ዉሃ ከወያኔ ምስለኔዎች ይፈስላቸዋል እንጅ::
ከዚህም የከፋና የከረፋዉ ነገር ደግሞ ትልልቅ ቁጥር ያላቸዉ ማህበረሰቦች መላዉ ኢትዮጵያን በታላቅ ክብርና ፍቅር መምራትና ኢትዮጵያዉያንን አንድ ማድረግ ሲችሉ በትንንሽ ክልል ስር ታስረዉ እጎሳ ከረጢት ዉስጥ እንዲከረቸሙ ተደረጉ:: አዕምሮአቸዉን ከኢትዮጵያዊነት በመነጠል እትንሽ ቋት ዉስጥ በመጨመር በመጨረሻም ኢትዮጵያዊነታቸዉን አዉልቀዉ ጎሳዊ ማንነታቸዉን እንዲለብሱ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ እንዲሁም ተቋማዊ ስራ ተሰራባቸዉ:: አብዝቶ የሚያሳዝነዉ ታዲያ ጎሳዊ ማንነታቸዉን ሊለብሱ ሲሞክሩ የየማህበረሰቡ ቁመት ከጎሳዊ ማንነቱ እጅግ የገዘፈና ትልቅ በመሆኑ የማንነት ቀዉስና የስነልቦና መዋለል ይስተዋል ጀመረ::
እናም መደምደሚያዉ ምን ሆነ?በመጨረሻም ህዝባችን ሀገር የሌለዉና ኢትዮጵያዊነቱን የተነጠቀ ሆነ ማለት ነዉ!
ይሄን እዉነታ በሚለተሉት የዜጎች የኑሮ ገጠመኝ እና ኩነቶች ዉስጥ ተመልከቱት::
ኩነት አንድ:-
————-
ሀጎስ ከሀይለስላሴ ጀምሮ ሀብት በጥረታቸዉ ካፈሩ ዜጎች የተገኘ ታታሪ ነጋዴ ነዉ:: ነዋሪነቱም አዉሮፓ ነዉ:: ኢትዮጵያ ሄዶ በመላ ሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋል:: ግን የሚፈራዉ ነገር አለ:: ትግሬ ስለሆንኩ ከወያኔ ጋር ተሞዳሙጄ ያፈራሁት ሀብት ስለሚመስላቸዉ በሌሎች ክልል ያሉ ኢትዮጵያዉያን ቀን ዘንበል ያለ እንደሆነ ሀብቴንም እኔንም ያጠፉኛል ብሎ ያስባል::
ኩነት ሁለት:-
—————
ሀያልሰዉ በትንሿ የሀረሪ ክልል ብዙ ሀብት አፍርቶ ነበር:: የሀረሪ ክልል ባለስልጣናት ሀረሪ የሚለዉን የቀልድ ክልል ብቻቸዉን እንድ ትንሽ ጀልባ ሊቆጣጠሩት አስበዋልና ሀረሪ ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያንን ሀብት እንዲሁም ንግድ ደጋግመዉ ሲያቃጥሉ ሀያልሰዉ ያፈራዉ ሀብት ሁሉ ደጋግሞ ስለወደመበት ካሁን ብኋላ የትኛዉም የኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ ንግድ ላለመስራት አስቦ ነበር:: አንዳንድ ሰዎች ግን አማራ ስለሆንክ አማራ ክልል ይሻልሃል ቢሉት አማራ ክልል የተሻለ ይሆናል ብሎ አማራ ክልል ኢንቨስት ያደረገዉ ሀብትም በሚገርም ፍጥነት አንዴ የቅሪት ፊዉዳል : አንዴ የኢሰፓ: አንዴ የመዓህድ ሌላ ጊዜ ደግሞ የቅንጅት አመለካከት አለዉ ተብሎ እንዲከስር ተደርጓል::
ኩነት ሶስት:-
————–
ደቻሳ ኢትዮጵያን ለመምራት የሚያስችለዉን የስነልቦና እና የእዉቀት ዝግጅት አድርጎ የጨረሰ ሰዉ ነበር:: ደቻሳ የሚያነሳቸዉ ዲሞክራሲያዊ አመለካከቶችን ግን ማንም ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ከምር አድርጎ ለመዉሰድ ሲቸገሩ ያስተዉላል:: “ምን ሆናችኋል?” ሲላቸዉ “ያዉ ዞረህ ዞረህ ኦሮሚያ ይገንጠል የምትል ይመስለናል” ይሉታል:: እሱም ይመልሳል:: “አማራ ክልል: ደቡብ ክልል እና ሶማሌ ክልል ዉስጥ ያለዉን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ የት ትቼ ነዉ የምገነጠለዉ:: ከዚያም በላይ ከብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን ጋር የተዋሃደዉን ዉህድ ኦሮሞ ለማን ትቼ ነዉ የምገነጠለዉ ? የኦሮሞ ማንነት ከኦሮሚያ የገዘፈ ነዉ::” ደቻሳ ለማስረዳት ይሞክራል:: ግን የሚያምነዉ የለም:: ወያኔ ኦሮሞዉን ጥሩ አድርጎ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ቆርጦታል::
ኩነት አራት:-
———-
ሰብሉ በደርግም በወያኔም ሰዎችን እየወነጀለ እና እያቃጠረ የሚኖር ሰዉ ነዉ:: ሰብሉ እምነት የለዉም:: ሰዉ አይወድም::ሌባ ነዉ:: በቀን ዉስጥ አስር አይነት ባህሪያትን ማሳዬት ይቻላል:: ባለስልጣን ሲያገኝ በፍጥነት መመሰልና መሆን ይችላል:: የዘር ሀረጉ የተመዘዘበትን ጎሳ አጠገቡ ካለዉ ባለስልጣን ጋር በፍጥነት የማመሳሰል ተሰጥዖው ልዩ ነዉ::ማንንም አይወድም:: ማንንም አያምንም:: የሰዉ ሀብት አጭበርብሮ እና ከባለስልጣናት ተሞዳሙዶ መንጠቅ ይችላል:: እግዜርንም ሆነ ሰይጣንን አይፈራም:: እግዜርም ሆነ ዲያቢሎስ አምላኩ አይደለም:: እግዜር መጥቶ ጌታህ ነኝ ቢለዉ ግን በፍጥነት እሽ ይላል:: እግዜር ዞር ሲል ዲያቢሎስ መጥቶ ጌታህ ነኝ ቢለዉም በፍጥነት ተገልብጦ እሽ ባሪያህ ነኝ ይላል::
በጣም ፈሪ ስለሆነ የማንንም አመለካከት መጋፋት እና እዉነት ነዉ ስለሚለዉ ነገር መቆም አያዉቅም:: ግን አድብቶ ማጥቃት ያዉቅበታል:: በተለይ ገንዘብ የሚያስገኝ ከሆነ ሁሉንም ተንኮሎች ማጠንጠን ይችላል:: ምላሱ ጤፍ ይቆላል:: እናም ይሄ ሰዉ በደርግም ጊዜ በወያኔም ጊዜ በሀገሪቱ ዉስጥ ሀብታም ሆኖ የቀጠለ ነዉ::
ኩነት አምስት:-
—————-
በወጣት ስሜት የተሞሉት መሃመድ: ንጹህ: አሊ: ግዞ: ሰማኝ: ደበላ: ምህረት እና አበራ ሆነዉ “አሃመነስ ቴክኖ ግሩ” የሚል ኢትዮጵያን መሰረት አድርጎ መላዉ አፍሪካ የሚያዳርስ ቴክኖሎጅ ፈጠራ እና ንግድ ላይ የሚሰራ ድርጅት መስረትዉ ነበር:: የድርጅታቸዉን ስም አሃመነስ ያሉትም ከክርስቶስ ልደተ አለም በፊት በ1900 ዓመተ አለም (ዓ.ዓ) አሃመነስ የተባለ ኢትዮጵያዊ የጠፈር ተመራማሪ በህዋ ዉስጥ 16 ፕላኔቶች አሉ ሲል የደረሰበትን የምርምር ምጥቀት ለማስታወስ እንዲሁም የባለዐእምሮ ህዝብ መሰረት ላይ የቆሙ ወጣት መሆናቸዉን እና እነሱም ለትዉልዳችዉ የሚያበረክቱት ነገር እንዳላቸዉ ለማጠዬቅ አስበዉ ነበር::
ሆኖም የሚያገኙት የወያኔ ባለስልጣን ሁሉ የሚጠይቃቸዉ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቁጭ ብለዉ በጋራ እንዲያነቡ አድርጓቸዋል:: “ብሄራችሁ ምንድን ነዉ? የሱ ብሄርስ ? የእርሷ ብሄርስ? ከጀርባችሁ ማን ነዉ ያለዉ? የአማራ የነፍጠኛ እና ትምክህተኛ ስሜት እመሃላችሁ አለ? የኦሮሞ የጠባብነት ስሜት እመሃላችሁ አለ? የጉራጌ አድርባይ ሀይል እናንተ መሃል አለ? የእስላም አክራሪነት ስሜት ያለዉ ሰዉ እመሃላችሁ አለ ?” ጥያቄዉ ማለቂያ የለዉም::
የመላዉ አለም ወጣቶች በዚህ የቴክኖሎጅ ዘመን ስለ ቴክኖሎጅ ምርምር : ስለህዋ ምጥቀት: ስለ ታላላቅ ፈጠራዎች በጋራ ይሰራሉ:: አዕምሯቸዉን አስፍተዉም ይጨነቃሉ:: እንኳን በአንድ ሀገር ዉስጥ ያሉ ዜጎች በመላዉ አለም ያሉ ዜጎች ስለጋራ ቢዝነስ ይጠበባሉ:: ስለጋራ ፈጠራ እና ስለጋራ ታላላቅ የአለም ንግዶች ተባብረዉ ይሰራሉ::
የኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ግን ወያኔ በቀዬሰዉ የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ታንቀዉ ገና ወደ ድንጋይ ዘመን ይንሸራተታሉ:: “እከሌ ጎሳ ቡዳ ነዉ:: እከሌ ጎሳ ከብት ነዉ:: እከሌ ጎሳ ካንሰር ነው:: እከሌ ጎሳ ሰዉ አይደለም::እከሌ ጎሳ ዝንጆሮ ነዉ:: እከሌ ጎሳ ከምድረ ገጽ መጥፋት አለበት::” ሲባባሉ እና ሲተቻቹ ሲሰዳደቡ ይዉላሉ::
ኢትዮጵያ በአለም ላይ ካሉ ሀገሮች ብዙ ሰፊ የሚባል የቆዳ ስፋት የላትም:: ቢሆንም ቀላል የሚባልም አይደለም:: በህዝብ ቁጥር ከአለም ሀገራት 13ኛ ደረጃ አላት:: በኢኮኖሚ ህዝቧ ገና ሌት ከቀን መስራት እና ወደፊት መራመድ አለበት:: ህዝቡ ብዙ ዉህድ ነገሮች ያሉት ዉህድ ህዝብ ነዉ::የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ግን ታላቅ ገበያ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ዉህድ ማህበረሰብ አብሮ እንዳይኖር እና አብሮ የኢኮኖሚ ግስጋሴ እንዳያደርግ ሁሉንም ነገር ተረት ተረት አድርጎታል:: ዛሬ ስለኢትዮጵያ ህዝብ ዉህድነት መናገር ልክ ተረት ተረት እንደ መተረክ ይቆጠራል::
ስለ ጋራ ብልጽግና ሳይሆን ስለ እርስ በእርስ መጠፋፋት ወጣቱ ሌት ከቀን እንዲያልም የጥላቻ ቋንቋዎች በስፋት ተዘርተዋል:: ዲሞክራሲያዊ የሀሳብ ልዉዉጥ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች መሃከል የሚታሰብ አይደለም:: ስለብልጽግና መነጋገር ተረት ተረት ነዉ:: ስለ ጋራ ቢዝነስና ታላላቅ ፈጠራዎች ማዉራት ተራ እና ከንቱ ነገር ኢንዲሆን ተደርጓል::
በኢትዮጵያዉያን ወጣቶች መሃከል ሀገራዊ አጀንዳ እንዲጠፋ ወያኔ ሁሉንም ወጥመዶች አጥምዳ ጨርሳለች:: በወያኔ የጎሳ ፖለቲካ የተነሳ የኢትዮጵያዉያን ወጣቶች በድንጋይ ዘመን እንዲኖሩ ታላላቅ አዕምሮ ፈሶበት የተፈጠረዉ ማህበራዊ ሚዲያ እና ልዩ ልዩ ለሰዉ ልጅ ብልጽግና የሚዉል የሚዲያ ቴክኖሎጅ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦችን ማጠላሊያ : ማራራቂያና ማጠፋፊያ እንዲሆን ሆኗል:: ኢትዮጵያም የማንም ያልሆነች ሀገር እንድትሆን ተደርጓል::ኢትዮጵያም የኔ የሚላት ዜጋ የላት::ዜጎቿም ሀገር የላቸዉም:: ከሁሉም የከፋዉ ደግሞ የነገ የጋራ ተስፋቸዉን ሁሉ ተነጥቀዋል::
በጎሳ ፖለቲካ ህሳቤ መሰረት ኢትዮጵያዊነት በቂ አይደለም:: እንዲያዉም ምንም ዋጋ የለዉም:: ወጣቶቹን የወያኔ ባለስልጣናት ሊገመግሟቸው እና ዉጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት የሚያስቀምጡላቸዉ ብሄራቸዉን : ሀይማኖታቸዉ እና አመለካከታቸዉን እየለኩ ነዉ::በጎሳ ፖለቲካ ዉስጥ ሰዉነት ከጎሳ ማንነት ያነሰ ነዉ:: ኢትዮጵያዊነትም ከቀበሌ ማንነት እጅግ ዝቅ ያለ ነዉ::
እናም በመጨረሻ “አሃመነስ ቴክኖ ግሩ” የመሰረቱትም ወጣቶችም: ሀጎስም : ሀያልሰዉም: ደቻሳም ለየብቻ ቁጭ ብለዉ ይቆዝማሉ:: ስለክልል ሲያስቡ ክልል የላቸዉም::ስለማንነታቸዉ ሲያስቡ እዉነተኛ ማንነታቸዉ ከጎሳ ማንነታቸዉ በላይ ነዉ:: ማንነታቸዉን በሀገራቸዉ ልክ እንዳያደርጉት ደግሞ ስለ ሀገር ሲያስቡ ሀገር የላቸዉም:: እነሱም ሊሞቱላት የሚያስቡት እንዲሁም የሚኮሩባት ሀገር እንደሌላቸዉ አምነዉ ኢትዮጵያ የሚለዉን ቃል ገፍተዉታል:: ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰርቶ የመለወጥ ተስፋቸዉ ተሟጧልና የሆነ ሌላ ሀገር በመሄድ በሌላ ሀገር ዉስጥ ጠንክረዉ ሰርተዉ ሀብታም ስለመሆን እያንሰላሰሉ ነዉ:: በደምሳሳዉ ሲታሰብ ሀገር የሌለዉ ህዝብ : ኢትዮጵያዊነቱን የተነጠቀ ህዝብ ምንም ነገር ቢያስብ ወይም ተስፋ በልቡ ባይቋጥር የሚደንቅም ላይሆን ይችላል::
ሀገር የሌለዉና ኢትዮጵያዊነቱን የተነጠቀ ህዝብ ከመሆንም የከፋዉ መጻኢ ራዕይዉ የተነጠቀ ህዝብ መሆን ነዉና የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም የጋራ ራዕይ የሌለዉ ድንግዝግዝ ጨለማ ዉስጥ የገባ ህዝብ ሆኖ በወንዝና በጎሳ ማንነት ቀለበት ዉስጥ ገብቶ የሚዳክር በእርስ በእርስ ጥላቻ መሰረት ላይ ተደላድሎ እንዲቆም ተደርጓል:: ሀገር የሌለዉና ኢትዮጵያዊነቱን የተነጠቀ ህዝብ ከመሆንም የከፋዉ የጋራ መጻኢ ራዕይ የሌለዉ ህዝብ መሆን ነዉ !
እናም እድገትና ብልጽግና ሰላም እንዲሁም የሁሉ ወገን ፍቅር የናፈቃቸዉ ሰዉ ናቸዉና በዬልባቸዉ ያነባሉ:: አንድኛቸዉም ግን ኢትዮጵያዊነትን ነጥቆ ሀገር አልባ ያደረጋቸዉን ነገር ምን እንደሆነ ደፍረዉ ተነጋግረዉ አያዉቁም:: በዉስጣቸዉ ግን ያዉቁታል:: የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ህዝባችንን ኢትዮጵያዊነቱን ነጥቆ እንዴት ሀገር አልባ እንዳደረገዉ ገብቷቸዋል::
እዉቀታቸዉ ግን ግማሽ ነዉ:: አሁን የገጠማቸዉ እዉነታ እንዲለወጥ ይፈልጋሉ እንጅ ይሄን ሁኔታ ሊለዉጡ የሚፈልጉትን ወገኖች ደግሞ ሲነቅፉ ይገኛሉ::ይባስ ብለዉም ህዝቡ በተገቢዉ መልክ ስላልደገፋቸዉ በቀጨጨና በመነመነ መሰረት ላይ የቆሙትን ተቃዋሚዎች እንዲህ አላደረጉ እንዲያ አላደረጉ እያሉ ሲተቹና ሲያንቋሽሹ ይዉላሉ:: በለዉጡ ሂደቱ ዉስጥ የኛ ሚና ምን ይሁን ብለዉ ግን ጠይቀዉ አያዉቁም:: ወይም አንድም ቀን ተቃዋሚዎች ምን ሊደገፉ ይገባል ሲሉ ጠይቀዉ አያዉቁም:: የትኛዉ ተቃዋሚ ነዉ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ሊያወጣት የሚችለዉ የሚለዉን ጥያቄ አንስተዉ አያዉቁም:: ተቃዋሚዎች በራዕይ : በጉልበት: በተቋማዊ አወቃቀር እና በሌሎች ነገሮች ሁሉ ለምን አቅመቢስ እንደሆኑም አስበዉም አያዉቁም::
አንድ ነገር እንዲለዉጥ ከፈለግህ ማወቅ ብቻዉን በቂ አይደለም:: ለለዉጡ መሳካት ተነስተህ መስራት አለብህ::ሌሎች እንዲህ አላደረጉ ወይም እንዲያ አላደረጉ እያሉ ማንንም መክሰስና መዉቀስ አይቻልም::
ሀገር ያለዉ ህዝብ ለመሆን ኢትዮጵያዊነትም ከስብርባሪ የወንዝ ማንነቶች በላይ ገዝፎና እሚያስከብር ማንነት እንዲሆን ብሎም ለዜጎች ሁሉ የሚመች እንዲሆን ለማድረግ በእያንዳንዱ ዜጋ መከፈል ያለበት ዋጋ አለ:: እያንዳንዱ ዜጋ ይሄን ዋጋ እስካልከፈለ ድረስ የግለሰቦች ትግል እና ጥረት ምንም የሚያመጣዉ መሰረታዊ ለዉጥ የለም:: ብዙዉ ኢትዮጵያዊ ይሄን ሀቅ አላምጦ እስቂዉጠዉ ብሎም ለተግባራዊ ለዉጥ እስኪነሳ ድረስ ኢትዮጵያዊነት ወደ ከፍታ ማማ ላይ ወጥቶ ለማዬት መናፈቅ ብቻ ወደ ተፈለገዉ ግብ የሚያደርስ አይሆንም::
የሆነ ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊነትን ወደ ከፍታ ማማ ላይ ለማዉጣት ከመስራት የተሻለ የመጻኢ ጊዜ አማራጭ የሌለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን የፈጠጠ እዉነት የሚያስተዉልበት ጊዜ ብሎም ለተግባራዊ ለዉጥ በጋራ የሚነሳበት ወቅት እሩቅ እንደማይሆን እሙን ነዉ::