>

ምክር!!!  ምክር ለማትሰሙ ፖለቲከኞቻችን...!!! የሕዝብን ለሕዝቡ ተውለት! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ምክር!!! 

ምክር ለማትሰሙ ፖለቲከኞቻችን…!!! የሕዝብን ለሕዝቡ ተውለት!
ያሬድ ሀይለማርያም

እባካችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ብዙ ብዙ በእናንተ ክፋት እና ክሽፈት የተከፋበት ነገር ስላለ ቢያንስ ቅድመ አያቶቹ የተውለትን እና መጽናኛዎቹን የሆኑትን ታሪካዊ ትውፊቶች፣ ሃይማኖታዊ እሴቶቹን እና ያስተሳሰሩትን ባህሎቹን ለሱ፣ ለራሱ ለሕዝቡ ተውለት።
– እንደ እናንተ ክፉት ቢሆን ኢትዮጵያ የዛሬ አስርት አመታት ወደ ትናንሽ አገሮች ተቀይራ ነበር፣
– እንደ እናንት የጨነገፈ አስተሳሰብ ቢሆን ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ በጏይማኖት እና በብሔር ተቧድነን በተላለቅን እና እሩዋንዳን የሚያስንቅ የዘር ጭፍጨፋ ባስተናገድን ነበር፣
– አዎ እንደ እናንተ ክሽፈት ቢሆን ኢትዮጵያ ከእነ ሶማሌ እና አፍጋኒስታን ተርታ የትርምስ እና የሽብርተኞች ቀጠና ሆና በየቀኑ የአጥፍቶ ጠፊዎች የውድመት ዜናዎችን ባስተናገደች ነበር።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከዚህ ሁሉ የፖለቲከኞች ክሽፈት፣ ጭንጋፍ አስተሳሰብ እና ጥቃት ጠብቀው ያቆዩን እና ያስተሳሰሩን እድሜ ጠገብ ባህሎቻችን፣ አለምን ያስደመሙ ታሪኮቻችን እና ጏይማኖታዊ ትውፊቶቻችን ናቸው። እነዚህን የቀሩንን እና ያስተሳሰሩን እሴቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃቶቻችሁን አቁሙ።
እባካችሁ ታሪኩን ለሕዝቡ ተውለት፣
እባካቸው በጏይማኖቱ ጣልቃ አትግቡበት፣
እባካችሁ ባህሉን አትንኩበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔር ፖለቲካ የሰከሩ እና በጨነገፉ እሳቤዎቻቸው ከሚያሰቃዩት ፖለቲከኞች ጥቃትና ፍላጻ የተረፈው በሚጋራው ታሪኩ፣ ሁሉ አቀፍ በሆኑት ጏይማኖቶቹ እና ባህላዊ ትውፊቶቹ ነው እንጂ በእናንተ ቸርነት አይደለም።
እባካችሁ መጽናኛዎቹን አትንኩበት፣
እባካችሁ ከሕዝብ ጋር እልህ አትጋቡ፣
እባካችሁ ከታሪኩ፣ ከሀይማኖቱ እና ከባህሉ ላይ እጃችሁን አንሱ፣
እባካችሁ መስቀልን፣ ጥምቀትን፣ ኢሬቻን፣ ጨምበለላን፣ አድዋን እና ሌሎች ሕዝባዊ በዓላትን የፖለቲካ መቆመሪያ አታድርጓቸው።
የቄሳርን ለቄሳር፤ የእግዚአብሔርን ለእዝጌሩ አንዲሉ የሕዝብን ለሕዝብ ተውለት።
Filed in: Amharic