>

የእግዚአብሔርን ትድግና የምንፈልግ ከሆነ ከሰፈራችን ‹‹ጌልገላ›› እንውጣ ! (ከይኄይስ እውነቱ)

የእግዚአብሔርን ትድግና የምንፈልግ ከሆነ ከሰፈራችን ‹‹ጌልገላ›› እንውጣ!

 

ከይኄይስ እውነቱ


በርእሰ መጻሕፍቱ – መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ – ተመዝግቦ ከምናገኘው አስደናቂ ታሪክ አንዱ የገባዖን ጦርነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእሥራኤል የተዋጋበት፤ በኢያሱ ልመና በእግዚአብሔር ፈቃድ ጠላቶቻቸውን እስኪያጠፉ ድረስ በገባዖን ምድር ፀሐይ ከመግባት አንድ ቀን ሙሉ የቆመበት፣ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ ከመውጣት የዘገየበት፤ ‹‹እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም›› የተባለበት ታሪክ፡፡ 

ኢያሱ ጠላቶቹን በማጥፋትና በመቆጣጠር፣ ኃያላን ከነበሩት የገባዖን ሰዎችም ጋር ሰላም ማድረጉን ሲሰማ አዶኒ ጼዴቅ የተባለው የኢየሩሳሌም ንጉሥ 5ቱን የአሞራውያንን ነገሥታት አስተባብሮ ከገባዖን ጋር ጦርነት ሊገጥሙ ከበቡአት፡፡ በዚህን ጊዜ የተከሰተውን መጽሐፉ እንዲህ ይገልጸዋል፤‹‹የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው፡- ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ አድነንም እርዳንም አሉት፡፡ ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ፡፡ እግዚአብሔርም ኢያሱን፡- በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው የሚቋቋምህ የለም አለው፡፡ ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው፡፡ እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው፤… እግዚአብሔር ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ፡፡›› ኢያ. 10÷1-11፡፡ 

እኛም ኢትዮጵያውያን ላለፉት 5ት ዐሥርታት በተለይም ባለፉት 31 የግፍ ዓመታት የከበቡንን ‹‹አሞራውያንን›› (የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት ያቆሙብንን ኢሕአዴጋውያንን፤ በተለይም ወያኔ እና ኦሕዴድ-ኦነጋውያንን) እንዲሁም በዘረኝነት በሽታ የተለከፉ የክፋት ኃይላትን እግዚአብሔር እንዲዋጋልን ከፈለግን ኃያል ክንዱን ተማምነን፤ 

 • ከምንርመጠመጥበት የአትድረሱብኝ ‹ክልል›፤ 
 • የዘረኝነት ሰፈር፤ 
 • የጐሠኝነት መንደር፤
 • የተረኝነት ጎጥ፤ 
 • የጠባብነት ቀዬ፤ 
 • የከፋፋይነትና የመለያየት ሰርጥ፤ 
 • የጥላቻና የድንቊርና ዋሻ፤ 
 • የአረመኔነትና የጭራቅነት ጎሬ፤ 
 • የስግብግብነትና ሁሉን ለኔ ብቻ ከሚል ደሴት፤ 
 • ከዝርፊያና ውንብድና ምድረ በዳ፤ 
 • ከሐሰትና ቅጥፈት ሸለቆ፤

ነቅለን ወጥተን ለሰልፍ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ትንሽ እምነት ካለን ከኢያሱ መስፍን ጋር የነበር እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ ኢትዮጵያን ከጠላ፣ ሕዝቧን ከናቀ ዲያቢሎሳዊ ኃይል ጋር በንግግር የሚፈታ ችግር አለ ብሎ ማሰብ ነፋስ መጐሰም ጉም መዝገን ይሆናል፡፡ በወያኔ ትግሬ ላገር ህልውና ብለን ስንቴ ተታለልን፣ የሱ ውላጅ የሆኑት ተረኞቹ ኦሕዴዶችስ በዚህ አራት ዓመት ውስጥ ዐውቀን እየታለልን ከ27 ዓመቱ የበለጠ ጥፋት አልተፈጸመም? ለመሆኑ ከዘረኛው ዐቢይና ተላላኪዎቹ ማጭበርበሪያዎች ያልመከነው የትኛው ነው? ከቡራዩ ፍጅት ጀምሮ እስከ ወይብላ ማርያም የተፈጸመውንና አሁንም ያላቋረጠውን ጭፍጨፋ ለማጣራት የተቋቋሙና በውሸት ቃል ተገብቶ ያልተቋቋሙ ኮሚሽኖች፣ የወሰን ኮሚሽን፤ የዕርቅ ኮሚሽን ወዘተ. የት ደረሱ? ገዳዩም ላጣራ ባዩም፤ አፈናቃዩም ዕርዳታ ልሰብስብ ባዩም፤ ሽብርተኛውም ሽብርተኛ ብሎ ፈራጁም፤ አገር አፍራሹም ‹የምክክር ኮሚሽን› አቋቁሜዬ አገር አድናለሁ ባዩም፤ ተከሳሹም ዳኛውም ራሱ ኦነጋዊው አገዛዝ በሆነበት ስለ ንግግር ማሰብ ይቻላል? የአገዛዙን ባሕርይ ዐላወቅኹም የሚል ለመንደቆር የመረጠ በመሆኑ ምርጫውን ከማክበር ውጭ ምን እናደርጋለን፡፡ በጨውነት ለመነጋገር በቅድሚያ ወደ ሰውነት ከፍ ማለትን ይጠይቃል፡፡ 

ዘረኞቹ አንድ ባንድ አገራዊ እሤቶቻችንን ሸርሽረው ከጨረሱ በኋላ ስለ አገር ህልውና፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ ወዘተ. ብናወራ ትርጕም አይኖረውም፡፡ ከ27ቱ የወያኔ ትግሬ ዘመን በከፋም አሁን የለየለት ዕብደትና ድንቊርና የነገሠበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በተቀደሰች ምድራችን ላይ የተዘራውን የክፋት፣ የተንኮል፣ የቂም በቀል፣ የመሠሪነት ሴራና ሽረባ ባጠቃላይ ማኅደረ አጋንንት በመሆን ከጥፋታቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ አፅራረ ኢትዮጵያን ለመግጠም ሰልፍ መውጣት አለብን፡፡ ኢያሱ፤ እግዚአብሔር የተዋጋለት በቅድሚያ የራሱን ሠራዊት ይዞ ሰልፍ እንደታዘዘው ከ‹‹ጌልገላ›› ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከዘረኞች ለማዳን የምንፈልግ ኢትዮጵያውያንም ኢያሱን አብነት አድርገን ሰልፍ እንውጣ፡፡ ለኢትዮጵያውያን የብሔራዊ በዓላት ሁሉ በኵር የሆነውን በዓላችንን – ዓድዋን – ግንባር ቀደም ጀግኖቻችንን እምየ ምንይልክን እና ብርሃን ዘኢትዮጵያ ጣይቱን ከፍ ከፍ አድርገን ያከበርነው እኮ በአገዛዙ ፈቃድ አይደለም፡፡ ጨክነን ባንድነት ኢትዮጵያን ብለን በመውጣታችን እንጂ፡፡ ወገኔ! እኛ ለበጎ ስንነሣ የመለኮት ጣልቃ ገብነት እንደማይለየን ማመን ያስፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ውስጥ ሱታፌ እንዳለን አንዘንጋ፡፡ እርሱ ከስንፍናና ሰነፎች ጋር ኅብረት የለውምና፡፡ 

ስለሆነም ከዘረኝነትና ከመሳሰለው የርኵሰት መንደር ወጥተን ወደ ሰፊውና ወደ ተንጣለለው ሀገረ- ኢትዮጵያ ወደተባለው ሜዳ እንውጣ፡፡ ኢየሱ ከጌልገላ ወደ ገባዖን ምድር እንደወጣ ሁሉ፡፡ በዚህች ኢትዮጵያ በተባለች የለመለመች መስክ ነገዳችንን፣ ጐሣችንን፣ እምነታችንን፣ ባህላችንን፣ ልዩነታችንን ይዘን ባንድ የኢትዮጵያ ሕዝብነት በአብሮነት የምንሰማራበት ከበቂ በላይ ቦታ አለ፡፡ ከተደማመጥን፣ ‹ሰው› መሆን ከቻልን፣ እንደ ባለአእምሮ አስበን ሁላችን እንደየ ሙያችንና ችሎታችን በርትተን ከሠራን፣ ፈጣሪ የሰጠንን ሀብት ባግባቡ መጠቀም ከቻልን፣ እንደ ቀድሞው መተሳሰቡ መተዛዘኑ ካለ አገራችንን የተድላ ደስታ ምድር ለማድረግ እንችላለን፡፡ ወደ ቀደመ ክብሯ፣ ልዕልናዋና ገናናነቷ መመለስ እንችላለን፡፡ አምላከ ኢትዮጵያ ይርዳን፡፡

Filed in: Amharic