>

የቡዳ መድኃኒቱ እስክንድር ነጋ...!‼ (ዘመድኩን በቀለ)

የቡዳ መድኃኒቱ እስክንድር ነጋ…!

ዘመድኩን በቀለ

“…ይብላኝ ለእኔና ለአንተ እንጂ እስክንድርማ (ከነ ጓዶቹ) የማይቁሙትን በጎ ዕድል የመረጠ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው። ካቻምና ኮንዶሚንየምህን እየቀሙህ፣ እየወረሱት ነው ብሎ ሲጮህልህ፣ አምናም ተረኝነቱ ለከት አጥቷል ብሎ ድምጹን ሲያሰማልህ አንተ እሱን እንደማገዝ ካንተው ብሶ ሥርሥሩ እየተንቶሶቶስክ እንደ አበደ ውሻ እግር እግሩን እያየየህ ትጮሃለህ። የሚያሳብድህን ጨርቅህን አስጥሎ ብቻህን እያወራህ እንድትሄድ እያደረገህ ያለውን መንግሥት ትተህ አንተ እስክንድርን ዕብድ ነው ትለዋለህ። ያበድከውስ አንተ።
“…አንተ ነካ ያደርገዋል የምትለው እስክንድር እኮ እኔ እና አንተ ከፎሊስ እይታ ውጪ እንኳ ይዘን ለመታየት የምንሰቀቀውን ሰንደቅ ዓላማ አልተውውም፣ አልጥለውም ብሎ እኮነው የማንም መንገደኛ እንደ መንደሩ ለማዳ ከብት አስሬ የሚያስር የሚፈታው። ብዕር ይዞ ከሚሳኤል በላይ የሚፈራው እስክንድር ዕብድ አይደለም። አንተ ዲቪ ሞልተህ፣ ስዕለት ተስለህ ለመሄድ በጦም በጸሎት ኔትወርክ የምታጣብበትን አሜሪካ ንቆ ከአንተ ጋር መከራህን ልቋደስ ብሎ የወሰነ ጀግና እኮ ነው።
“…እስክንድር ማለት ሞትን የተጸየፈ፣ የፍርሃት ጠባዩ የጠፋለት፣ ስሙ ከግብሩ የሰመረለት የተለየም ዕደለኛም የሆነ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው። ያመነበትን ነገር እስከጥግ ድረስ ሄዶ ለማስፈጸም የማይሰቀቅ፣ የማይደክመው፣ የማይሰለቸው፣ ሼም የጠፋለት ጀግናም ነው። መንግሥት ተብዬው “ሰንደቅ ዓላማን አትያዝ” ነው የሚለው። እርሱ ደግሞ አይደለም መያዝ ባጌጥበትስ፣ ብደምቅበትስ ምን ያገባሃል ነው የሚለው። ታዲያ ዕብዱ ማነው? መንግሥት ተብዬው ወይስ እስክንድር? …አንተ ደግሞ ከዳር ቆመህ “…ምንአለበት እስክንድር ለሰላም ሲል ሰንደቅ ዓላማውን ለዛሬ እንኳ ቢተወው፣ እንደው የሚመክረው ሰው ይጥፋ? ምንአለ ተረኝነትን ባይቃወም። ምንአለበት የከፈልንበትን ኮንዶሚንየም ሌላ ያልደከመበት ተረኛ ሲወስደው እያየ ባይቃወም። ምንአለበት ስደተኞችን ለህዝብ ባያሳይ፣ ምንአለበት በዚህ ጊዜ መንግሥትን ባይከስ፣ ባያሳጣ እያልክ የሚዘገንን አስተያየት እየሰጠህ ትንበጫበጫለህ። በጭባጫ… አልጫ ሁላ። አርፈህ ብቻህን መፍራት መንቦቅቦቅ እየቻልክ የአንተን ሽንታምነት ሌላው ላይ ለማጋባት ትላላጣለህ። ዛሬ ጠባዬን ላሳምር ብለህ ከጽንፈኛው ጋር ተመሳስለህ ለመኖር ስትል የጣልከውን ሰንደቅ ዓላማህን ነገ የሚያነሣልህ ያዘው ከፍ አድርገህም ስቀለው የሚልህ ታገኝ መስሎሃል። “ዱቤ ከፈለጉ ነገ ይምጡ” እንዲል ሸምሱ ባለ ሱቁ… እህም… ነገም እኮ ይብሳል እንጂ የሚቀንስ ነገር የለም። እንዲያውም በዓድዋ በዓል ላይ የተሳተፈን የአዲስ አበባን ወጣት በሙሉ በዕለቱ የፌደራል ፖሊስ ሲቀርጸው ስለዋለ ሰሞኑን አፈሳ ጠብቅ። ዛሬ ይሄን በተባበረ ክንድ ካላስቆምከው እስሩም እንደ ዘይት ዋጋ ጣራ እየነካ ነው የሚሄደው። ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እኮ ለምን የዓደዋን በዓል አከበርክ ተብሎ ነው ያ ሁሉ ተማሪ ሲወገር የከረመው።
“…እስክንድር እኮ ሥራው ነው። ፖለቲካ ማለት የእስክንድር የሙሉ ጊዜ፣ የሙሉ ሰዓት ሥራው ነው። አንተ ጋዜጣና ፌስቡክ እያነበብክ የምትቀደድበትን ፖለቲካ እስክንድር በህይወት ኖሮበት ነው የሚያውቀው። ምን ማድረግ፣ ምን አለማድረግ እንዳለበትም ጠንቅቆ የሚያውቅ ልምድ ያለው ፖለቲከኛም ነው። ብዙዎች የወደቁበትን የተነሡበትንም ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ እንዳንተ አይነቱ ጃምቧም ይሄን ባያደርግ፣ ያንን ባይሠራ የምትለው ሰው አይደለም። እስክንድርን ካልመከርኩ የምትለው አንተ ቦቅቧቃው እኮ ነህ። እስክንድር ምን እየሠራ እንደሆነ አሳምሮ የሚያውቅ የነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊ ምን እንዳደረገው አስታውስ። የኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የዐብይ ሽመልስ መንግሥት፣ አቃጣሪና ገሌው ኢዜማ ናቸው አሳምረው የሚያውቁት። በኢትዮጵያ ውስጥ በተጠና ሁኔታ የገዢዎችን ነርቫቸውን የሚበጥስ ድርጊት የሚፈጽም የሚያንጨረጭራቸው ነፍስ ያለው ፖለቲከኛ ጥራ ካልከኝ አንድ እስክንድር ነጋን ብቻ ነው የምጠራልህ።
“…እስክንድር በቲዊተር ገፁላይ “ኃይል የእግዚአብሔር ነው” ብሎ ሰለጻፈ ብቻ የሚንበጫበጨውን አይተህ ሰውየው እንዴት ያለ የፖለቲከኞች የቡዳ መድኃኒት ባለ ከባድ ሚዛን ታጋይ እንደሆነ ትረዳለህ። እስክንድርን የምትንቀው አንተ ብቻ ነህ። ዕብድ ነው፣ ያመዋል የምትለው አንተው በዘይትና በቤት ኪራይ ወጪ የቀወስክ ጧ ያልከው ቀዌው ብቻ ነህ። እስክንድርን አንተ እንደምትለው እነርሱ አይሉትም። አያላግጡበትምም። አይንቁትምም። ኦነግ፣ ህወሓት፣ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ ኢቲቪና ኢሳት እኩል የሚሰድቡት፣ የሚቃወሙት ሰው አምጣ ካልከኝ እስክንድር ነጋ ብቻ ነው። እነሱስ እሺ ነርቫቸውን ስለሚነካው ነው የሚገርመው የአንተ ከእነሱ እኩል እስክንድር ላይ ማቀርሸት ነው። ደግሞም እኮ እስክንድር ለማላገጥ ፖለቲካው ውስጥ አልገባም። ሥራውን በታማኝነት እየሠራ ያለ ፖለቲከኛ ነው። የህዝብ ድምጽ ከመሆን በላይ ሌላ ምን እንዲሆንልህ ነው የምትፈልገው። ተሰዶ ለመጣው ድምጽ፣ ለተገፋው ድምፅ፣ ለተጨቆነው ድምፅ፣ ለተበደለው ድምጽ ከመሆን ሌላ ምን ይሁንልህ? ገተት ሁላ…!
“…ጃዋር እኮ ዝም ቢል ኦነግ ሸኔ ሥራውን እየሠራለት ስለሆነ ነው። ቢጠፋ ሽመልስ አብዲሳ ዕቅዱን እየተገበረለት ነው። ባይታይ ዐብይ አሕመድ እያጸዳለት ነው። ጃዋር ዓላማውን፣ ዕቅዱን የሚፈጽሙለት ነፍ ሠራተኞች አሉት። የትግል አጋሮችም አሉት። እናም እስክንድር ለምን እንደ ጃዋር አህመድ ዝም አይልም ስትል ታስቀኛለህ። የአንተን ፍርሃት እስኬው ላይ ልታጋባ ታስላለህ አይደል? ቀኬያም።
“…ለማንኛውም እስክንድር ሕጋዊ መብቱን በሕጋዊ መንገድ እየተጠቀመ የፖለቲካ ሥራውን በሕግ አግባብ አሳምሮ እየሠራ ያለ ፖለቲከኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው። ያውም እንቅልፍ አጥቶ እየሠራ ያለ ትጉሕ ሠራተኛ ነው። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየሠራ ያለ አይሰለቼ ሠራተኛ ነው። አዎ እስክንድር እንደ ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ፣ እንደ ዩሱፍ ኢብራሂም፣ እንደ ጣሂር መሀመድ፣ እንደ ክሪስ ዊኒጥ ዊኒጥ ብሎ ሲያበቃ በወሳኙ ወቅት ዝም ሊል የማይቻለው አይለወጤ፣ ዘመን አይሽሬ ታጋይ ነው። ባልደራስ እንደ አብንና ኢዜማ ገሌ ሊሆን አልተፈጠረም። ባልደራስ የብልጽግናው መንግሥት አጋር እህት ኩባንያ የሆነ ፓርቲ እኮ አይደለም። የባልደራሱ እስክንድር የቅንጅቱ አየለ ጫሚሶ እኮ አይደለም። የአብኑ በለጠ ሞላን ሊሆንም አይችልም። የኢዜማው ብርሃኑ ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌና፣ የሺዋስን ሊሆንም አይችልም። እስክንድር ተቃዋሚ ነው። ተቃዋሚ ቢሉህ ደግሞ የመንግሥት ተቃዋሚ ነው በቃ። ለምን እንደ ኢዜማ አጋር አትሆንም ብሎ ነገር አለ እንዴ? በግድ? ሃይ አቦ ምንድነው ሳ?  ሂእ…
“…የዓድዋ ድል ላይ መገኘት መብቱ ነው። የየካቲት 12 ሰማዕታት በአል ላይ መገኘትም መብቱ ነው። የካራማራ ሰማእታት በአልም ላይ መገኘት መብቱ ነው። በገዛ ሃገሩ በታክሲ መሄድ፣ በእግሩ መሄድ፣ በአውቶቡስ መሄድ መብቱ ነው። ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ማለትም መብቱ ነው። አዲስ አበባ ተወልዶ አዲስ አበባ ያደገ የአዲስ አበባ ልጅ ነውና ስለከተማው ሃሳብ መስጠት፣ ቅርሶቿ አይወድሙም ብሎ መሟገት መብቱ ነው። እንኳን እሱ ተወላጁ ከበሻሻም፣ ከመቀሌም፣ ከየትም መጥቶ አዲስ አበባ የሚኖር መብቱ ነው። ድንጋይ አልወረወረ፣ ቦክስ አልሰነዘረ፣ መጠየቅ፣ መሟገት መብቱ ነው።
“…ከቻልክ አግዘው። ካልቻልክ ጮጋ በል እንቅፋት አትሁነው። እናትህ እና እህትህ፣ ሚስትህም ቀሚስ ሥር ተወሽቀህ እኚኚኚ አትበል። • ገተት ‼
Filed in: Amharic