አቻምየለህ ታምሩ
የኢትዮጵያ ጦር የዚያድ ባሬን ወራሪ ጦር አሳዶ ከመሬቱ ካስወጣ በኋላ የመጨረሻው ውጊያ የነበረው ካራማራ ላይ ነበር። ጦርነቱ ካራማራ ላይ በኢትዮጵያ ጦር ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ኦጋዴን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ዋለች። ይህ የሆነው የዛሬ 44 ዓመት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. ነው።
በዚሁ እለት ድሉ ለዓለም ሲበሰር እጅግ አስቸጋሪ የነበረውን የዚያድ ባሬ ጦር ከበባ ሰብሮ በመግባት ካራማራ ላይ የተውለበለበውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በተራራው ጫፍ ላይ ከፍ አድርጎ የሰቀለው ጀግና አርበኛ ብ/ጀኔራል [ያኔ ኮሎኔል] ደሣለኝ አበበ ነው። ብ/ጀኔራል ደሣለኝ አበበ የተወለደው ከአባቱ ከአቶ አበበ መንገሻና ከእናቱ ከወይዘሮ ሰብለወንጌል ዳዊት ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ጎጃም ውስጥ ደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ትምህርት ቤት ነው።
ደሣለኝ አበበ የዝነኛው የሐረር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ምሩቅ ሲሆን በመቀጠል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን፤ ወደ አሜሪካን አገር ተጉዞም ከእውቁ ሲራኪዩስ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪውን አግኝቷል። ከዚያም በአገራችን ጦር ኃይል ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ማለትም በቀ.ኃ.ሥ. ጦር አካዳሚ በማስተማር፣ በምስራቁ የወረራ ጊዜ የብርጌድ አዛዥና የክፍለ ጦር አዛዥ ሆኖ የሰራ ሲሆን በ1970 ዓ.ም. የ10ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ነበር።
የካራማራው ድል እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች የአድዋን መንፈስ ተላብሰው አድዋ የወደቁት የኢትዮጵያ ብርቱ ጀግኖችን ጀብዱ የደገሙበትና እውነተኛ የአድዋ ድል አድራጊ ጀግና የኢትዮጵያውያ ልጆች መሆናቸውን ያስመሰከሩት ድል ነው። የካራማራው ድል በአይነቱ ከአድዋው ድል ይለያል።
በአድዋ ድል በተለያዩ አውደ ውጊያዎችና በመጨረሻው የአድዋ ጦርነት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በነገድ፣ በሃይማኖትና በድርጅት ሳይወሰኑ በአንድ ግንባር ተሰልፈው ጠላትን ተፋልመዋል። በካራማራው ጦርነት ግን የኢትዮጵያ ጀግኖች የተዋጉት ወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር ብቻ ሳይሆን ዚያድ ባሬ ቀለብ ይሰፍርላቸው ከነበሩት የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪሎች ጋር ጭምር ነበር።
በካራማራው ድል የ10ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ብ/ጀኔራል ደሣለኝ አበበ የኢትዮጵያ አርበኞችን እየመራ የወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር አፈር ድሜ ሲያበላና በካራማራ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደ አላማ ሲያውለበልብ በክፍሉ ታደሰ የሚመራው ኢሕአፓ፣ በመለስ ዜናዊ የሚመራው ሕወሓት፤ በነ ሌንጮ ሌታና ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ከዚያድ ባሬ ጋር ተሰልፈው የኢትዮጵያ ጀግና አርበኞችን ይዋጉ ነበር።
አገርና መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ዛሬ አገዛዙ አዲስ አበባ ውስጥ የሆቴል ወጫቸውንና የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሸፍኖ አዘባኖ እያኖራቸው የሚገኙት ኢሕአፖውያን፣ ኦነጋውያንና ወያኔዎች እጃቸው በመጫኛ ታስሮ ለፈጸሙት የአገር ክህደት ወንጀል ለፍርድ ይቀርቡ ነበር።
የዚያድ ባሬን ወራሪ ጦር ሰብሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ካራማራ ተራራ ላይ ከፍ አድርጎ የሰቀለው የአርበኛው የብ/ጀኔራል ደሣለኝ አበበ የሕይዎት ፍጻሜ የሆነው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የተባለ የሰው ደም የተጠማና የሰው ስጋ የተራበ ጨካኝ አውሬ በ1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት አካሄደብኝ ብሎ ያለ ፍርድ በግፍ ረሽኖት ነው።
ማሳሰቢያ፡-
ጀኔራል ደሳለኝ አበበን «አንተ» ያልሁት ጀግና አንቱ ስለማይባል ነው!