>

በግፍ የታሰሩት የባልደራስ አባላትና የአዲስ አበባ ልጆች 14ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው! (ባልደራስ)

በግፍ የታሰሩት የባልደራስ አባላትና የአዲስ አበባ ልጆች 14ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው!
ባልደራስ

በነ ደረጄ ይበይን መዝገብ ተከሰው በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡት 15 አዲስ አበቤዎች በአድዋ ድል በአል አመፅ እንዲነሳ አደርጋችኅል በሚል 14ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል
መርማሪ ፓሊስ ያልተያዙ ግብረ አበሮች አሏቸው እነሱን ልያዝ በማለት ገና እማስረው አዲስ አበቤ አለ በሚመስል ቃል ጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ባለው መሰረት ተፈቅዶለታል
ቢንያም ታደሰ ለፍርድ ቤቱ የባልደራስ አባል ስለሆንኩ የታሰርኩት በቂም በቀል ነው ሲል ሌሎቹም አዲስ አበቤዎች በተንኮል እና በሴራ እንደታሰሩ  ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል
የባልደራስ እስረኞች የችሎት ውሎ–ቁጥር 1
•ቢኒያም እና ሳሙኤል ለ14 ቀን ተቀጠሩ፣ ቀሪዎቹ 31ዱ እስረኞች ለሐሙስ መጋቢት 1/2014 ዓ.ም ተቀጥረዋል
• ክሱ የዓድዋ እና የካራማራ ክብረ-በዓላት ናቸው
ባለፈው ቅዳሜ በግፍ የታሰሩት  33 የባልደራስ  አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ተከሳሾቹ ለሁለት ቡድን ተከፍለው፣ 31ዱ እስረኞች ከልደታ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው አብደላ ሕንፃ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ፣ ለሐሙስ መጋቢት 1/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት  ተቀጥረዋል፡፡ ጊዮርጊስ ወዳለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተወሰዱት ቢኒያም ታደሰ እና ሳሙኤል ዲሚትሪ ደግሞ ጊዮርጊስ የሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
• የ31ዱ የችሎች ሂደት   
31ዱን እስረኞች ፍርድ ቤት ይዞ የቀረበው መርማሪ ፖሊስ፣ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ፣ “ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በአድዋ እና ካራማራ ክብረ በዓላት ብጥብጥ  እና ሁከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው፡፡ ይህንን ለማጣራት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ የጋዜጠኞቹ ስልክ መመርመር አለበት” ብሏል፡፡
ለመርማሪው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት ወግደረስ ጤናው፣ ጌጥዬ ያለው እና  ስንታየሁ ለማ ሲሆኑ፣ ወግደረስ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው ንግግር፣ “በወቅቱ ስናደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር በቦታው የነበሩት ፖሊሶች ታዝበዋል፡፡ በምንም መስፈርት በሁከትና ብጥብጥ ልንጠረጠር አንችልም ” ብሏል፡፡  ጌጥዬ ያለው በበኩሉ፣ “ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲሞክሩ የነበሩት፣ እኛ ሳንሆን ሲገፈታትሩን የነበሩት የፀጥታ አካላት ናቸው፡፡ለዚህ የሰጠነው  ምንም አይነት የሃይል ምላሽ አልነበረም” ብሏል፡፡ ስንታየሁ ለማ ደግሞ፣ “የፀጥታ ሃይሎች ሲገፈታትሩን፣ መሪያችን በሰጠን ትዕዛዝ መሠረት በሰላማዊ ትግል መሬት ቁጭ ከማለት ባሻገር ምንም የፈፀምነው ድርጊት የለም፡፡ ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ተገቢ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታችንን ያክብርልን” በማለት ጠይቋል፡፡
ፖሊስ የጋዜጠኞች ስልክ ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግበት የተናገረውን አስመልክተው፣ ጌጥዬ እና ወግደረስ በሰጡት ምላሽ፣ “ፖሊስ ስልካችንን በተለየ ሁኔታ  የሚመረምርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስልካችን በተለየ መልኩ ከተመረመረ፣  በሕገ መንግሥቱ 29 መሠረት ሃሳባችንን በነፃነት እንድንገልጽ የተቀመጠው መብት የሚጥስ ተግባር  ነው የሚሆነው ” ብለዋል፡፡
•የቢኒያም እና የሳሙኤል የችሎት ሂደት
በሌላ በኩል፣ከ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተወሰዱት ቢኒያም እና ሳሙኤል፣ ከተለያዩ ሰፈሮች ታድነው ከተያዙ 13 የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ተደምረው፣ “ደረጄ ይበይን” በሚል የክስ መዝገብ ችሎት ፊት ቀርበዋል፡፡ ደረጀ ይበይን ቅዳሜ እለት ከተያዙት የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን ፣ እሱና 14ቱ ተጠርጣሪዎች፣ “በአድዋ ክብረ በዓል እለት ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል፣ ፈጥረዋል ” በመባል የምርመራ መዝገብ ተከፍቶባቸዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው አቤቱታ፣ “ያልተያዙ ግብረ አብሮች አሉ፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል አለብኝ፡፡ ስለዚህም፣ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ” ብሏል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1ኛ ተጠርጣሪ ደረጀ ይበይን ባቀረበው አቤቱታ፣ “የታሰርነው በአሉን በማክበራችን ብቻ ነው እንጂ፣ ምንም የተለየ ነገር አልፈፀምንም ” ብሏል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ተመሳሳይ ይዘት ያለው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ የቤተሰብ ሃላፊ ስለሆንን ወይ በነፃ ወይ በዋስትና ልንለቀቅ ይገባል ብለዋል፡፡  ቢኒያም ታደሰ በበኩሉ፣ “እኔ የታሰርኩት የባልደራስ አባል ስለሆንኩኝ በቂም በቀል ነው፡፡ የአድዋን በዓል በሰላም አክብረን ወደቤታችን ገብተናል፡፡ እኔ የታሰርኩት የካራማራ የድል በዓልን በሰላም እያከበርን በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱም ላይ ፍፁም ሰላማዊ ነበርን” ብሏል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል አንዳንዶቹ ባቀረቡት አቤቱታ፣ለእስር የተዳረጉት የኳስ አስጨፋሪዎች በመሆናቸው ብቻ ተነጥለው ለእስር መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ቢኒያም ታደሰም ታዋቂ የጊዮርጊስ አስጨፋሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የእነ ቢኒያምን ችሎት ለመከታተል ታድመው ከነበሩት መካከል ናትናኤል የዓለምዘውድ ማስታወሻ ሲይዝ ተገኝቶ፣ፖሊሶች ከችሎት ከሕግ ውጭ ያስወጡት ሲሆን፣ አስካል ደምሌ ደግሞ የያዘችውን ማስታወሻ በፖሊስ ተቀምታለች፡፡
• ቀጠሮ
በመጨረሻም፣ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ያሉት 31ዱ ተጠርጣሪዎች፣ ለሐሙስ መጋቢት 1/2014 ዓ.ም የተቀጠሩ ሲሆን፣ ቢኒያም እና ሳሙኤል ደግሞ፣ አብረዋቸው ከተካተቱት 13 የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ፖሊስ በጠየቀው መሠረት የ14 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
Filed in: Amharic