>

ዝምታችን ገና  ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል...!!! (በፍቃዱ አባይ)

ዝምታችን ገና  ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል…!!!

በፍቃዱ አባይ

“… የተረኝነት ጠበል ሁላችንንም እያረጠብን ነው…!!!


 

መንግሥት በመንግሥት ላይ ቢለወጥ ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል ነገር አይገኝም። አንደኛው በዝባዥ ሄዶ ሌላውን በላተኛ ከመቀየር ያለፈ ለህዝብ የሚፈይዱት ምንም አዲስ ነገር የለም። ደርግ ወርዶ ኢህአዴግ/ህወሐት ወደ ስልጣን ሲመጣ ብዙ ተሰፋ ተደረገ።ለ27 ዓመታት ግን ሀገሪቷን ከማቆርቆዝ እና ከማሰቃየት ባለፈ ለሀገር እና ለህዝብ መከታ የሚሆን ታሪክ ሳይጽፍ ወደቀ።
አሁንም ብልጽግና ሲመጣ እውነትም ለውጥ የሚከሰት መስሎን አበድን። እብደታችን የእውነት ነበር። ለውጥ የመፈለግ፣የኢትዮጵያን ትንሳኤ በመናፈቅ ፣አዲስ ዘመን እንዲመጣ ካለን ቅን ምኞት አብረን ተሰለፍን። በግሌ ባደረኩት ሁሉ አልጸጸትም። ምክንያቱም ምኞትና ተስፋዬ ከልብ የመነጨ ነበር። ነገር ግን አራት አመታትን አየን ጠብ የሚል ተስፋ የለም። እምነቴ እና ምኞቴ ልክ እንደ ጉም ብትን ብሎ ጠፍቷል።
አሁን ነገሮች ይበልጥ ወደ አስቀያሚነት እያመሩ ናቸው። እንደ አንድ ሀገሩን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ለሚያውቃት በብልጽግና ተስፋ ቢቆርጥ አይፈረድበትም። በብልጭልጭ መብራቶች፣በአረንጓዴ መናፈሻዎች፣በአማላይ እና አሳሳች ንግግሮች እየተሸወድን ነው።
ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ብቻ ለምትመስለው በዚህ መሰሉ ጌጣጌጥ ቢታለል አልፈርድበትም። እውነተኛዋ ኢትዮጵያ ያለችው ከሸገር ባሻገር ነው።ያልተቋጨ ጦርነት አሁን ድረስ መከራውን ባበዛበት ህዝብ ፣ድርቅ የሚለበልበውና የሚቀመስ ያጣ ህዝብ በበዛበት ሀገር፣ ሰላም ያጣህዝብ ፣አርሶም ሆነ ሸምቶ ለመመገብ እድል የተነፈገበትህዝብ ፣የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ታቅፎ የቀረ ህዝብ ፣የሰላም እና ደህንነት እንቅልፍ የነሳው ህዝብ፣በ21ኛው ክፍለ ዘመን በቁሙ ሰው የሚነድበት ሀገር፣ ረሀብ እና ስደት መከራውን የሚያበላውን ኢትዮጵያዊ ለማየት በእኔ ልክ ብዙ መጓዝ አያስፈልግም።በዙሪያችን ያሉትን ቅርብ ከተሞች ብቻ ማየት በቂ ነው።
አዲስ አበቤም ከብልጭልጩ ባሻገር የኑሮ ውድነቱ አቅሉን አሳጥቶታል።በአብዛኛው የከተማዋ ክፍል ውሀ የለም። መብራት በሳምንት ሁለት ቀን የሚያገኙ አምስቱን ቀን ከሰል ሲያቀጣጥሉ የሚውሉ ነዋሪዎችን በጉያዋ ይዛለች። የነዳጅ ሰልፍ፣የትራንስፖርት ሰልፍ፣ የሸማቾች እና የዳቦ ቤቶች ሰልፍ የሸገር መለያዎች ሆነዋል። የተረኝነት ጠበል ሁላችንንም እያረጠብን ነው።
አራት አመት ለአንድ ህዝብ ብዙ ነው። የብልጽግና ሰበቡ ብዙ ነው። ሁሌም ችግርን ከማቃለል ይልቅ ለችግሮቹ ምክንያት ይሰጠናል። ብልጽግና ይናገራል እንጂ አያዳምጥም። ፖለቲከኞቹ የቃላት ሽንገላውን ተክነውበታል። አውራዎቹ በዘመነ ህወሐት የተቹትን ሁሉ አብልጠው እየደገሙ ናቸው። በድግስ እና በግብዣ አብደዋል። ምኒልክ በቤተመንግስታቸው የብልጽግናን ያህል ደግሰው ስለማወቃቸው እጠራጠራለሁ።
በስመ ጉባኤ ዛሬም ፌሽታው ፣ድግሱ ፣ጭፈራው እየተደገመ ነው። ህዝብ በኑሮ ውድነት ናላው ዞሮ እነርሱ ግን ማንንም ሳይፈሩ ዛሬም እየተምነሸነሹ ናቸው። አንድ ጤና ጣቢያ ሊገነባ በሚችል ወጪ እነርሱ ዳንኪራውን እያስነኩት ነው። በየሰበቡ የሚወጡ ወጪዎች እንዲቀሩ፣የባለስልጣናት የውጭ ሀገራት ጉዞዎች እንዲቀንሱ፣የመኪና እና የነዳጅ ወጭዎች እንዲስተካከሉ፣ለኮፍያ እና ለቲሸርት የሚፈሰው ገንዘብ እንዲገደብ እና ሌሎች ደምን የሚያሞቁ ነገር ግን  በስካር ውስጥ ሆነው  ያወሩንን አሁን እረስተውታል።
ኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚያሰፈልጋት እና ባለስልጣናት ቅድሚያ በሚሰጡት መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል።
ይህ ነገም እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም። እኛ ደግሞ ዝም ማለትን መርጠናል። ዝምታችን በዚህ ከቀጠለ፣መንግስትን ከስካሩ ካላነቃነው፣ይበቃል ወደ ቀልብህ ተመለስ እና ወደ ተግባራዊ እርምጃ ግባ ብለን ጎትተን ካላመጣነው ዝምታችን እየሰረሰረ ያጠፋናል።
እንደ ህዝብ  የመረጥነህ፣ድምጻችንን የሰጠነህ ለኢትዮጵያ እንድትበጅ እንጂ በጀማ ታጥረህ በውዳሴ ሰክረህ በህዝብ ሀብት በየሳምንቱ እንድትደግስ አይደለም ማለት ይጠበቅብናል።
ምክንያቱም ሽማግሌዎች ዝምታን መርጠዋል።ተሰሚነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አድፍጠዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጭፈራው አድማቂ ሆነዋል።ሚዲያዎቻችን ለህወሐት እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም ለብጽግና ማሸብሸባቸውን ቀጥለዋል። ስክነት፣እርጋታ፣ ቆም ብሎ ማሰብን የሚሰብክ ኢትዮጵያዊ ጠፍቷል። ይህንን ለማረጋገጥ ሀገራችሁን ዞር ዞር ብላችሁ ተመልከቱ። ከጭፍን ድጋፍ እና ተቃውሞ ውጡ። ሁሉንም መርምሩ። ያን ጊዜ ሀገራችሁ እና ህዝባችሁ ያሳዝናችኋል። ያን ጊዜ ለምን እንደምጮኸም ይገባችኋል።
ዝምታችን ይሰበር!!!
Filed in: Amharic