>
5:18 pm - Wednesday June 15, 5785

ገዥዎቻችንና የሃይማኖት አባቶቻችን ከየት ነው የመጡት? (ፊልጶስ)

ገዥዎቻችንና የሃይማኖት አባቶቻችን ከየት ነው የመጡት?

ፊልጶስ


በአፍሪካ ምድር የሚፈጸመውን ግፍና በደል  ስንመለከት ርግጥ ገዥዎቻችን እንደ ህዝብ  ሰዎች ናቸው ወይ? እንደ ሰው፣ እንደ አካባቢያቸው ተወልደው ጭቃ እቡክተው በማህበሩ ውስጥ አብረው ችግሩንም ሆነ ደስታውን አይተውና ተካፍለው ያደጉ ናቸው ወይ

ከቀበሌው ገዥ እስክ ከፍተኛው  የስልጣን እረከን ድረስ ትላንትም ሆነ ዛሬ ያሉት፤ ሥልጣን ሲይዙ ከሰው ወደ አውሬነት ተቀይረው የመጡበትንና ቃል የገቡትን  ‘ረስተው፤  የገዛ ወገናቸውን  የምድርን ስቃይ ሁሉ የሚያሳዩት ለምን ይሆን?

በተለይ ደግሞ ዛሬ  በእኛ አገር ገዥዎቻችንና አጫፋሪዎቻቸው የሚፈጽሙት  ርግጥ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ምድረ የተፈጠሩ ናቸውን? እንመራሃላን የሚሉት ወገናቸው  ያለቅሳል፤ እነሱ ይስቃሉ፤ ህዝብ በሃዘንና  በረሃብ ይጠበሳል፤ እነሱ በደስታና በቁጣና ተይዘው ይፈነጩበታል። 

ኑሮ ማሸነፍንና በሰውነቱ ብቻ ተከብር መኖር የሚፈልገውን ትውልድ የፈጠራና የጥላቻ ታሪክ  እየጋቱና  ”ርስበርስ እያስተራረዱ በሚፈስ ደም ስልጣን ሲይዙ፣ ገንዘብ ሲሰበስቡ፣ መድረክ ላይ እየወጡ ሲደሰኩሩና ሲደነፋ፤ ርግጥ እንደ ሰው እንቅልፍ ይወስዳቸዋል ወይ? እንደ ሰው አንድ ቀን እንሞታለን ብለው ያስባሉ ወይ?  

…እንዲህ በዚህ ግዜ -እንዲህ በዚህ ሰዓት

ከጠዋትእስከ ማዕልት፣ ከማዕልት እስከ ንጋት፤

ኢትዮጵያን—— ያየ ሰው

ድምጿን——- የሰማ ሰው፤

የጭካኔው ዓይነት – የሰቆቃው ብዛት

ቀመር ስለሌለው፣ በሰባአዊ -ፍጥረት፤

ውሉ ስለጠፋ፣ መነሻ-መድረሻው

እንኳንስ  የሰው ልጅ፤  ግራን- ግራ ገባው::…

ሰውየው ህልማ ያያል፤ ህልመኛው ሰውየ፤ ለሊቱን ሙሉ ያየው ህልም ሰለረበሸው በጠዋቱ ተነስቶ  ወደ ታወቁት ህልም ፈች ሄደ።፡

ህልመኛውም ለህልም ፈችው ያየውን ህልምና የለቀቀበትን ፈርሃት ማስረዳት ጀመረ።

የሚያስፈራ ህልም ነው ያየሁት፤ ሁለት ዓይኔ ጠፍቶ፣ ሁለቱም ጆሮየ ደንቁሮ፣  አልሰማ፣ አላይ ማሰብም ሆነ ማገናዘብ አቅቶኝ፣ ከሙት ሬሳ ጋር እየታገልኩ፣ ሙሉ ለሊት ስሰቃይ ነው ያደርኩት። ምን ኣይነት ስቃይ ሊመጠባኝ ይሆን? ” በማለት ህልም ፈችውን ጠየቀ።

ህልም ፈችውም ፈገግ ብለውበጣም ጥሩ ህልም ነው ያየኽው። ልትደሰት ይገባሃል።አሉት።

ህልመኛውእየቀለዱ ነው አይደል? ወይስ ሊያጽናኑኝ ነው?” አላቸው።

አየህ ! ያየህው ህልም የሚያሳየው፣  በቅርቡ ገዥ ትሆናለህ። ሥልጣን ትይዛለህ።እሉት። 

ቀጥለውምአየህ!  በኢትዮጵያ ምድር የዘመናችን  ገዥዎች  ዓይን አላቸው ግን አያዩም። ጀሮ አላቸው ይነገራቸዋል፤ ግን  አይሰሙም፤ አያዳምጡም ጭንቅላት አላቸው ግን ህሊና የላቸውም። የፈለገውን ያህል ቢሞት፣ ቢገደል ምናቸውም አይደልም። እናም  የህልምህ ፍቹ የሚያሳየው በቅርቡ ትልቅ ባለሰልጣን እንደምትሆን ነው።በማለት ነግረው አሰናበቱት።

በ’ርግጥም ገዥዎቻችን የሚያይም ሆነ የሚሰማ ጀሮና የሚያገናዝብ ህሊና ቢኖራቸው ከዚህ ደራጃ ባልደረስን ነበር። ማን ነበር ” በኢትዮጵያ ወስጥ ባለሥልጣንና ባለሃብት ለመሆን ከፈለክ፤ ደደብና ደፋር ሁን።” ያለው።

አሁን ካሉት ከጠ/ሚንስተር አብይ አህመድ ጀምሮ ትላንትም የነበሩም  ገዥዎቻችን፤ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደራጃ በኢትዮጵያ ምድር የተውለዱና ያደጉ፤  መራብን መጠማትን፣ መታረዝን፣ በአጠቃላይ መገለጫችን የሆነውን ድህነትን ያዩና ያጣጣሙ ናቸው። ወደ ፓለቲካው ዓለም ለመግባትና ሥልጣን ለመያዛቸውም ምክንያትና ዋና አላማ የሚያደርጉት፤ የደሃ ወገናቸውን ህይወት መቀየርና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በመስበክ ነው። ግን በሚዘገንን ሁኔታ   በተለይም በአሁኑ ግዜ  እንኳን ደሃ ወገናቸው  ትዝ ሊላቸው    ንብረትና ሃብቱን ግጠው ጨርሰው፣ የኢትዮጵያዊ ደም የሚጠማቸውና የሰው ደም ካላዩ  ስልጣን ያላቸውና የገዙ የማይመስላቸው ገዥዎች መበሩን ይዘው፤ ከየተ እንደመጡና ሰው መሆናቸውን  ለመጠራጠር  ተገደናል።

የስቃያችን እና የመከራችን  ‘’እግዚኦታ!” ደግሞ መራራ የሚያደርገው፣ የሥጋን ዓለም ንቀው ለእግዚአቢሄር አደርን ከሚሉ የሃይማኖት ተቋምም ሆነአባትስለ ህዝብ ስቆቃና ስለ ገዥዎቻችን እረመኔነት  መናገርና መገሰጥ አይደልም ተባባሪ ሆነው፤ እነሱም በህዝብ ገንዘብና ንብራት የዘመኑን የቅንጦት ኑሮ ሲኖሩ ማያታችን ነው።

በእውነቱቆምብለን እናስብ። እስከ አሁን የጠፋው ህይወት፣ የፈሰሰው ደም፡ የወደመው ንብረት፤  የደረስው ስቆቃና ዋይታ አዕምሮ ከሚገምተው በላይ ነው። እስከ መቼ  እንቀጥላለን? ኢትዮጵያ ሰላስ ወይም አምስት ወይም ሶስት ወይም  መቶ ዓመት ወይም የአንደ ወር እድሜ ይኑራት፣— ዛሬ እኔ፣ አንች፣ አንተ፤ ሰው በመሆናችን ብቻ ተከባብረን የህግየባለይነትን አሰፍነን የማንኖርበት ምክንያት የለም። አይኖርምም። ለዚህ ደግሞ እደግመዋለሁ፤  ሰው መሆናችን በቂ ነው።  አንድ ታዋቂ ፈላስፋአገሬ ዓለም ነው፤ ዘሬም የሰው ልጅ ነው።ይል ነበር አሉ። ይህ ፈላስፋ አሁን በህይወት ቢኖርአገሬ ዓለም ነው፤ ዘሬም የሰው ልጅ ነው፤ ከኢትዮጵያ በቀር።”  የሚል ይመስለኛል።

 ገዥዎቻችንም ሆናችሁ የሃይማኖት አባቶች እስቲ ታሪክ ሰርታችሁ ለትውልድ የሚጠቅም ስራ ሰርታችሁ ለማለፍ ነገ ሳይሆን ዛሬ ተነሱ። ህዝብም ከፋፍለው የሚገዙንን እና በሃይማኖት ስም የሚነግዱብንን  ግብዞችበቃችሁ!” እንበላቸው። ምክንያቱም  ከየትም አልመጡም፤ከእኛ ከራሳችን የወጡ ናቸውና። በጎሳም ሆነ በመንደር ተቧድነን የትም እንደማንደርስ አየተነዋል።  ቅዱሱ መጸሃፍ፤ርስበርስ ብትጣሉ፤ ርስበርስ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ–” ይላል። 

 ኢትዮጵያ ለሁላችንም ከበቂ በላይ ነች። ሥልጣን ለሚፈልገው ሥልጣን፣ ሃብት ለሚፈልገው፡ ሃብት፡ በአጠቃላይ  ሰርተን ልንበለጽግባትና ሁላችንም ማስተናገድ የምትችል አገር ናት።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic