>

መቼ ይሆን? (ዘምሳሌ)

መቼ ይሆን?

ዘምሳሌ


እድላችን ቀንቶ  ተስፋችን ሚቆየን
የሀገር ምጡ ብስራት የህልማችን እውን
ደርሶ የምናቅፈው ከልብ ተለውጠን
ውልደቱ መች ይሆን  የደስታችን ዘመን

መቼ ይሆን ኢትዮጵያ
የማይሆነው መሬትሽ የእቡያን መብቀያ
የዘራፊዎች ድርጎ ወንበር መሸለሚያ
የጨካኞች  በትር እሳር መፈልፈያ
የኋላቀርነት  ጠርዝ  የጋርዮሽ  ትቢያ

ቀንሽ  መቼ  ነው ሀገሬ
የተጫነሽ  ሸክም  የመከራው  ቀንበር
የታፈንሽበት  የጥቂቶች የጥላቻ  ክምር
የዘር ምንገላው  ሸር የሀሰት ጎሬና እስር
ከላይሽ ወርዶ ከውጥሽ ከስሞ ሚቀበር

እስከመቼ መቼ እናት አለም
ብቅ የሚለው ተስፋችን ሚጨልም
እድሜና ታሪክሽ  ፅናትሽ ሲታለም
የመታደስሽ ጥንስ እየፈላ ሚከስም
የበረከትሽ ፍሬ በነጣቂዎች ሚለቀም

አሁንማ
አርበኞችሽ  ሸመገሉ  አባቶችም በሞት ተገለሉ
ጠላቶችሽም በዝተው  ጉያሽ ስር በቀሉ
ጊዜ  ባደላቸው  ስልጣን ገዢዎች  እየታበሉ
በኋላቀርነት  ወድቀው በዘር  ጉንጉን  ተከለሉ

ደሞኮ ሀገር ማለት ሰው ነው  ይሉናል
ሰው ግን  ሀገር  ተነፍጎት ከምድሩ  ይነቅላል
ዘር ተመርጦ ተለይቶ በገዛ ምድሩ ይንከራታል
ስፍራ ጎጥ ተመድቦ በደቦ ይፈረድበታል

ግና እናት አለሜ እለቱ  የመታነፅሽ ብስራት
የሚበጀው ዳግም የሰላምሽ ስሬት
የሚፀናልሽ  ሰናይ  እፎይ የምትይበት
ማልዶ ብስራቱ ሰላምሽ ፀንቶ ሚታወጅበት

እስከመቼ  በተስፋ እንጠብቅ
ሳይደላን እየኖርን  በችግር ስንፏቅ
ነፃ አውጪ ሲነግስ ነፃነትን ሳናውቅ
ቀልባችን  ሲረግፍ  ሰላማችን ከኛ ሲርቅ

ስሚኝ  እንጂ እናት አለም
እንዳንቺ  እኮ እልቂት የበዛበት ህዝብ የለም
በዘረኝነት የተመረዘ  እርስበርሱ የሚላተም
አድሮ ጥጃ ያልገባው የማህፀንሽ መርገም

መቼ ይሆን ክስተቱ   የተስፋው ትውልድ
ታሪክሽን አቃንቶ  በጎዳናሽ   የሚሄድ
ሀገር የሚያስከብር  አፍረን እንዳናጎበድ
የምናየው  ወይ የምንሰማው ሲወለድ

ውልደቱ መች ይሆን  የደስታ ልቀቱ ዘመን
የሚሰምረው   የምንጠብቀው  ብሩህ ቀን
የምንታደስበት ዘር መቋጠሩ  አብቅቶን
የምኖረው ኑሮን በመሬትሽ እንደልባችን ሆነን

መች ይሆን ሀገሬ  ከቶ  የምናየው  በቶሎ
ምስቅሉ የሰዎችሽ  ልቦና ተስተካክሎ
የባንዲራሽም ቀለም  ምድረ ገፅሽን አካሎ
ህዝብሽ  የሚኖረው ቃል ለምድር ሰማይሽ ምሎ
መቼ ይሆን ?

Filed in: Amharic