>

መልካም ልደት ለታላቁ የዲፕሎማሲ ሰው...!!! (ታሪክን ወደኋላ)

መልካም ልደት ለታላቁ የዲፕሎማሲ ሰው…!!!

ታሪክን ወደኋላ 

*.... ከ 110 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ኢትዮጵያን በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉትና በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ፖለቲከኞች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉት ስመ ጥሩ ላዕከ መንግሥት (Diplomat) ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የተወለዱት ዕለት ነበር
 
“መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም ተወለድኩ ፣ የአማርኛ ትምህርቴን በራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን አጠናቀቅሁ፣ የውጭ ሀገር ትምህርት ምኒልክ ተማሪ ቤት ለሁለትና ለሦስት ዓመት ተተማርኩ በኋላ እ.ኤ.አ.
በ 1925 አለክሳንድሪያ ግብፅ በሚገኘው የፈረንሳይ ሊሴ ትምህርቴን እንድቀጥል ተላክሁ፡፡ እዚያም እ.ኤ.አ. ከ 1925 -1931 ትምህርቴን አጠናቅቄ የፈረንሳይን ባካሎሪያ /ባሸልዩ/ ተቀበልኩ፡፡ ተዚያም ፓስ ሶርቦን ዩኒቨርስቲ ሕግን ስማር ኦት ኤቱድ /Houte Etude Connerdiala/ እንዲሁም ሲዮንስ ፖለቲክ የሚባሉ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶችም ገብቼ እማር ነበር፡፡ በነዚሁም ትምህርቴን አጠናቅቄ እ.ኤ.አ. ከ1931-1936 ያገኘኋቸው ዲግሪዎች፡-
– ሊሳንስ የሕግ / L.L.B ወይም Licence en Droit
– ዲፕሎም ዶ ዶክቶራ በፑብሊክ ሎው (Diplome de Doktorat en Droit Public)
– በኢኮኖሚክስ የዶክቶራ ዲፕሎም (Diplome de Doktorat en Droit Economique)
– ሰርቲፊካ ዴቱድ ሱፒሪዬንስ ኮምርሲአል (Certificat d’Etude Superieures Commercials)
– የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ቤት የጨረስኩበት ሰርቲፊካ ናቸው፡፡” (ምንጭ፡- የአክሊሉ ማስታወሻ፣ ገጽ 2)
ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ለእናት ሀገራቸው ካበረከቷቸው ሥራዎች መካከል በጥቂቱ…….
▻ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ውክልናና ጥቅም እንድታገኝ ያደረጉት ተጋድሎና ጀብድ ቀን በባቡር ፣ ሌሊት በመርከብ እንዲሁም በአውሮፕላን ያለእረፍት ለበርካታ ቀናት እየተጓዙ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ደክመዋል፡፡
▻ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ ወቅት ባደረሰችው ጉዳት ካሳ ልትከፍል ይገባል ብለው በመከራከር በጊዜው ጥቁሮች እንደሰው በማይታዩበት ጊዜ በአውሮፓ የአለም መሪዎች ስብሰባ ላይ እሳቸው ብቻ ጥቁር በስብሰባው ላይ ተገኝተው ለኢትዮጵያ የሚከፈላት የካሳው ብር 5 ሚሊዮን ዶላር ነው
ተብሎ ቢወሰንም ክቡር አክሊሉ ግን እንደዛ እንደማይሆን በውሳኔው እንደማይስማሙና በመሟገታቸው የክፍያው የብሩ መጠን ወደ 25 ሚሊየን ዶላር ከፍ እንዲል አድርገዋል።
▻ ገና በወጣትነታቸው በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ፤ በአፋምቦ ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላና ኤርትራን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከነበሩ ቅኝ ገዢ አገራት ግዛትነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል።
▻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የእንግሊዝ መንግስት ያቀረበው ድርድር ወድቅ አድርገው የራሳችን ብሔራዊ ባንክ ባለቤት እንድንሆን አድርገዋል።
የእንግሊዞች ሀሳብ የነበረው ባንኩ መቀመጫውን በለንደን ይሆናል የባንኩ አስተዳደሮች በእንግሊዝዋ ንግስት ይመረጣል ኢትዮጵያ ወርቁን ትልካለች ከዛ ተመርቶ ይላክላቸዋል ሲሉ ጀግናው አክሊሉ ሀ/ወለድ ግን “እኛ የራሳችን ባንክ እዚሁ አ/አ እንዲሆን ነው ምንፈልገው ንግስቲቷ በኛ ባንክ ሰራተኞች መራጭ ማን አደረጋቸው እኛ የናንተ ቀኝ ተገዢዎች አይደለንም” በማለት ተከራክረው በማሸነፍ ኢትዮጵያ የራሷን ገንዘብ አምራች አድርገዋታል።
▻ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተሰሩ ታላላቅ ስራዎችና ተቋማት ምስረታ በብዙው መስኮች የተሳተፉ ሲሆን በግንባር ቀደምትነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምስረታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ።
▻ እኚህ ታላቅ ዲፕሎማት ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር ከነ ዶ/ር ምናሴና ክቡር ከተማ ይፍሩ ጋር በነበራቸው ጥምረት የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንም በመመስረት በሀገራችን ውጪ ጉዳይ ታሪክ የምንጊዜም ወርቃማው ዘመን ሆኖ በታሪክ እንዲታወስ ታላቁን ሚና ተወጥተዋል።
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°
የታሪክ ነገር ሆኖ እሥር ቤት ገባን፡፡ ከፀሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ጋር ተገናኘን፡፡ እንደ ነገ ሊገደሉ ዛሬ ከእርሳቸው ጋር ራት በላንና እስከ 10 ሠዓት ከሌሊቱ ስናወራ ቆየን፡፡ ብዙ የአገር ጉዳይ ነገሩኝ፡፡ ‹‹እኛ እኮ ታሰርን ያለ ሕግ›› አሉኝ፡፡ ‹‹እንዳልካቸውን ጠየቅን እርሱ ‹መርማሪ ኮሚሲዮን ተቋቁሟል፤ በዚያ በኩል መልስ ይሰጣችኋል› አለ፡፡ የጦር ሚኒስትሩን ብንጠይቀው እርሱም ተመሳሳይ መልስ ሰጠን፡፡ በምን ምክንያት ያለ ሕግ እንታሰራለን ?›› አሉ …
ሊገደሉ ሲጠሩ ሄጄ አነጋገርኳቸው፡፡ ዮጋ ይሰሩ ነበር፡፡
<ለምን ይመስልሃል [የተጠራነው] ?›› አሉኝ፡፡
‹‹ምንም አይደለ ለፎቶግራፍ ምናምን ነው…›› አልኳቸው፡፡
ጨበጡኝና (በፈረንሳይ ቋንቋ) ካሚም ኬል ዴፎርማሲዮን ፕሮፌሲዮናል “የሆነ ሆኖ ይህ የሙያ ትምህርትህ ምን ያህል አወላግዶሃል” ሊገድሉን ሲወስዱን ‹ምንም አትሆኑም› ትለናለህ ተሾመ ?›› ብለው ኮነኑኝ፡፡ ሳብ አደረጉና ጨበጡኝ፤ ሳሙኝ እና ወጥተው ሄዱ፡፡ ከዚያ ወዲያ አላየኋቸውም፡፡
አቶ ተሾመ ገ/ማርያም በዘውድ መንግሥት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የነበሩ ከሸገር ሬዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ከሰጡት ቃለምልልስ የተናገሩት (ጥቅምት 27 ቀን 2003 ዓ.ም) የተወሰደ።
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°
አለመታደል ሆኖ ጀግኖቿን ቅርጥፍ አድርጋ የምትባል ሀገር  ክቡር ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከመወከልና ለጥቅሟ በመሟገት ዘብ የቆሙ እኚህ ታላቅ የዲፕሎማቲክ ሰው እረፍት አጥተው እንዳልተሟገቱ ሁሉ …በኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከሌሎች 60 ኢትዮጵያውያን ጋር በደርግ ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡ በወቅቱ ሲገደሉ ዕድሜያቸው 63 ዓመት ነበር።
እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነት የምታወጧት ከሆነ ድርጊታችሁን በጸጋ እንደ በረከት እንቀበላለን።”..………ፀሐፊ አክሊሉ ከመገደላቸው በፊት የተናገሩት ንግግር
‹‹የምንጊዜም ወርቃማው ኢትዮጵያዊ ላዕከ-መንግሥት (Diplomat)›› 
ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ውክልናና ጥቅም እንድታገኝ ያደረጉት ተጋድሎ ከማንም ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ሊሰወር የማይገባ አኩሪ ጀብድ ነው፡፡ ቀን በባቡር፣ ሌሊት ደግሞ በመርከብ እንዲሁም በአውሮፕላን ያለምንም እረፍት ለበርካታ ቀናት እየተጓዙ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ደክመዋል፡፡
ገና በወጣትነታቸው በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አፋምቦ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላና ኤርትራን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከነበሩ ቅኝ ገዢ አገራት ግዛትነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሰሩትን ስራም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡
ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከመወከልና ለጥቅሟ ከመሟገት በተጨማሪ፣ እድገት እንድታስመዘግብና የበለፀገች አገር እንድትሆን የሰሩት ስራም በዋጋ የማይተመን ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከምትመካባቸው ግዙፍ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሰረት የክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነበር፡፡
ጀግኖቿን ቅርጥፍ አድርጋ እየበላች ጠላቶቿን አንቀባራ የምታኖረው ኢትዮጵያ፣ ለባለውለታዋ ለአክሊሉ ሀብተወልድ ውለታና በጎ ስራም ምላሿ በጥይት ደብድቦ መግደል ነበር፡፡ ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቀን ከሌሊት እየተጓዙ ለኢትዮጵያ ጥቅም እንዳልደከሙ ሁሉ … ኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም ከሌሎች 60 ኢትዮጵያውያን ጋር በደርግ ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
ክቡር ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከዛሬ 109 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለዱት።
ክብርና ዘላለማዊ እረፍት ለክቡር አክሊሉ 🙏
” መልካም ልደት ለታላቁ የዲፕሎማሲ ሠው !!!
Filed in: Amharic