>

በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብል[ጽ]ግና ምድራችን ካስተናገደቻቸው ዘረኛ ድርጅቶች ሁሉ ዘረኛነትን ፍጹማዊ ያደረገ ዘግናኝ የዘር ድርጅት ነው! (አቻምየለህ ታምሩ)

በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብል[ጽ]ግና ምድራችን ካስተናገደቻቸው ዘረኛ ድርጅቶች ሁሉ ዘረኛነትን ፍጹማዊ ያደረገ ዘግናኝ የዘር ድርጅት ነው! 
 
አቻምየለህ ታምሩ

 

*…. ብል[ጽ]ግና ከመንፈስ አባቱ ከኢሕአዴግ እጅግ የሚከፋ ዘረኛ የኮምኒስት ድርጅት ነው።  ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ዳያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ነበረው። የብል[ጽ]ግና ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ግን ዘርና ዘር ብቻ ነው።        
ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝደንትነት ስለሚመራው ብል[ጽ]ግና ልዩ ባሕርያት ሲናገር በኢትዮጵያ ከተከሰቱ ፓርቲዎች ሁሉ አገር በቀል እሰቤ በውስጡ በመያዝ የተመሰረተ የመጀመሪያው ፓርቲ መሆኑን ገልጿል። ይህን የተናገረው ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው እለት በዋለው ውሎ የፓርቲውን የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት “ሲያስመርጥ” ውሏል።
ማእከላዊ ኮሚቴ ወይም Central Committee እንደ ቀድሞው ሶብየት ኅብረት፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ አልባኒያ፣ ሰሜን ኮሪያ ወዘተ ያሉ የኮምኒስት አገሮችን ይገዙ የነበሩ የኮምኒት ፓርቲዎች ስራ አስፈጻሚ አመራር አባላት የሚጠሩበት ስያሜ ነው። በአገራችንም በደርግ ዘመን አወቃቀሩ ከሶብየት ኅብረት ኮምኒት ፓርቲ የተቀዳ “የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ”፤ በፋሽስት ወያኔ ዘመን ደግሞ ከአልባንያ የተቀዳ “የኢሕአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ” የሚባል የስራ አስፈጻሚ አመራር አባላት የሚጠሩበት ስያሜ ነበር።
ዐቢይ አሕመድ ልዩ ተክለ ቁመና ሊያላብሰውና የአገር በቀል እሳቤን መሰረት በማድረግ የተመሰረተ አድርጎ ሊሸጠው የሚፈልገው ብል[ጽ]ግና ፓርቲ እንደ ኢሠፓና ኢሕአዴግ ሁሉ የነ ቻይና፣ የነ ሶብየት ኅብረት፣ የነኩባና የነ አልባንያ ኮምኒስት ፓርቲዎች  ስራ አስፈጻሚ አመራር አባላት በሚጠራበት የማእከላዊ ኮምቴ ስያሜ የፓርቲውን ስራ አስፈጻሚ አመራር ስብስብ እየጠራና የኮምኒስት ፓርቲዎች ስራ አስፈጻሚና ማእከላዊ ኮሚቴ እያሉ በሚያደራጁበት የአገዛዝ ሰንሰለት ካድሬዎቹን አደራጅቶ ነው። ድንቄም አገር በቀል እሰቤ በውስጡ በመያዝ የተመሰረተ የመጀመሪያው ፓርቲ!
ብል[ጽ]ግና ከመንፈስ አባቱ ከኢሕአዴግ እጅግ የሚከፋ ዘረኛ የኮምኒስት ድርጅት ነው።  ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ዳያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ነበረው። የብል[ጽ]ግና ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ግን ዘርና ዘር ብቻ ነው።
የብል[ጽ]ግና ማእከላዊ ኮሜቴ አባላት የተሰባሰቡት ያልመረጣቸው እንወክለዋለን የሚሉት የነገዳቸው ሕዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አጠቃላይ ቁጥር አኳያ ተሰልቶ ነው። የመለስ ዜናዊው ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካን በኢትዮጵያ የተከለ ነቀርሳ ቢሆንም እንደ ዐቢይ አሕመዱ ብል[ጽ]ግና ግን የዘር ፖለቲካን ፍጹማዊ ያደረገ አልነበረም።
የመለስ ዜናዊ ኢሕአዴግ ፍልስፍናዬ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ይል ስለነበር የአራት እኅት ተብዮ ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከአራቱም ድርጅቶች በእኩል ቁጥር የሚውጣጡ ነበሩ። የዐቢይ አሕመድ ብል[ጽ]ግና ግን ፍልስፍናው ዘር ስለሆነ ዲያሌክቲክ ማቴሪያሊዝሙ ዘር ብቻ ነው።
ኢሕአዴግን አዋሕጄ ብልጽግና ሆኛለሁ የሚለው የዐቢይ አሕመዱ ብል[ጽ]ግና የነገድ ድርጅቶች ግንባር የነበረው ኢሕአዴግ በነገድ ያላከፋፈለውን የእኅት ድርጅቶቹን የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ድርሻ  ውሕዱ ብል[ጽ]ግና በየነገዱ ሕዝብ ቁጥር ልክ አከፋፍሎታል። እንዲህ አይነት ፍጹማዊ የሆነ የዘር ምደባን መሰረት ያደረገ ዘረኛ ድርጅት በአለም ታሪክ ታይቶ ስለማወቁ እርግጠኛ አይደለሁም።
ባጭሩ በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብል[ጽ]ግና የመለስ ዜናዊው ኢሕአዴግ እንኳን ተግባራዊ ያላደረገውን የዘር ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ወደ መሬት በማውረድ የዘር ፖሊሲን ፍጹማዊ ያደረገ፤  በአገራችን ታሪክ በአምስት አመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራም ቢሆን ታይቶ የማይታወቅ የዘረኛነት ፖሊሲን መመሪያው ያደረገ የምድራችን ዘግናኝ ፍጹም ዘረኛ የኮምኒስት ድርጅት ነው።
Filed in: Amharic