>

የአብን አመራር  የ"ጦስ ዶሮ"ይዞ በመቅረብ ዝምታውን  ሰብሯል...!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

የአብን አመራር  የ”ጦስ ዶሮ”ይዞ በመቅረብ ዝምታውን  ሰብሯል…!!!
ወንድወሰን ተክሉ

*…. በፋኖ እና በደጋፊዎቹ ላይ ግን  ሰይፉን መዟል- ምን ወጥኗል?? 
የአብን ጠላቶች ወዳጅ የአብን ወዳጅ ደጋፊዎች ደግሞ ጠላት የተደረጉበት ሰሞነኛ ዘመቻ፦ 
*…. የአብን አመራሮች በለጠ ሞላ፣ጣሂር መሀመድ፣ጋሻው መርሻና ክርስቲያን ታደለ እጅግ የተናበበ ዘመቻን ከፍተዋል። የዘመቻቸው አስኴል ኢላማም «መንጋ፣ምቀኛ፣የፖለቲካን “ሀ” “ሁ”ን የማያውቅ መሀይም፣የወያኔን መመታት የማይፈልግ…..» እና ወዘተ ብለው በገለጹት ደጋፊዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ማየት አጃኢብ አስብሏል። 
በለጠ ሞላ  ደጋፊውን « መንጋ» እያለ ሲገልጽ  ጋሻው መርሻ ደግሞ የአማራን ፖለቲካ «አታካች» እያለ በመግለጽ  ከደጋፊዎቹ የሚስተጋባውን ጥያቄ ሲያጣጥልና አታካች ፖለቲካ ብሎ ሲደመድም የድርጅቱ ቃለ አቀባይ የሆነው ጣሂር ደግሞ « የወያኔን መመታት የማይፈልግና የፖለቲካን ሀ ሁን የማያውቅ ጫጫታ» እያሉ  በመግለጽ ነው ምታቸውን የሰበሩት። ይህንንም ድርጊታቸውን  በጸረ አማራነታቸውና በጸረ አብን አቌሞቻቸው ነጋጠባ ሲሳደቡና ሲያወግዟቸው በነበሩ የኢዜማ እና የብልጽግና አክትቪስቶችና ጋዜጠኞች በኩል በታላቅ አድናቆትና ሙገሳ እየተቀባበሉ  ሲያስተጋቡላቸው እያየን ያለንበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው።
በአጭር  አገላለጽ አብን የጥቃት ሰይፉን ከሰገባው በመምዘዝዞ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት፣በሀሳብና በሞራል ሲደግፉት በነበሩ ደጋፊና አባል አማራዊያን ላይ አነጣጥሮ ሲሰብቅ የአማራን ሕዝብ አማራዊ አደረጃጀት እንዳይፈጠር እና ብሎም ከተፈጠረም በኋላ ተሽመድምዶ እንዲበተን በማድረግ ደረጃ በመንቀሳቀስ ጸረ አማራ የሆኑት ኢዜማዊያን እና ጽግናዊያን አበጀህ የእኛ ጀግና መብሰል ማወቅና ማደግ ማለት እንዲህ ነው እያሉ እንደ እብድ ገላጋይ ካራና ገጀራ እያቀበሉ ሲያጨበጭቡ ያሉበትን ሁኔታ  እያየን ያለነው።
ከዚህ መንፈስና እይታ በተለየ ሁኔታ የድርጅቱ  የውጭ ጉዳይ ኋላፊ የሆነው ዶ/ር ቴውድሮስ ኋይለማሪያም ደግሞ ለየት ባለ ሁኔታ «የሌባ ጣት ፖለቲካ ምን ይፈይዳል» በሚል ርእስ ስር
«….እውነት እንነጋገር ከተባለ ህዝባችን አልካደንም። ባለማተብ ባለዲን ፣ እምነቱን አጥባቂ ቃሉን ጠባቂ ነውና። ከስፍር ጎድለንና ከገለባ ቀልለን የተገኘነው እኛው ነን…» በማለት ከአራቱ አመራሮች አጠቃላይ እይታና ፍረጃ ወጣ ባለመልኩ ችግሩ እኛውጋ ነው ያለው የሚል ይዘት ያለውን መልእክት ዛሬ አስተላልፎ ያየነው።
የድርጅቱ መሪ በለጠ ሞላ «ጩህት በዛ» በሚል ር እስ ስር «…. “አማራ፣ አማራ!” እያለ በበዛ ጩኸቱ የሚያደነቁረን መንጋና የመንጋ አዝማች ስሜቴን ለአፍታም አስቦት አያውቅም ….» በማለት መንጋ እያለ  ስሜቱን እና እይታዊ አቌሙን ገልጿል።
እንደ በለጠ ሞላ አባባል  በእሱና በባልደረቦቹ ላይ ትችት ሂስና ጥያቄ ያቀረበውን አማራን «…. እናም በድንጋይ ሲወግረኝ የከረመው ነውርየለሹ መንጋ…» እያለ ከገለጸ በኋላ በመቀጠልም
«…….መንጋ ምክንያት የለውም ወይንም ምክንያቱ ምቀኝነት፣ ተንኮልና ክፋት እንጅ እውነት የህዝብ ጉዳይ አሳስቦት አይደለም …» ይለንና    ቀጥሎም  « እኔም ብቻየን አይደለሁም። ሁለትም፣ ሶስትም፣ አራትም አይደለንም። ብዙ ነን። በምቀኞችና በመንጋ ስንወገርና ስማችን ሲብጠለጠል ዝም ያልነው አስበንና መርጠን ነው» በማለት ይገልጻል።
ይህ ማለት ሶስቱ የአብን አመራር ከደጋፊዎቻችን እና ከአባሎቻችን የተሰነዘረብን ትችት ነቀፌታና ተቃውሞ መሰረት ያለው ትችት ቢሆንም በእኛ በኩል ያሉንን እውነታዎችን የማሳወቅ ሁኔታ ስላልነለረ እውነታው የተወቅስንበት እውነታ ያለው እንደመሆኑ መጠን የእኛ ምክንያት ይህ ነው በሚል ከመግለጽ በአካሄዳቸው ላይ ጥያቄ ያነሳን በጅምላ መንጋ ቅናት ጥላቻ በሚል ፍረጃ  ሲገልጹት ታይተዋል። በሌላ አገላለጽ ሶስቱ አመራሮች እኛ የፈለግነውን ብንሰራ የምንሰራውን የምናውቅ ነን እና ስለምን ጥያቄና ትችት ልታቀርቡልን ቻላችሁ የሚሉ መስለዋል።
ለመሆኑ ይህንን ያህል ዝም ያሰኛቸውና ተዘመተብን የሚሉትስ ጥያቄ ምንድነው ??
፠ የአብን አመራሮችን ከፖለቲካ መድረክ አጥፍቶ በዝምታ የቀበረው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ 
👉 ከብልጽግና ጋር ተቀላቅሎ ስልጣን መቀራመትን አስመልክቶ
👉 በመተከል እና  በኦሮሚያ ለሚጨፈጨፈው አማራ ጉዳይ ለምን አብን ዝም ይላል
👉 የበለጠ ሞላ ጸረ አማራ ከሆነው  አንዳርጋቸው ጽጌና ከወሎ ሕብረት ጋር ያልተገባ ፖለቲካዊ ግልሙትና ለምን አስፈለገ
👉 አብን እራሱን ችሎ የአማራ ሕዝብ ትክክለኛ እና ብቸኛ ተወካይ ሆኖ መጔዝ ሲገባው ስለምንድነው የመንግስት አገልጋይ ሆኖ የስልጣን ቅንጣቢን ቃርሞ የድርጅቱን ዓላማና የሕዝቡን እምነትና ተስፋን የሸጠው ??
👉 አብን ለምንድነው ከ48% በላይ አማራ በሆነበት አዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ዝም የሚለው??
👉 አብን የአማራ ልጆች በሆኑት ፋኖዎቻችን ላይ የያዘው ዝምታ ለምንድነው??
የሚሉት ጥያቄዎች ወሳኝኝ ጥያቄዎች ናቸው የአብንን አመራር በዝምታ ውስጥ አስገብቶ የነበረው።
ይህንን እጅግ ፍትሃዊ የሆነን ጥያቄ ሁሉም በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ በኦሮሚያና በመተከል ለሚገደለው አማራ ዝምታን የመረጡት መግለጫ ማውጣትና መንጫጫት አይጠቅምም ብለው እንደሆነ ነው ጣሂር ሊነግረን የቻለው።
ዛሬስ ዝምታቸውን የሰበሩት ምላሹን ይዘው በመምጣት ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ እስከዛሬ ዝም ያሉት የ”ጦስ ዶሮ “ፍለጋ ሲባዝኑ ነበር በሚያስብል ሁኔታ ሶስቱ አመራሮች – ማለትም በለጠ ሞላ፣ጣሂር ኢብራሂምና ጋሻው መርሻ ለየብቻቸው ግን እጅግ በተናበበና በተጠና መልክ በጋራ ደግመው ደጋግመው ያስተጋቡት ይህ ምክንያት አልባ ግን ምክንያት ካለውም ምቀኝነት፣ቅናት፣ተንኮል፣ጥላቻ ብቻ የሆነው መንጋ በተንጨረጨረ ቅናታምነቱ የተነሳ የስድብ ውርጂብኝ ሊያወርድባቸው የመቻሉን ጉዳይ እንጂ  እነሱ በአመራራቸው እንከን እና ጥፋት ስለሰሩ እንዳልሆነ አድርገው  ነው ይዘው የቀረቡት።
ይህ ማለት በአጭሩ ከአንድ ባለትዳር ወንድ ጋር ስትማግጥ በሚስቱ የተያዘች ሴት በሁለታችን ፍቅር እርር ድብን ቅጥል ብላ ብዙ የምታወራብን ሚስቱ ቅናተኛ ምቀኛ ስለሆነች ነው ብላ ስትናገር እንደመስማት ያህል ማለት ነው።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን ) ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሬዚዳንቱ በለጠ ሞላ፣ቃለ አቀባዩ ጣሂር ኢብራሂም እና የፕሬዚዳንቱ ምክትል ዩሱፍ ኢብራሂም  ከብልይግና የተጨራቸውን የስልጣን ቅንጣቢን አፈፍ አድርገው በመውሰድ የተሾሙ የመንግስት ሹመኞች ናቸው።
ታዲያ በእነሱ መሾም የቀና የተናደደና ብሎም በምቀኝነት ወይኔ እኔ መቀመጥ በሚገባኝ የስልጣን ወንበር ተቀመጡ ብሎ የተቃወማቸውና የተቻቸው ይኖር ይሆን ብላችሁ ብትጠይቁ የምታገኙት ምላሽ በሶስቱ ላይ የቀረበው ጥያቄም ሆነ ትችት ወቀሳም ሆነ ውግዘት እናንተ የአማራ መሪ ናችሁ እኛን ምሩን ብለናችሁ እንዴት ሆኖ ነው  ያለአንዳች ድርጅታዊ ውሳኔ እኛን ሜዳ ላይ በትናችሁ ወደ ብልጽግና ሽምጥ የጋለባችሁት የሚል ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ነው ሲቀርብላቸው የነበረው እንጂ  ዛሬ ሶስቱ እየተቀባበሉ እንደገለጹት ምቀኝነት፣ቅናት፣ጥላቻና ምክንያት የለሽ መንጋነት አይደለም።
በለጠ ሞላ፣ጣሂር ኢብራሂምና ዩሱፍ ኢብራሂም የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ወይም የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አሊያም የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንኴን ሳይመክርበትና ብሎም በአብላጫ ድምጽ ሰጥቶበት ሳያሳልፈው ነው በራሳቸው ግለ ውሳኔ የተወረወረላቸውን የስልጣን ቅንጣቢን ቅልብ አድርገው በመውሰድ ማንም እንዳይናገረን ያሉት። ይህንን ሕገ ደንብ የጣሰን አሰራር ይህ ጸሐፊ ዛሬ ሳይሆን በወቅቱ – በመስከረም 2021 ላይ ግልጽ አድርጎ ደግሞ ደጋግሞ የገለጸው ሀቅ ሲሆን ጣሂር መሀመድ የድርጅቱ ቃለ አቀባይ ነኝ የሚለን ከአንድ ቀን በፊት በወዳጁ አዲስ ድምጽ ሚዲያ ላይ ቀርቦ አምኖ የገለጸው ሀቅ ነው።
« አዎን ካለብን ውጥረትና የድርጅት ሕገ ደንብ ክፍተት የተነሳ ጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ ማእከላዊ ኮሚቴውና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሳይመክረበት ነው የተሰጠንን ስልጣን የወሰድነው» በማለት ከገለጸ በኋላ « ማእከላዊ ኮሚቴው ግን ከተሾምን በኋላ የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የድርጅቱን መተዳደሪያ ሕገ ደንብ ጥሳችኋል ብሎ ውሳኔ አሳልፏል » በማለት በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ግልጽ የእይታና የአቌም ልዩነትን መደበቅ በማያስችል መልኩ ተናግሯል።
እናም የድርጅቱን ሕግና ደንብ ብንጥስም በእኛ ምኒስቴር መሆን ተናዶ የሚቃወም ምቀኛ ቅናተኛ በጥላቻ የተሞላ ምክንያት አልባ መንጋ ነው እንጂ  ሌላ ሰው መሆን የለበትም እያሉ ነው እንጂ  ይበልጥ ለምን ጠየቃችሁኝ በሚል ስሜት የተሳደቡት እንጂ  ጥፋተኞች ነንን ትንፍሽ ማለት አልፈለጉም።
👉  ፋኖን በተመከተ የአብን አመራር ያንጸባረቀው ምላሽ፦ 
በፋኖ ገዳይ ላይ ለቀረበለት ጥያቄ ጣሂር የመለሰበት መንገድ ሌላው ተመስገን ጥሩነህ ሆኖ ነው የመለሰው። ልክ ተመስገን ጥሩነህ ፋኖን የገለጸበት አገላለጽ ነው የተጠቀመው።
በቃ ምን አለፋችሁ ጣሂር የባጥ የቆጡን እየቀባጠረ የፋኖን መመታትን አስፈላጊነት የገለጸበትን ዙሪያ ጥምጥም ከመግለጽ…..ይልቅ በአጭሩ ልክ ተመስገን ጥሩነህ የተጠቀመበትን « አንዳንድ ፋኖ ነን የሚሉ ከድል በኋላ እራሳቸውን ፋኖ እያሉ የሚገልጹና በትግሉ ወቅት አንዳችም  ሚና ያላበረከቱ..» እያለ የገለጸበትን ቃል በቃል ጣሂር ተጠቅሞበት ከጋዜጠኛው ለቀረበለት በፋኖ ላይ እየተካሄደ ስላለው ዘመቻ ያለውን ምላሽና እይታን ሰጥቷል።
ይህ ማለት በጣሂር አይን በፋኖዎቻችን ላይ እየተደረገ ያለው ዘመቻ ተገቢ ነው -ፋኖ ትጥቅ መፍታት አለበት ብሎ የሚያምን እና በፋኖ እንቅስቃሴ ፍጹም የተበሳጨ መሆኑን ከዙሪያ ጥምጥም አገላለጹ መረዳት ይቻላል ማለት ነው። ግን ለምን ለሚለው እሱ ራሱ የሚመልሰው ይሆናል።
አብን በቅርቡ -ማለትም በያዝነው መጋቢት ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል። እንደነ ጣሂር እና ጋሻው  «በቃን ደክሞናል» በማለት ከድርጅቱ አመራር እንደሚነሱ ያላቸውን አቌም ፈንጥቀዋል። የተፈጸሙ ሕገ ደንብ ጥሰቶች ማስተካከያ ይደረግባቸውና የብልጽግና ባልስልጣን የሆኑት ከፓርቲው አመራርነት እና ከመንግስት ምኒስትርነት ስልጣን መካከል አንዱን መምረጥ እንዳለባቸው ውሳኔ ይተላለፍላቸዋል። ይህንን ሁሉ ጉድፉን አጽድቶ በአዲስ አመራር እራሱን አጠናክሮ መምጣት መቻሉ ጉዳይ ላይ ዛሬ የምንሰጠው መላምት ሳይሆን ከሳምንታት በኋላ የምናየው ሀቅ ስለሆነ እንጠብቃለን።
በጣሂር በኩል ግን እሱና መሰል ባልደረቦቹ በቃን ያሉ ስለመሆናቸው ፍንጭ ሰጥቷል። ያንን ካደረጉና በአንድ ግዜ የሁለት ጌታ ባሪያ አትሆንም የሚለውን ቃል ጥቅም ላይ በማዋል የምኒስቴርነት ስልጣናቸውን መርጠው የድርጅቱን ኋላፊነት ለድርጅቱ ከተው የዘገየ ግን ትክክለኛ እርምጃ ይሆንና ድርጅቱን መልሶ በማጠናከር ደረጃ  እንደ አስተዋጽኦ የሚቆጠር ይሆናል። ይህንን ሳያደርጉ ቀርተው እኛ ነን ትክክለኞቹና ሁለቱንም ስፍራ ይዘን የምንሾፍረው እኛ ነን ካሉ ግን ሰዎቹ በአማራ ትግል ላይ ትልቅ ሴራ ያነገቡ ሆነው ይወጣሉ።
ይህንን ካልን  በኋላ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት በለጠ ሞላ እና የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ኋላፊ ዶ/ር ቴውድሮስ ኋይለማሪያም ካስተላለፉት ውስጥ የሚከተለውን ቀንጭበናል።
👉  በለጠ ሞላ  
«… .. አማራነት የሚገለጸው አማራ በሚል የበዛ ጩህት አይደለም። የዛሬው ጩኸታም መንጋ ትላንት ወንድሞቻችንና መላው ህዝባችን ለህልውናው መጠበቅ ሲያደርግ የነበረውን ትንቅንቅ “የጠሚ አብይ አህመድን ስልጣን ለማስጠበቅ የሚደረግ ከንቱ ጦርነት” ሲሉት ነበር። ዛሬ የፋኖ ጠበቃ እኛ ነን ይሉናል።
አንዱ ለሠራዊቱ እንጀራ ሲያቀርብ ሌላው እንጀራ ይሸጥ ነበር፣ አንዱ በሬ ሽጦ መሳሪያ ሲገዛ ሌላው መሳሪያ ይሸጥ ነበር፣ አንዱ ሲሰጥ ሌላው ይቀማ ነበር….የሆነው ይሄ ነው….በዚህም በዚያም ድብልቅልቅ ያልን መደማመጥ የተሳነን ጯሂወች ነን! »
በለጠ ሞላ  የአብን ፕሬዚዳንት
 
👉 ዶ/ር ቴውድሮስ ኋይለማሪያም 
«……  ህዝባችን  አላዋረደንም። የትንሽ የትልቁ መዛበቻ ያደረግነው ፣  የውርደት የሀፍረት ማቅ ያከናነብነው እኛው ነን። በህዝብ ስም የምንነግድ ፣  መልሰን ሌባ ጣታችንን ወደ ህዝብ የምንጠቁም እኛ ነን።  ሁሉን አዋቂ ፣ ሁሉን ተቺ ፣ በሁሉ አኩራፊ እኛው ነን። ህዝባችን ተሳስቶ ከሆነ  በገርነቱ የማይገባንን ክብር አትረፍርፎ በመስጠቱ  ብቻ ነው።
ህዝባችን አልከበደንም። ከህልቆ መሣፍርት ጠላቶቹ  በላይ መርግ ሆነን ጫንቃውን የሰበርነው እኛው ነን። መጀመሪያ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ወርደን በራሳችን እንቁም። ለስህተታችን  የጦስ ዶሮ መፈለግ ፣ ለጥፋታችን  ክሬዲት መሻት የትም አያደርስም።     ሰከን ብለን ለጥፋቱም ለልማቱም በግልም በቡድንም የራሳችንን ድርሻ እንመርመር። ከራስ መጋፈጥ ከባድ ቢሆንም ጨከን ብለን እንሞክረው»
ዶ/ር ቴውድሮስ ኋይለማሪያም የአብን የውጭ ጉዳይ ኋላፊ
በድርጅቱ ውስጥ እንደ ዶ/ር ቴውድሮስ አይነት ኋላፊነትን ወሳጅና ብሎም ወደ ውስጥ ተመልካች ድርጅቱን  ይታደጉታልና ወደ ፊት ለፊት ወጥተው ትግላቸውን ማቀጣጠል ይጠበቅባቸዋል። በነገራችን ላይ ዶ/ር ቴውድሮስ ኋይለማሪያም በአዲስ አበባ ስልጣን ተሰጥቶት አልቀበልም ብሎ እምቢ ያለ አመራር መሆኑን ላስታውስ እወዳለሁ።
አብን በቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤ  እራሱን ከምእንግስት ሹመኞች አጽድቶ ነጻ ድርጅትነቱን አስጠብቆ ይወጣል ወይንስ ድርጅቱን ለመንግስት አገልጋይ ሹመኞች አስረክቦ ይወጣል የሚለውን ምላሽ እኩል የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic