>
5:13 pm - Sunday April 18, 2038

የመንጋ ትርጉም ላልገባቸው....!!! (አሳዬ ደርቤ)

የመንጋ ትርጉም ላልገባቸው….!!!

አሳዬ ደርቤ

በጦርነቱ ወቅት የአብን አመራሮች ሕዝብን ሲያስተባብሩ ጠሚው ደግሞ ጦሩን ሲመሩ ነበር፡፡ እኛም ከግል አቋም ይልቅ የወገንን ጥቅም በማስቀደም ከአብን በተጨማሪ የብልጽግና ደጋፊ ሆነን የድርሻችንን ስናበረክት አሁን የሌላ ድርጅት ተከፋይ ያደረጉን ሃይሎች የዐቢይና የአብን ካድሬ አድርገው ባዶ ኪሳችንን በገንዘብ ሲሞሉት ነበር፡፡
በዘመቻው ጅማሮም ‹‹ይሄን ነቀርሳ ድርጅት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለን እንጣለው›› የሚል አገራዊ ጥሪ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ወራሪው ሃይል ራያ በደረሰ ቅጽበት ‹‹አራት ኪሎን መመኘት የሚያመጣውን ጉዳት ካየህ ይበቃኻል›› ብለው ምሕረት ካደረጉለት በኋላ የሕዝብ ስጋት ሆኖ እንዲኖር ፈቅደውለት ሲመለሱ ‹‹የተዘረፍነውን ሳናስመልስ አንመለስም›› ሲሉ የነበሩ የአብን አመራሮች አብረው መመለሳቸው የሚያስገርም አይሆንም፡፡
እኛ ደግሞ እንደነ ናትናኤል ‹‹በዚህን ያህል ደሞዝ ካድሬ ሆኜ ላገለግል ቃል እገባለሁ›› የሚል የኮንትራት ውል ላይ ያኖርነው ፊርማ ባለመኖሩ መከላከያ ሠራዊትና መንግሥት ባለባት አገር ላይ አፋርና ሰቆጣ ዳግም ሲወረር ተመልክተን ወደ ቅዋሜ መመለሳችን ዜጋ ባይስብለን እንኳን መንጋ የሚል ታርጋ የሚያሰጠን አይሆንም፡፡
ምክንያቱም የመንጋ መገለጫው እንደ እስስት በሚለዋወጥ ፖለቲካና ፖለቲከኞች እየተመሩ አንዲት መፎክር እየደሰኮሩና የተሸመደደ መዝሙር እየዘመሩ መጎዝ እንጂ እየጠየቁ መጓዝ አይደለም።
ይሄን ብዬ ወደ አብን ስመለስ ትናንት ልተቻቸው የቻልኩት በጦርነቱ ላይ ተሰውተው የቀሩ ይመስል የሚወክሉት ሕዝብ እሪታና ለቅሶ ምድሩን ሲያናውጥና በንጹሐን ላይ ጭፍጨፋ ለፈጸሙ አመራሮች ይቅርታ ሲሰጥ ጸጥ ለጥ ብለው ሲጓዙ በማየቴ ነው፡፡
➔አብረዋቸው የተሾሙ የኦነግ አመራር የአድዋን ድል ድልድይ ስር ሲጥሉት ‹‹ዳግማዊ አድዋን እናከብራለን›› ሲሉ የነበሩ የእኛው ሹማምንቶች ግን መግለጫ ለማውጣት ሲሰንፉ በመታዘቤ ነው፡፡
➔አብንን የተቸሁት ለቀብር የታሰበው ድርጅት ለድርድር ሲጋበዝ፣ ጌታቸው ረዳ ‹‹ፋሽሽቱ መንግሥት›› ማለቱን ትቶ በአማራ ኤሊት ላይ ጦሩን ሲመዝዝ፣ በወለጋ የተጨፈጨፉ ከ200 በላይ አማራዎች አስከሬን ወደ መቃብር ሲጋዝ፣ በመርሕ የለሽ የተግማማ ፖለቲካ ውስጥ እራሳቸውን አስማምተው ከመንግሥት ጋር ሲሽኮረመሙ በመታዘቤ ነው፡፡
➔አብኖች ላይ ብእሬን ያነሳሁት ሹመት የሰጣቸው መንግሥት ፋኖን ኢ-መደበኛ ሃይል ብሎ ሲፈርጅ ‹‹ኖ›› በማለት የተቃወሙትን የአማራ ብልጽግና አመራሮች እያስወገደ ፋኖን ለመልቀም የተስማሙትን ሲሾም…  የራያን ሕዝብ ከወራሪ እጅ መጣሉ አንሶ የወልቃይት ጥያቄንም ከስጋት ውስጥ ሲጥል… ለአማራ ሕዝብ ለመሞት የተዘጋጀ ፋኖ በአማራ እጅ ሲገደል፣ የብልጽግና የሃይል አሰላለፍ ከብአዴን ወደ ትሕነግ ሲያጋድል… እልፍ አእላፍ ሕዝብ ሲፈናቀል… ብሎም የአማራ ስጋት ከቀን ወደ ቀን ሲያይል…. መልስ ሆነው ሊገኙ ቀርቶ ጥያቄ የማንሳት አቅም አጥተው ሲልፈሰፈሱ ስላየሁ ነው፡፡
ይሄንንም ትችት በቀናነት ከመቀበል ይልቅ መንጋዎች፣ ምቀኞች፣ ተከፋዮች፣ ጩኸታሞች… በሚል ፍረጃ አጣጥለው ‹‹በስሌት እየተመራን የጀመርነውን የድል ጉዞ በስሜት እየደነፋችሁ አታበላሹብን›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ እኛም ይሄን ጥያቄ ተቀብለን ድምጻችንን ከማጥፋታችን በፊት እንዲህ ማለት እንሻለን፡፡
‹‹አብን በዚህ መልኩ ከቀጠለ በብልጽግና ጉባዔ ላይ ብአዴን ነጥብ ጥሎ እንደወጣው ሁሉ… አብን ደግሞ ወደ አገራዊ ምክክሩ አጀንዳውን ይዞ ከገባ በኋላ ባዶ እጁን ይወጣል፡፡ ያኔ አማራን ሊታደግ ቀርቶ እራሱን ማስቀጠል ተስኖት ዞናዊ ፓርቲ ያቋቁማል፡፡ ወይም ደግሞ ይከስማል! ማርክ ማይ ወርድ!”
Filed in: Amharic