>
5:21 pm - Friday July 21, 6305

በሕልውና አደጋ ውስጥ ካለው ብልጽግና ለውጥ መጠበቅ " ላም አለኝ በሰማይ... !" እንዲሉት ተረት ያለ ነው...!!! (አድማሱ አብርሃም)

በሕልውና አደጋ ውስጥ ካለው ብልጽግና ለውጥ መጠበቅ ” ላም አለኝ በሰማይ… !” እንዲሉት ተረት ያለ ነው…!!!
አድማሱ አብርሃም

የመንግስት ኃላፊነቱን መወጣት ያልቻለው ብልጽግና የምትፈልገውን ሁሉ እየመረጠ እያጠነፈፈ ይነግርሃል። የሚነግርህ ነገር ሁሉ መስማት የምትፈልገውን እንጂ መፍትሄውን አይደለም። የሚሰራውና የሚናገረው ነገር የተራራቁበት በቁሳዊ ልማት ወጥመድ የሚሰቃይ ፓርቲ ቢኖር ብልጽግና ነው። ብልጽግና የኢሕአዴግ ወራሽ ድርጅት ነው። ስም ከመቀየር ውጪ ምንም ልዩነት የላቸውም። መንግስትና ፓርቲ ተደበላልቀው የመንግስት ሚዲያዎችን እያጨናነቁት ነው። መሬት ላይ ያለውእውነታ ፣ የብልጽግና አመራሮች የሚያወሩትና የብልጽግናው መንገድ የተባለው እጅግ የማይገናኙ የተራራቁ፣ ሃራምባና ቆቦ ናቸው ። የሕወሓት አመራሮችም ይሁኑ የኦሕዴድ አመራሮች አንድ አይነት ከአንድ ባሕር የተቀዱ አስተሳሰባቸው በዘር ፖለቲካ የተቀኘ ነው። ብልጽግና ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ሕወሓት ኢሕአዴግ በደንብ ጠፍፎ የሰራቸው በመሆኑ ሕወሓት ኢሕአዴግ ሲሰራው የነበረውን ነገር ሁሉ ይደግሙልሃል፤ ብልጽግናዎች ሲደግሙልህ ታዲያ አንድ ከሕዝቡ ልብ ያገኙት እውነትን ለሽፋን ይጠቀሙበታል ኢትዮጵያዊነት ።
ብልጽግና በሆዳቸው የሚገዙ ፖለቲከኞችንም የሚፈለፍለው በሕወሓት/ኢሕአዴግ ቀመር ነው። ብልጽግና አመራሮቹ በኔትወርክ ተደራጅተው በሌብነትና በውሸት ላይ ስለተመሰረቱ ይህን ኔትወርክ ለማፍረስ ከባባድ ጥረቶች ስለሚተይቁ ለማፍረስ ከብዶት እየተሰቃየ ነው። ከታጣቂ ሃይሎች ጀምሮ እስከ ማሕበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ድረስ የብልጽግና አመራሮች የጥቅም ኔትወርክ በመዘርጋት ለሃገር የማይበጅ ትልቅ ስሕተት ውስጥ ከመዘፈቃቸውም በላይ ስልጣናቸውን ሃገርን ለማፍረስ እየተጠቀሙበት ነው።
የብልጽግና አመራሮች ከአባታቸው ሕወሓት/ኢሕአዴግ የወረሱትን የዘረፋ ስራ በመተግበር ሚስቶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በሕገወጥ ንግድ ውስጥ አሰማርተው በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የሃገርን ኢኮኖሚ መቀመቅ ከተውታል። የውጪ ምንዛሬ በሕገወጥ መንገድ ከማዘዋወር ጀምሮ በጉምሩክ በኩል የሚያልፉ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ለሕጋዊ የንግድ ስራዎች ትልቅ ጋሬጣ ሆነዋል። ይህን የኢኮኖሚ አሻጥር በማስፋት ከታጣቂ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር በነዳጅና በማእድን ኮንትሮባንድ ላይ ተሰማርተዋል። እንዲሁም በርካታ ወንጀሎችን ይሰራሉ ያሰራሉ፤ ከዚህም አልፈው የሃገር ቅርስ አውጥተው ይሸጣሉ ያሻሽጣሉ። ባንኩም ታንኩም አይሮፕላኑም መርከቡም በጃቸው በመሆኑ የሚጠይቃቸው አካል የለም።
የሃገሪቱ መሪዎች የሚያጨበጭብላቸው እንደሚፈልጉ የተረዱት የብልጽግና አመራሮች ያላቸውን ኔትወርክ በመጠቀም ለሃገሪቱ መሪዎች ውዳሴና ጭብጨባ የሚለግሱ ዜጎችን በጥቅም ገዝተዋል። በተለያዩ መንገዶች የተገዙ ጥቅመኞች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚከፈላቸው ከየመንገዱ ጀምረው እስከ ማሕበራዊ ሚዲያ የተነገራቸውን እየደጋገሙ ሲያጨበጭቡ እውነታን የነገራቸውን ሲዘልፉ ይውላሉ።
የብልጽግና አመራሮች የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ የሚስተካከላቸው ምንም የለም። ሁሉም ሚኒስትሮች ካለምንም ፍርሃት በፍረት ያልተደረገውን ተደረገ ያልተሰራው ተሰራ የሚል የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ በአለቆቻቸው ዘንድ ክብርና ሞገስን ለማግኘት በሚያደርጉት ሩጫ የሃገሪቱን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ እሴቶችን አውድመዋል። እነዚህ የብልጽግና ሚኒስትሮች በድፍረት በሚያቀርቡት ሪፖርት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ስም ነግደዋል። ለዜጎች ያልተደረገውን እንደተደረገ በማውራት ያልተመዘገበ እድገት እንደተመዘገበ አድርገው አቅርበው አሳስተዋል። ሃገርን ገለዋል።
የሕግ የበላይነትን በብልጽግና ዘመን መመኘት አይቻልም። ፖለቲከኞች በፍርድ ቤት ጉዳዮችና በፍትሕ አካላት ስራዎች ላይ እጃቸውን በማስገባት የሕግ ጥሰት እንዲፈጽሙ ስለሚያደርጉ የሕግ የበላይነት እንዳይኖር ሆኗል። ሌላው የሃገሪቱ የሰላምና የደሕንነት ጉዳይ ነው። ይህ የሰላምና የደሕንነት ጉዳይ ከዛሬ ነገ መሻሻልን ያሳያል ተብሎ ቢጠበቅም ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት ሄዷል። በአፋርና በአማራ በትግራይ ያሉ ጦርነቶችና የጦርነት ውጤቶች አሁንም ድረስ ቀጥለዋል። በኦሮሚያ ክልል መንግስት ከሚያስተዳድረው ይልቅ የኦነግ ጦር የሚያስተዳድረው አከባቢ እየበለጠ ነው። እንዲሁም በቤንሻንጉል ጋምቤላና ሌሎች አከባቢዎችም የሰላምና ደሕንነት ጉዳዮች ከመፈታታቸው ይልቅ እየተወሳሰቡ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ስሕተት ደግሞ ብልጽግና የሚከተለው የደከመ ፖሊስና አመራሮቹ የሚሄዱበት የሴራ ፖለቲከ ውጤት ነው። እነዚህና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ብልጽግናን የሕልውና አደጋ ውስጥ ከተውታል።
ስለ ብልጽግና ፓርቲ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። ብልጽግና ፓርቲ በፍጹም ራሱም ማጥራት የማይችል ለሃገር አደገኛ የሆነ ፓርቲ ነው። ከሕወሓት ሲንከባብለ ከመጣ ችግር ጋር አብሮ የሚንከባለለው በሕልውና አደጋ ውስጥ ካለው ብልጽግና ለውጥ አገኛለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ በሃገር ላይ ትልቅ ስሕተት እየሰራ ነው።
Filed in: Amharic