>
5:26 pm - Friday September 15, 5279

የመንፈስ ረሃብ! (ጌታቸው አበራ)

የመንፈስ ረሃብ!

  ( ጌታቸው አበራ)


‘ዶላር’ ምን ያደርጋል – ያለ አቅሙ ገዝፎ፣

ምግብ ምን ያደርጋል – ሞልቶ ተትረፍርፎ፣

ዲግሪ ምን ያደርጋል – ስም ብቻ ለጥፎ፣

የመኖሬን ትርጉም – በጥያቄ አስይዞ፣

የሰራ-አካላቴን – አንደ ብል መዝምዞ፤

የመንፈስ ረሃብ ነው-የያዘኝ ሰቅዞ!

የተፈጥሮ ጸጋ – የውበት ማኅደር፣

የአምላክ ችሮታ – በረከትስ ነበር፤

ታድያ ምን ያደርጋል – ወይ አለመታደል፣

የስንዴውን ማሳ -እንክርዳድ ወሮታል፤

የአድማስን ውበት-ጽልመቱ ጋርዶታል!

 

..ይታየኛል ከሩቅ .. በሃሳብ መንገድ ጉዞ፣

የሀገሬ መሬት ትዝታውን ይዞ፤

ውበትን ያዘለች ፀሐይ ውጣት-ጥልቀት፣

ሰማይና ምድር የሚሳሳሙበት፤

ያ!ጋራው፣ ተራራው፣ ሜዳው፣ ሸንተረሩ፣

የህይወት ምንጭ ወንዞች- እስትንፋስ አየሩ፣

ብርሃን፣ ጨለማ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣

“እዚያ” ብቻ ያሉ መስለው የሚታዩት።

 

    ይሰማኛል ከሩቅ… ህብረ-ድምጽ ሙዚቃ፣

    የተረበሸውን መንፈስ እሚያነቃ፤

    ሆያ ሆዬ ..አስዮ.. ባለዱላ ልጆች፣

    ቄጠማ የያዙ ያበባ ሸጌዎች፣

    አሸበል ገዳዬ፣ የሸበሏ አደይ..፣

    ሳዱላዬ ነይ ነይ-የበላይ ነሽ ወይ፣

    አለው መላ መላ..ኤቦ ኤቦላላ፣

    ወሰላ፣ ወሰሰላ.. ጭፈራ ጨምበላላ፤

    የሰላሌ ዜማ .. የአፋር የሱማሌ፣

    የትግራይ ከበሮ .. የወለጋ የባሌ፣

    የሐመር ህብር.. የጋምቤላ ቶም ቶም፣

    የዶርዜ ቅላፄ .. ህብረ-ዜማ ጣዕም፤

    ክራርና ዋሽንት፣ መሰንቆ በገና፣

    የመንፈስ ምግቦቹ – የህሊና ቃና፣. . .

    መቋሚያ ጸናጽል. ከበሮ ድም ድምታ፣

    ምስጋና ማቅረቢያ ‘ክበር የኛ ጌታ’!

    መኖር ‘ባይታገድ’- ቢኖር ኖሮ ሰላም፣

    ሀገሬ ነበረች – የዚህ ሁሉ ሃብታም!

    ..ባይታረድባት-እንደ በግ የሰው ልጅ፣

    ህይወትን ፍለጋ-እኔስ የትም አልባጅ፤

    ..ሰው በቁም አቃጣይ-ባይኖር አረመኔ፣

    ከእናት አገር ወዲያ እኔማ ለምኔ?!

    ..ጥምቀተ-ባህርን፣ታቦትን ደፋሪ፣

    ሰላማዊ ዜጎች፣ምዕመን አሸባሪ፣

    ታቦት ሸኚ ገዳይ-እርኩስ ባይኖርባት፣

    ኢትዮጵያስ ነበረች!ሠርክ እሚኖርባት!

መጋቢት 2014 ዓ/ም

   (ማርች 2022)

Filed in: Amharic