>

ግልጽ መልእክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ...!!! (አሳዬ ደርቤ)

ግልጽ መልእክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ…!!!

አሳዬ ደርቤ

‹‹ጩኸታችሁን በማቆም የአማራ ሕዝብ እፎይታ እንዲገኝ አድርጉት›› የሚል መልዕክት ለአማራ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ማስተላለፍዎን ሰማሁ፡፡ እናም ለአፍታ ያክል አማራ ሆነው የሕዝቡን ሰቆቃ ያዳምጡበት ዘንድ ጆሮየን አውሸዎት፣ አንደበትዎን በመውሰድ እንዲህ ልልዎ ወደድኩ፡፡
ውሃን የሚያስጮኸው በውስጡ ያለው ድንጋይ ነው፡፡ ከጥቃታችን ጋር ሲነጻጸር ጩኸታችን ኢምንት ነው፡፡ ከፈሰሰው ደማችን ጋር ሲወዳደር እንባችን እና ለቅሷችን ምንም ነው፡፡
.
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- እኛ እኮ የምናለቅሰው የእርስዎ መንግሥት ሊጠብቃቸው ቀርቶ አጀንዳ ሊያደርጋቸው ያልቻሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትኩስ አስከሬኖችን ታቅፈን እንጂ ከመቶ ዓመት በፊት የተፈጸመብንን ግፍ እያስታወሰን አይደለም፡፡ እኛ እኮ ስንጮህ የነበረው ‹‹ኖ ሞር›› እያልን እንጂ የሆነን ብሔር ‹‹ዳውን ዳውን›› እያልን አይደለም፡፡
ለመሆኑ ኦነግ ሸኔ የአማራ ንጹሐንን የሚጨፈጭፈው የእኛ ጩኸት እያበሳጨው ነው እንዴ? ትሕነግ ከአማራም አልፎ አፋርን የሚያወድመው የእኛ ድምጽ ደሙን እያፈላው ነው እንዴ? ሕዝቡን ከአደጋ ሊታደግ የተደራጀው ፋኖ ኢ-መደበኛ ሃይል ተብሎ በየስፍራው የሚሳደደውና የሚገደለው በአማራ አክቲቪስቶች ጩኸት የተነሳ ነው እንዴ?
በዚያ ላይ ደግሞ የአማራ እሪታና ኡኡታ የእርስዎን ጆሮ አግኝቶ የሚያውቀው መቼ ነው? አሸባሪው ሃይል ጣርማ በር ደርሶ አራት ኪሎ ላይ መዛት እስኪጀምር ድረስ የአማራ እናቶች ዋይታ ሊያሳዝንዎት ይቅርና የፓርቲዎን ድግስና ፌሽታ ማደብዘዝ ችሎ ነበር እንዴ?
እናስ በሰላማዊ መልኩ መኖር ሲጀምር የመንግሥት አመራሮች ባደራጃቿውና ይሁንታ በቸሯቸው አሸባሪዎች ጥቃት የሚንገበገበውን፣ ተደራጅቶ እራሱን መካለከል ሲጀምር ደግሞ ኢ-መደበኛ ተብሎ በመንግሥት ጥይት የሚደበደበውን ሕዝብ ችግር በመፍታት ፈንታ የጥቃቱን ምክንያት ከአክቲቪስቶች ጩኸት ጋር ማቆራኘት ለምን ፈለጉ?
አንድ ነገር ልንገርዎ…
በየትኛውም መልኩ ቢሆን የአማራ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች በእርስዎ አንደበት ሊሞገሱ እንጂ ሊወቀሱ የተገባ አይደለም፡፡
የአገሪቱ ጦር በከሃዲያን ብረት ሁለት ጊዜ ሲመታ ‹‹መከላከያን ይቀላቀሉ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ፣ የዲጂታል ወያኔዎችን የሳይበር ዘመቻ ሲደመስሱ፣ ከወገናቸው ጥቃት ይልቅ የአገራቸውን ቀጣይነት አስቀድመው ‘ኖ ሞር’ እያሉ ሲጮሁና ዶላር ሲለግሱ፣ የፓርቲዎ ደጋፊ ሆነው የእራሳቸውን ፓርቲ ሲያፈርሱ…. የከረሙ የአማራ አክቲቪስቶችንም ሆነ ፖለቲከኞችን መውቀስ የሚችለው ጌታቸው ረዳ እንጂ እርስዎ አልነበሩም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አብዛኛው አማራ በእርስዎ መንግሥት ተስፋ መቁረጡን ሲረዱ የህውሓትን ፍረጃ ተረክበው የአማራ ልሂቃንን እና ባለሃብትን ለመወንጀል በቁ፡፡ በመንግሥት ቁማርተኝነት እና ዳተኝነት መቀመጫ ያጣውን ሕዝብ በሶሻል ሚዲያ ጩኸት ሊያሟክኩት ከጀሉ፡፡
የሕዝብ ሚዲያዎችን አፍነው፣ ተጠያቂነትን አምክነው፣ በሕግ ፈንታ በሃይል የምትተዳደር አገር እውን አድርገው፣ የአማራን እልቂት ከማሳ ጉብኝት ያነሰ አጀንዳ አድርገው…. ወገኖቻችንን ሰለባ ሲያደርጉ መክረምዎ አንሶ ‹‹ድምጻችሁን በማጥፋት አማራን ታደጉት›› የሚል ጥሪ አቀረቡልን፡፡ ይሄም በሌላ ቋንቋ ሲገለጽ መንግሥቴን መቃወም እስኪቆም ድረስ አማራን ማውደም ይቀጥላል›› እንደማለት ነው፡፡
እኔ እምልዎት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ‹‹ዳውን ዳውን ነፍጠኛ›› የሚለውን የአዲስ አበባን ዩኒቨርስቲ ጩኸት በፈገግታ እያዳመጡ ፍትሕን በሚጠይቁ ድምጾች የሚቆጡ እስከ መቼ ድረስ ነው? የአማራን እልቂት እንዳልሰማ እያለፉ ጩኸቱን የሚያወግዙት፣ የሚፈስሰውን ደም ችላ ብለው እንባን የሚከለክሉት ይሄን ሕዝብ ምን ያህል ቢጠሉት ነው?
ፋኖን እየበተኑ ከወሬ ያለፈ ተግባር እንፈጽም ዘንድ የሚመክሩን፣ በዞን የሚሸነሽኑ አመራሮች እየሾሙ አንድነታችንን እንዲናጠናክር የሚነግሩን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን የምታፈናቅል አገር ከፈጠሩ በኋላ ሕዝቡ የተራበው በስንፍናው የተነሳ መሆኑን የሚያስረዱን፣ በሕገ መንግሥትና በመንግሥት ታዛ ስር በተጠለሉ ሃይሎች የሚፈጸመው ጥቃት ዋነኛ ምንጩ  ጩኸት መሆኑን የሚነግሩን የማሰብ አቅማችን ምን ያህል ወርዶ ቢታይዎት ነው?›› ብዬ ከጠየቅኩ በኋላ የእራስዎን ምክር ወደ እርስዎ በመመለስ የህውሓትን ያህል የእፎይታ ጊዜ ይሰጡን ዘንድ እለምንዎታለሁ፡፡
Filed in: Amharic