>

ከዛሬ 34 ዓመታት በፊት የ‹‹ናደው›› እዝ እና ኣፍአበት...!!!! (ልኡል አምደጽዮን )

ከዛሬ 34 ዓመታት በፊት የ‹‹ናደው›› እዝ እና ኣፍአበት…!!!!
ልኡል አምደጽዮን 

ሻዕቢያ [መጀመሪያ በብ/ጀኔራል ታሪኩ ዓይኔ፣ በኋላ ደግሞ በብ/ጀኔራል ውበቱ ፀጋዬ ይመራ በነበረው] በ‹‹ናደው›› እዝ ላይ ጠንካራ ጥቃት ከፍቶ የሞት የሽረት ትግል በማድረግ አፋቤት (ኣፍዓበት)ን የተቆጣጠረው ከዛሬ 34 ዓመታት በፊት (መጋቢት 9 ቀን 1980 ዓ.ም) ነበር፡፡ 
ብዙ ሺ ኢትዮጵያውያን የሞቱበትና የቆሰሉበት እንዲሁም ቢሊዮን ብሮች የፈሰሱበት የ‹‹ቀይ ኮከብ አብዮታዊ ዘመቻ›› ያለድል ከተጠናቀቀ በኋላ በውድቀቱ ምክንያት እርስ በእርስ መወነጃጀል ተጀመረ፡፡
የዘመቻው ጽሕፈት ቤት ኢንስፔክሽን መምሪያ ‹‹ስለጉዳዩ ማጣሪያ/ግምገማ አድርጌያለሁ›› ባለው መሰረት የ21ኛው ተራራ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ውብሸት ማሞ ተረሸኑ፡፡ የክፍለ ጦሩ 47ኛው ብርጌድ አዛዥ የነበሩት ሌተናንት ኮሎኔል ስለሺ አስፋው ማዕረጋቸውን ተገፍፈው ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ የ‹‹መብረቅ›› እዝ አዛዥ የነበሩትና በኋላ በጀኔራሎቹ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት (1981 ዓ.ም) ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ብ/ጀኔራል (በኋላ ሜ/ጀኔራል) ቁምላቸው ደጀኔ የቁም እስረኛ ሆኑ፡፡
‹‹በኅዳር ወር 1980 ዓ.ም በናደው እዝ ግንባር ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ናቸው›› የተባሉትና የእዙ ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጀኔራል ታሪኩ ዓይኔ የካቲት 7 ቀን 1980 ዓ.ም ተረሸኑ፡፡ የ‹‹መክት›› እዝ ዋና አዛዥ ብ/ጀኔራል ከበደ ጋሼ ደግሞ ማዕረጋቸው ተገፎ ያለጡረታ ከሰራዊቱ ተሰናበቱ፡፡
ብ/ጀኔራል ታሪኩ ዓይኔ ከተገደሉ ከአንድ ወር በኋላ፣ መጋቢት 7 ቀን 1980 ዓ.ም ሻዕቢያ በናደው ዕዝ ላይ የተጠናከረ ማጥቃት ሰነዘረ፡፡ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ፣ መጋቢት 9 ቀን 1980 ዓ.ም ሻዕቢያ የናደው እዝን ጠንካራ ይዞታ በማስለቀቅ የአፋቤት (ኣፍዓበት) ከተማን ተቆጣጠረ፡፡ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሰራዊትም ወደ ከረን አፈገፈገ፡፡ ናደው እዝ በሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ግንባር ግዙፍ የሰው ኃይልና የመሳሪያ ክምችት ነበረው፡፡ እዙ ሲሸነፍ መሳሪያው ሁሉ በሻዕቢያ እጅ ገባ፡፡
የቀን መርዘምና ማጠር ካልሆነ በቀር ሻዕቢያ አፋቤት ላይ የተጎናፀፈው ድል ሙሉ ኤርትራን ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ዘመቻ ትልቅ ኃይል/ሞራል እንደሚሆንለት ግልፅ ነበር፡፡
Filed in: Amharic