>

ግልጽ መልእክት ለፕሮፌሰሩ...!!! (አሳዬ ደርቤ)

ግልጽ መልእክት ለፕሮፌሰሩ…!!!

አሳዬ ደርቤ

*… እርስዎ አመራር ሆን ተብሎ በአማራ ክልል ውስጥ የተፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ዝቅ ማድረግ፤ ሲሻቸውም በዜሮ ማባዛትን የተካኑ ካድሬዎችን በስርዎ ኮልኩለው ስለ ትምህርት ጥራት እየደሰኮሩ ወንበር ማሞቁ ከድሀ ህዝብ የተሰበሰ የግፍ ደም-ወዝ እየበሉ መኖሩ ሰላም ይሰጥዎታል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፤ ሲጀመር በዲሽቃ እና በሙዚቃ ያጠናን ተማሪንስሐ በእኩል ነጥብ እለፍ ማለትስ ተገቢ ነው…???
 በከባድ መሣሪያ ተኩስ እየታመሱ እና በኩራዝ ጭስ እየተጨናቦሱ እንደ ነገሩ አንብበው ለፈተና የቀረቡ የአማራ ክልል ተማሪዎች  ውጤት ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ ሆን ብሎ እንዲሳሳት መደረጉ ተረጋግጧል፡፡ ተፈታኞቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ ፈንታ ክልልን እና ሥምን መሠረት አድርገው ውጤት በሚተምኑ ከንቱዎች እጅግ አስነዋሪ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል፡፡
እናም ለተፈጸመው አሳፋሪ ድርጊት ተቋሙን እንጂ እርስዎን በዚያ ልክ አውርጄ መወንጀል ባልሻም እንደ አንድ ዜጋ ግን ለሚከተሉት ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ እንዲሰጡ እጠይቃለሁ፡፡
➔እንደ ኮንዶሚንየም እጣ የተቋሙን ቴክኖሎጂ በመጥለፍ የተማሪዎችን ውጤት በእነሱ ችሮታ ላይ እንዲመሰረት አድርገው በአማራ ክልል ውስጥ የተፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ዝቅ ያደረጉ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች… ለሌሎች ደግሞ የፈተና መልስ ሲሰጡ እንደነበረው ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ ውጤት የማይሰጡበት ምክንያት አይኖርም፡፡
ስለዚህ ቅሬታ ባቀረቡ ተማሪዎች ውጤት ፈንታ የሁሉም ተማሪ ውጤት እንደገና እንዲታረም ማድረግ ይጠበቅብዎታል፡፡
➔ሲቀጥል ደግሞ የተማሪዎች ውጤትን ከፍ እና ዝቅ አድርገው በማዛባት ትውልዱ ላይ ጥቃት የፈጸሙ የተቋሙ ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ የማጣራት ሥራ ከተሠራ በኋላ እርምጃ ወስደው ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባዎታል።
➔በመጨረሻም በዲሸቃ እና በሙዚቃ ድምጽ ሲያጠኑ የከረሙ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡበትን ነጥብ ተመሳሳይ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተረድተው ማስተካከያ እንዲያደርጉ እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ፡፡
ይሄን ማድረግ ካልቻሉ ግን በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የተፈጸመው ይህ አስነዋሪ ድርጊት የተማሪዎቹን እጣ ፈንታ የሚያበላሽ ብቻ ሳይሆን የእራስዎን ሥም እና ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የሚያጠለሽ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
Filed in: Amharic