“ምን አገባኝ!” እና “ምን አሳጣኝ ብዬ!” ያሳጡን ዕድሎች
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ባለቤት እንደሆነች ይታመናል፡፡ በአግባቡ የሚያስተዳድር ጥሩ መንግሥት ካለ የሕዝብ ብዛት በራሱ መጥፎ አለመሆኑ ይታሰብልኝና በአፍሪካ ምድር ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ውስጥ እንደኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ሽቅብ የተተኮሰ ሀገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም – የለም ማለቴ ግን አይደለም፤ ቢጠና ሊኖር ይችላል፡፡ የኛ ግና ለየት ባለ መንገድ ቁጥራችን ጨምሯል፡፡ መጨመሩ መጥፎም ደግም ጎን አለው – ይህ የሚወሰነው ደግሞ እንደመንግሥቱ ዓይነት ነው፡፡ ለምሣሌ ቻይና (1.402 ቢሊየን)የሕዝብ ብዛቷ ችግር እንዳልሆነባት ይወራል፡፡ ችግሩ በርግጥም የሚሠሩ እጆች አንሰው የሚበሉ አፎች ሲበዙ እንጂ የሕዝብ በዛት ብቻውን ችግር አይሆንም፡፡
ጎረቤቶቻችን እነሱዳን (43.85ሚ)፣ ኬንያ (53.77ሚ) እና ጂቡቲ (988,002) ባለፉት አራትና አምስት አሠርት ዓመታት የጨመሩት ከኛ ጋር ሲነጻጸር በተለይ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ከነባራዊው ሁኔታ ተነስቼ ስገምት ታዲያ የኛ ብዛት ወደመረገሙ ሳይጠጋ አይቀርም፡፡ የእርግማው ምንጭ ግን የሚነሱት መንግሥታት የአስተዳደር ችሎታ ማጣት ነው፡፡
ፕሌቶ በአገር አስተዳደር ረገድ የሕዝብ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሲገልጽ የተማረውና የነቃው ወገን አገርን በማስተዳደር ዘርፍ ኃላፊነቱን ሲወጣ በመጠኑ የተማረው ሀገርን በመጠበቅ፣ ብዙ ያልተማረው ደግሞ በግብርና ምርት በመሣተፍ አንዲትን ሀገር አቅፎና ደግፎ እንደሚይዝ ወይም መያዝ እንደሚኖርበት ያብራራል፡፡ እኛ ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ የተማረው ከአስተዳደር ሲሸሽ ያልተማረውና ፊደልን ለይቶ ያልቆጠረው ወደፖለቲካው እየገባ ሀገርን ሲያተራምስ እናያለን – “የተገላቢጦሽ አህያ ወደሊጥ ውሻ ወደግጦሽ” እንዳለው ኃይሉ ገ/ጊዮርጊስ (ገሞራው)፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ስንመረምር በርግጥም ኢትዮጵያ በመቶ ሚሊዮን ከሚገመተው ሕዝቧ ሀገርን በትክክል የሚመራ ሰው አጥታ ሳይሆን ፖለቲካው ከጊዜ ወደጊዜ በማይረቡ ዜጎች እየተያዘ ሀገርን በፍትህና በርትዕ ማስተዳደር የሚገባቸው ሰዎች አንድም በወምበዴዎቹ ሠርጎ-ገቦች እየታደኑ ወደእሥር ቤት እየተወረወሩና እየተገደሉ አንድም ግድያንና እሥራትን በመፍራት ሀገር ጥለው እየተሰደዱ አንድም “ልጆቼን ላሳድግበት” በሚል ፍራቻ አንገታውን በመድፋት በየቤታቸው ተደብቀው ይሄውና አገር የጃርቶች መፈንጫ ልትሆን በቃች፡፡ ፍርሀት መጥፎ ነው፡፡ ፍርሀት የራስን ግላዊ ህልምና የወደፊት ተስፋ እንዲሁም ኩሩ ስብዕና ብቻ ሣይሆን አገርን ያሳጣል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያን አፍርሰው ከእንደገና ውብ አድርገው መገንባት የሚችሉ ስንትና ስንት የተማሩ ዜጎች ያሏት ሀገር በደናቁርት ዘረኞች የፊጥኝ ታስራ እንደክርስቶስ በኤሎሄ ላማሰበቅታኒ ጩኸት ጣር ላይ ልትገኝ የቻለችው በ“ምን አገባኝ”ና በ“ምን አሳጣኝ ብዬ!” የዜጎች ፍርሀት ወለድ ወረርሽኝ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ በዚህ ከቀጠልን ጠቅላላውን እንጠፋለን፡፡ አንድዬ ይድረስልን እንጂ በዚህ መልክ የጠፉ ሀገሮች እንዳሉ ታሪክ ራሱ ምሥክር ነው፡፡ ፈጣሪ ግን ኢትዮጵያን መቼም ቢሆን አይረሳትምና ተስፋችን በርሱ ነው፡፡
አንዲት በተደጋጋሚ የምትጠቀስ ግጥም እኔም እዚህ ላይ ልጥቀሳት፡-
“ ‹እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ፤
እሱ ነው አገሬን ያረዳት እንደበግ›፤
በሚል ግጥም ልጽፍ ብድግ አልኩኝና፤
‹ምን አገባኝ› ብዬ ተውኩት እንደገና”፡፡ (በጣም ገላጭ ግጥም ናት)
አዎ፣ “ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆመው ማውረድ ያቅታል” ይባላል፡፡ በጣም ትክክለኛ አባባል ነው፡፡ ብዙዎቻችን የሀገራችን ጉዳይ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ብለን እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ወደሰማይ አንጋጠን በተስፋ ስንጠብቅ ችግራችን ከመቀረፍ ይልቅ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰና ይበልጥ እየተወሳሰበ መጥቶ ዜጎች በሰላም ወጥተን መግባት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደረስን፡፡ የአምስት ሊትሩን እሽግ የምግብ ዘይት በብር 1000፣ አንድ ኪሎ ምሥር ክክ 130 ብር፣ አንድ ኪሎ ሥጋ ቁርጥ/ጥብስ ከብር 1000 እስከ ብር 1500 እና አንድ ኩንታል ጤፍ በብር 6000 ገደማ መግዛቱን ለባለጠጎች ቅንጦት እንተወውና እኛ ድሆች ግን ከሰኞ ወደ ማክሰኞ የምንደርሰው በስለትና በጸሎት ሆነ፡፡ ከአዲስ አበባ ሰንዳፋ ለመሄድ አሥሬ መታወቂያህ እየታዬ አማራ የሚል ቅጽል ያለህ ከሆንክና በዚያም ላይ አለባበስህ ታይቶ (ምናልባት የአፄዎቹ ምልክት ያለበት ልብስ ከለበስክ) ከመኪና ያወርዱህና ያስሩሃል፤ ከመጠጥ ቤትም አፍሰው ይወስዱሃል – ማን ከልክሏቸው፡፡ ለማንም ብትጮህ ሰሚ የለም፤ ብአዴን ተብዬው መጋዣም ሆዱ ሰብቶ ጆሮው ከምንጊዜውም በባሰ ደንቁሯል፡፡ አክራሪ ኦሮሞ ባለበት ሁሉ አማራ የመኖር መብት የለውም ወይንም መብቱ እጅጉን የተገደበ ነው፡፡ አንድ አማራ ኢትዮጵያዊ – አክራሪ ኦሮሞም ጭምር – በሚኒሶታ (ሚኒ-ሱልልታ) ያለው መብት በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሞ አካባቢ አንድ መቶኛው የለውም – ያለው ብቸኛ መብት በተጠየቀ ጊዜ አንገቱን ለሸኔ ሠይፍ ሳያንገራግር ማቅረብ ነው፡፡
ቁጭ ብለንም ሆነ ተኝተን ስናስበው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰው አላጣችም፤ ሞልቷታል፡፡ ግን “እባለጌ ቤት ሥጋና ምንትስ እርካሽ ነው” እንዲሉ ሆኖብን በዚያ ላይ ወንበሩን የያዘው ስድና ዋልጌ ሆነና ሀገራችን የወላድ መካን እንድትሆን ተፈረደባት፡፡ አንድ ንፍጡን ያልጠረገ ስድ አደግ በርሱ አምሳያ ቀርፆ ከየሥርቻው የሰበሰባቸውን የፓርላማ አባላት ተብዬዎች እያሽቆጠቆጠ ራሱን በራሱ ሲያስመርጥ እንደማየት ያለ ታላቅ ክፍለ ዘመናዊ ሀገራዊ ቅሌት የለም፡፡ ያ ሳይበቃው “ከኔ የተሻለ ሰው ዕጩ ልጠቁም የሚል ካለ ዕድል እንስጠው” በማለት ሲያላግጥ መስማት በራሱ የሚፈጥረው ጸጸትና ቁጭት መብረጃ የለውም፤ ከአእምሮም አይወጣም፡፡ በርሱ ቤት በዚያ ፓርላማ ውስጥም ሆነ በመላ ሀገሪቷ ከርሱ የተሻለ ሰው እንደማይገኝ ያላንዳች ሀፍረት በግልጽ ማወጁ ነው (በፓርላማው ውስጥ እርግጥ ነው ከርሱ የሚሻል ባይገኝ አይገርምም)፡፡ እንግዲህ ተመልከቱልኝ – ከ120 ሚሊዮን ሰው አንድ በሳል ምሁር እርሱ ብቻ ሆኖ ተገኘ፤ ከ120 ሚሊዮን ዜጋ ሀገርን በአራት ዓመታት ውስጥ ዶጋመድ የሚያደርግ ነበልባል ሰው መፈጠሩን ደግሞ እኔ አውቃለሁ፡፡ ግሩም ነው – ሀፍረትን ከሸጡም አይቀር እንዲህ ነው፡፡ ይህን መሰል አስገራሚ ትውልድ ሀገር ሲመራ እንደማየት እርግማን የለም፡፡
“ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ከርሱ ይልቅ አንድ የኦሮሞም በሉት የአማራ ወይንም የሌላ ዘውግ የገጠር ገበሬ የተሻለ የፍትኅ ሚዛን አለው፡፡ ገበሬው በአማራና በኦሮሞ ወይ በትግሬ መካከል ጥልን ዘርቶ የሰውን ደም በከንቱ አያፈስም፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስላለው በዘርም ሆነ በነገድ ዜጎችን እያባላ የሰማይ ቤቱን አይዘጋም፡፡ ይህ ሰው በላ አሰለጥ ግን ወራትን ለማይዘልቅበት ምድራዊ ሥልጣን ሲል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሓን ዜጎችን እርስ በርስ እያፋጀ በገዛ ሀገራቸው አንዱን አፈናቃይ ሌላውን ተፈናቃይ፣ አንዱን ገዳይ ሌላውን ሟች እያደረገ ኢትዮጵያን የለዬላት ምድራዊ ሲዖል አደረጋት፡፡ እግዚአብሔር የሥራውን ይስጠው ከማለት ውጪ ምንም አልልም፡፡
ለማንኛውም ይህ “ምን አገባኝ” የምንለው ፈሊጥ፣ ይህ “ምን አሳጣኝ ብዬ” የምንለው ራስን ከኃላፊነት የማሸሻ አነጋገር ሀገርን መቀመቅ እየከተታት ስለሆነ የተደበቃችሁ የጥሩ አስተሳሰብ ባለቤቶች እባካችሁ ከዚህ ወዲያ የምንሆነው ነገር የለምና ወደመድረክ ብቅ እያላችሁ የበኩላችሁን ተወጡ፡፡ ሁሉ ነገር ደግሞ በግድ በቁጣና በዛቻ ሊሆን አይጠበቅም፡፡ በሚዲያዎች በኩል ወይንም በሚገኝ አጋጣሚ ሁሉ ወጣቱን በመምከር፣ በማስተማር፣ የጥንቱን የአብሮነት ባህልና ወግ ተከትሎ ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ በማድረግ፣ በገንዘብም በሞራልም የነፃነት ትግሎችን በመደገፍ፣ ወዘተ፣ መሣተፍ ከሁሉም “ኢትዮጵያ የጋራ ሀገሬ ናት” ባይ ይጠበቃል፡፡ እንደሰጎኒቷ ራሳችንን በፍርሀት አሸዋ ውስጥ ቀብረን ነፃነትን ከሌሎች መጠበቅ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነውና አሁንም ቢሆን ከዚህ በባሰ ሳይረፍድ ከየተደበቅንበት እንውጣ፡፡ የተረገሙ ሽንቶች ከአራት ኪሎ እስከ ደምቢዶሎ ተቆጣጥረውታል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሰውን ዝምታ ስታዘብ እነዚህ ሰዎች ምን እስኪያደርጉን እንደሚጠበቅ አይገባኝም፡፡ ከላይ መጠበቁ እንዳለ ሆኖ የራስን ድርሻ መወጣትም ተገቢ ነው፡፡ ነጻነት በነጻ የሚገኝ የቡና ቁርስ አለመሆኑን ብዙዎቻችን አልተረዳንም፡፡ ነጻነትን የሚሻ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይገባዋል እንጂ ከሌሎች ሞት የርሱን ድሎት መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የኔ የዳግማዊ ድርሻ ከበፊትም መጮህ ነውና እጮሃለሁ፡፡ አንድ መረዳት ያለብን ነገር እነዚህ ሰዎች ከዚህ የበለጠ ዕድል ካገኙ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሁላችንም የሞጋሣ ሰለባዎች እንደምንሆንና ሌላው ቀርቶ ከኦሮምኛ ውጪ መናገር በትንሹ እንደሚያሳስር አትጠራጠሩ፡፡
“ምን አገባኝ” ብዙ እየጎዳን ነው፡፡ “ምን አሳጣኝ ብዬ” የሚባለው የራስ ወዳድነት መገለጫ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ አንድ ሰው ስለሚኖርበት ማኅበራዊ መዋቅር ካላገባው ምን እንደሚያገባው ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ዜጋ በጋራ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ሲገባው “ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ” እንዲሉ “ምን አሳጣኝ ብዬ! ምን ጎደለብኝና እዚያ ሄጄ እጨማለቃሁ!” የሚባሉት አባባሎች ጉዳታቸው ቀላል እንዳልሆነ እያየን ነው፡፡ አሁን ፖለቲካውን የሚያቦኩና የሚጋግሩት ሥራ-ፈቶችና ሥራ መፍጠርም ሆነ ተቀጥረው መሥራት የማይሆንላቸው ሰነፎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የሥራ ዕድል የሚያጡ ብዙዎች ዜጎች ከነሥንፍናቸውና ከነግማግም ጠባያቸው(አስተሳሰባቸው) ፖለቲካውን እየተቆጣጠሩ ይህን የተከበረ አገርን በዕውቀትና በጥበብ የማስተዳደር ተግባር በዘረኝነትና በሙስና አግማሙት፡፡ አሁን ባሉበት ደረጃ ተወስነው የሚቀሩ እየመሰለንም ብዙዎቻችን ዝም ብለናል፡፡
ፖለቲካ በመሠረቱ መመራት ያለበት ከፍ ሲል በፕሌቶ እንደተጠቀሰው በዐዋቂ ሰዎች ነበር፡፡ ግና ዐዋቂዎች ፈሩና ተደበቁ፤ የነሱን መደበቅ ያወቁ ወስላቶች ደግሞ አለዕውቀትና አለችሎታ ፖለቲካውን ተቆጣጠሩና ይፈነጥዙበት ገቡ፡፡ በዚያ ላይ ቦሃ ላይ ቆረቆር እንደምንለው እኒህ ደናቁርት ዘረኝነትንና ሃይማኖትን እንደአገዛዝ ሥልት እየተጠቀሙ ሀገራችንን መመለሻ ወደሚያሳጣ የውድቀት አፋፍ እያዳፏት ይገኛሉ፡፡ በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት አገርን ለመምራት መጀመሪያ ኦሮሞ መሆን አለብህ፣ የኦሮሞነትን መሥፈርት ካለፍክ ሃይማኖትህ ፕሮቴስታንት መሆን አለበት፣ ይህን ፈተና ካለፍክ የኢትዮጵያዊነትን የወል ዕሤቶች መጥላትህ አለመጥላትህን የሚለካ ሊትመስ ፔፐር በምላስህ ይሰካና ከወደቅህ ማለትም ኢትዮጵያን የምትወድ መሆንህ በመሣሪያው ከተሳበቀብህ ትባረራለህ – በመባረር ብቻም ከተተውክ እሰዬው፡፡ በነዚህ በሦስቱም አልፈህ የብልጽግናን ወንጌል መቀበልህንና ፀረ-ኦርቶዶክስ መሆንህን ለመለየት ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ትፈተናለህ፤ ያን ካለፍክ አንደበትህ አለቃህ የሚናገረውን ሀሰትም ይሁን እውነት እንዳለ ማስተጋባት መቻል አለመቻሉ ይፈተናል፡፡ ሌላ ሌላ አጋንንታዊ ፈተናም ይኖራል – ማን ያውቃል ሰባቱ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉበትን ባንዲራም እንደቴዎድሮስ አድሃም በግልጽ እንድታውለበልብ ይጠበቅብህ ይሆናል – ዓለም የደረሰችበት ዝቅጠት ከዚህም በላይ ነው – ከዚህ በላይ ዝቅጠት መኖሩን እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ ይህን ሁሉ መመዘኛ ካሟላህ አንጎልህን እቤትህ ታስቀምጥና በጥቅምና በፕሮፓጋንዳ የናወዘ አካልህን ብቻ ይዘህ ወደብልጽግና ቢሮ በመሄድ ቅን አሽከር ትሆናለህ፡፡ ከዚያም “ሳይጠሩህ አቤት፣ ሳይልኩህ ወዴት” ማለት ነዋ – ይሄ ሁሉ ውርደት ታዲያ ለአንዲት እንጀራ ነው! “አንቺ አንዲት እንጀራ መስታውቴ ነሽ፤ ከቶ የሥንቱን ፊት ታሳይኛለሽ፡፡” የተባለው ለዚህ ይሆን? አዎ፣ ሆድ መጥፎ ነው፤ ገደል ይከታል፤ ቃልን ያስበላል፤ ልጅንና መላ ቤተሰብን ሳይቀር እንዳወጡ ያሸጣል፡፡ በተለይ እምብርት ያልተበጀለት ሆድ፡፡
የሚሆነው ሁሉ ከመሆን ባይዘልም የተደበቃችሁ ወገኖች በብርጭቆ ውስጥ ተሸሽጋችሁ (ተሸሽገን) ከመንጨርጨር የምትችሉትን (የምንችለውን) ሁሉ ለማድረግ ብቅ ብቅ ማለት ጀምሩ (እንጀምር)፡፡ ይህንንም ስታደርጉ በተቻለ መጠን ለዘንዶው ጭዳነት ሳትዳረጉ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ መልካም ሥልቶችን በመጠቀም ይሁን – ልብ አድርጉ! ዘንዶው ዘወትር መስዋዕትን ይፈልጋል – አልጋው የሚጸናው የሰው ደም በተለይም የአማራ ደም ሲያገኝ ነውና ሕዝብን ለማገልገል ስትነሱ በጥንቃቄ ይሁን – ዶክተር አምባቸውንና ጄኔራል አሣምነውን ያዬ ከዘንዶ ጋር አይቃለድም፡፡
… ስለችግር ማውራት አቅቶኝ አይደለም ይህን መሳይ ምክር ላይ ለዛሬ ያተኮርኩት፡፡ እንጂ ችግርን ማውራት ብፈልግ ኖሮ አማራን ከኢትዮጵያ ምድር በሁሉም ዘርፍ ለማጥፋት የተሸረበውን ዓለም አቀፍ ሰይጣናዊ ሤራ ከግብ ለማድረስ በትምህርት ሚኒስትርነት የተሾመው አማራ ጠሉ ጂኒ ሰሞኑን የአማራ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ለማድረግ (ሊያውም ትምህርት ራሱ ከስም ውጪ እንዳለ ተቆጥሮ መሆኑ ነው) የሠራውን ኦሮሙማዊ ሸርና ተንኮል ማንሳት አቅቶኝ አይደለም – አሥረኛ ክፍል ዘጠኝ “ኤ” ያመጣችና 12ኛን የክፍል ውስጥ ውጤት ሸልላ በአንደኛነት ያለፈች ኮረዳ ማትሪክ መሰሉን ፈተና 162 ምናምን ታመጣለች ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው፤ ግን ግን ሰው የዘቀጠ ቢዘቅጥ እስከዚህን ወርዶ መፈጥፈጥ አለበት? ኦሮሙማዎች ኧረ እባካችሁን ትንሽ ሰከን በሉ!! ነገ እኮ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ የነገ ትውልድን ላለማሳፈር መሠራት ያለበት ዛሬ እንጂ ነገ አይደለምና እነዚህን ሰዎች መካሪ ካላቸው ይምከራቸው፡፡ ሥራቸው ሁሉ እኮ ከጤነኛ ሰው ቀርቶ ከበሽተኛም ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ለማንኛውም እንደዚህ ችግርን ማንሳት ማለት ሽንት ቤት ተቀምጦ ፈስ ገማኝ እንደማለት ነውና ዋናው የዘር ፖለቲካ ነቀርሣ ከቤተ መንግሥት ሳይነቀል ተዘርዝረው የማያልቁ ችግሮችን ለመዘርዘር መሞከር ምክንያትን ትቶ በውጤት ብቻ እንደማተኮርና የቁስልን ሥረ መሠረት አጥንቶ ከማከም ይልቅ የላይ ቁስልን ለማድረቅ ብቻ ጂፒ ወይ አልኮል እንደመቀባት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ይቺ ከወደራሽያ በኩል የምትጨሰው ጭስ ደግሞ ለሀገራችን መጠነኛ እፎይታ የሚሰጥ ጊዜን የምታመጣ ይመስለኛልና አንናቃት፡፡ ይህች የምታስነጥስ የመተማዋ ዓይነት ጭስ ወደገላግሌው የሦስተኛው የዓለም ጦርነት ደረጃ የማደግ “ወርቃማ” ዕድል እንዳላትም ከተለያዩ ጥቁምታዎች መረዳት አይቸግርም፡፡ ዓለማችን አንድ ነገር ለመገላገል ምጥ ላይ ትመስላለች፡፡ በውል ተለይታው ያልታወቁ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች ፍልሚያ ላይ ናቸው፡፡ የሚጠቅ ነገር ይወለድ፡፡
በነገራችን ላይ የሚገርማችሁ ነገር ዘለንስኪና የኛው ጉድ በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ፤ ሁለቱም ከአንድ ማዕከል መላካቸውና የጌቶቻቸውን ትዕዛዝ እየተከተሉ መራመዳቸው፣ ሁለቱም ሕዝባቸውን በማስጨረስ ረገድ ደንታቢስ መሆናቸው፣ ሁለቱም ለሥልጣናቸው እንስፍስፍና ሟች መሆናቸው፣ ሁለቱም በኦርቶዶክስ ላይ መዝመታቸው፣ ሁለቱም ኮሜዲያኖች መሆናቸው፣ ሁለቱም የምዕራባውያን ቅምጦች መሆናቸው፣ ሁለቱም ውሸታሞች መሆናቸው፣ ሁለቱም ሽቅርቅሮች መሆናቸው፣ ሁለቱም ለማስመሰል እንጂ ሁነኛ ሃይማኖት የሌላቸው መሆናቸው፣ ሁለቱም አስመሳዮች መሆናቸው … አይ! ምነው ሸዋ! አሁንስ አበዛሁት፡፡ ቢበቃኝስ? በያላችሁበት ሰላም ሁኑልኝ….