>

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች    ለተጨማሪ 10 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ታዘዘ !!! (ባልደራስ)

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች 

– ለተጨማሪ 10 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ታዘዘ !!!

ባልደራስ

 

 “ሽንት ቤት ላይ ታስረናል፤ ግን አንሰበርም፣ አንሸነፍም”   ብለዋል!

የባልደራስ አባላት ቢኒያም ታደሰ እና ሳሙኤል ዲሚትሪ /ኩባ/ ጨምሮ፣ በደረጀ ይበይን የክስ መዝገብ የተካተቱት የ15 የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ ጠዋት አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው የፌደራል የመጀመሪያ  ደረጃ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ታሳሪዎቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከ15 ቀን እስር በኋላ ሲሆን፣ ዛሬ ቢያንስ በዋስትና ይለቀቃሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ እስረኞቹ በግምት 4፡00 ሰዓት ላይ ችሎት ፊት ሲቀርቡ፣ ከፊሎቹ በአድዋ ክብረ በዓል ጊዜ አድርገውት የነበረውን ቲሸርት ለብሰው ቀርበዋል፡፡ ሁሉም በጥሩ የሞራል ደረጃ ላይ እንደሚገኙም የፍርድ ቤት ታዳሚ ለመታዘብ ችሏል፡፡
•የፖሊስ አቤቱታ 
ፖሊስ ምርመራውን  ምን ደረጃ ላይ እንዳደረሰ በፍርድ ቤቱ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ “የበርካታ የምስክሮችን ቃል ተቀብያለሁ፣ ስልኮች እንዲመረመሩ ለመረጃ እና ደህንነት ልኬያለሁ፣በቤት ብርበራ ያገኘኋቸውን ማስረጃዎች እየተመለከትኩ ነው፡፡ ሆኖም፣ አሁንም ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል ጊዜ ያስፈልገኛል፣ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን እያፈላለኩኝ ነው፣ የቪዲዮ ማስረጃዎችን ከመገናኛ ብዙሃን እንዲሰጡኝ ጠይቄ መልስ እየጠበኩኝ ነው፣ የተጠርጣሪዎችን የጀርባ ታሪክ እያጠናሁ ነው፣ እስረኞቹ ቢለቀቁ ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን ስለሚያጠፉብኝ በእስር ላይ ቆይተው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይጨመርልኝ ” ብሏል፡፡
•የተከሳሽ ጠበቆች ምላሽ
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ፣ “እስረኞቹ የሚገኙት በቤተሰቦቻቸው ጥየቃ በማያመቸው እና በምርመራ ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች በማይታሰሩበት በአባ ሳሙኤል መሆኑ ወጣቶቹን የመበቀል አጀንዳ እንዳለ ያመላክታል፣ እንደ ክሱ ጥፋተኛ ቢሆኑ እንኳን የቅጣቱ ጣራ 300 ብር ወይም 3 ወር እስራት ስለሆነ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም፣ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት መሞከር ጭራሽ ወንጀል ነው ተብሎ በህግ የተደነገገ ነገር የለም፣ባለሥልጣናት የግል አቤቱታ ባለቀረቡበት ሁኔታ ፖሊስ በስማቸው ምርመራ የሚያደርገው በህግ አግባብ አይደለም፣ እስረኞቹ ማስረጃ እና ምስክሮች ሊያጠፉ የሚችሉበት የተለየ መንገድ ስለመኖሩ ፖሊስ አሳማኝ መከራከሪያ አላቀረበም፣ ከእስረኞቹ መካከል በደም ግፊት፣ በስኳር እና በተለያዩ ህመሞች እየተሰቃዩ የሚገኙ አሉ፡፡ ስለዚህም፣ተጠርጣሪዎቹ ተጨማሪ 14 ቀን በእስር ላይ የሚቆዩበት ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ በነፃ ይሰናበቱ፣ አልያም በዋስትና ዛሬውኑ እንዲለቀቁ ይደረግልን” በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
•የእስረኞቹ አቤቱታ
 የባልደራስ አባልና ታዋቂ የጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ የሆነው ቢኒያም ታደሰ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ “የታሰርንበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው፣ ታስረን የምንገኘው በሽንት ቤት ላይ ነው፣ ህክምናም የለም፣ ጥየቃው በሳምንት 3 ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ከእነዚህ ቀናት መካከል እሁድ ስላልተካተተ ቤተሰቦቻችንን በአግባቡ ማግኘት አልቻልንም ” ብሏል፡፡
ሌላ እስረኛ በበኩሉ፣ “ የታሰርኩት ታማሚ እናቴን የምንከባከበው እኔ ብቻ በሆንኩበት ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ነው፣ እናቴ መንቀሳቀስ አትችልም፣ በጣም ችግር ላይ ትገኛለችና የዋስትና መብቴ ተጠብቆ እናቴን ወደመንከባከብ ልመለስ ይገባል ” በማለት ሲቃ እየተናነቀው ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ ሌላ እስረኛ ደግሞ፣ “እኔ በሙያዬ ነገረ ፈጅ ነኝ፣ ስለ ህግ አውቃለሁ፡፡ አሁን ምርመራ እየተደረገብን ያለው አዳነች አበቤን ብቻ ተሳደባችሁ ተብለን ነው፡፡ ስለ አንድ ባለሥልጣን እንጂ ስለ ብዙ ባለሥልጣናት እየተጠየቅን አይደለም፡፡ ግለሰቧ አቤቱታ ባላቀረቡበት ሁኔታ ፖሊስ ምርመራ ማድረግ አይችልም” ብሏል፡፡
የፍርድ ቤቱ ብይን
ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ወገን ካዳመጠ በኋላ፣አስቀድሞ ወስኖ የቆየ በሚያስመስለው ሁኔታ የቀረቡትን ክርክሮች በቂ ምላሽ ሳይሰጥባቸው ተጨማሪ 10 ቀናት በመፍቀድ፣ ለመጋቢት 22 2014 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጥቷል  ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከችሎት ሲወጡ ፍርድ ቤቱ ለነበሩት ቤተሰቦቻቸው፣ የባልደራስ አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም የችሎቱን ሂደት ለመከታተል በቦታው ለተገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥተዋል፡፡ “አንሰበርም፣ አንሸነፍም” በማለትም ተናግረዋል፡፡
Filed in: Amharic