>
5:26 pm - Saturday September 15, 1500

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች ጠበቃ በነፃነት እንዳይናገሩ ተፅዕኖ ተደረገባቸው (ባልደራስ)

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች ጠበቃ 
  በነፃነት እንዳይናገሩ ተፅዕኖ ተደረገባቸው
ባልደራስ


 “ፖሊስ ወጣቶቹን እየተበቀለ ነው” መባሉ ዳኛውን አስቆጣቸው፣በንዴት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጡ
/
ከ30 በላይ የባልደራስ አባላትና ሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶች በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት ዛሬ አራዳ ጊዮርጊስ ምድብ የመጀመሪያ ደረጃ ፌደራል ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ታስረው ከሚገኙበት አባ ሳሙኤል እስር ቤት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ የፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ የደረሱት የግፍ እስረኞቹ፣ 4፡30 ላይ ችሎት ሲቀርቡ ፊታቸው ላይ ጥሩ ስሜት ይነበብ ነበር፡፡
ከብዛታቸው አኳያ በ3 መዝገብ የተከፋፈሉ ሲሆን፣ ቅድሚያ በእነ ኤርሚያስ ብርሃኑ መዝገብ የሚገኙት 10 ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል፡፡
 የፖሊስ ጥያቄ
ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ “ የምስክሮችን ቃል አልጨረስኩም፣ ስልኮች እንዲመረመሩ ለመረጃ እና ደህንነት ልኬያለሁ፣በቤት ብርበራ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ማስረጃዎች አግኝቻለሁ፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች አሉ፣ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እያሰባሰብኩ ነው፣እስረኞቹ ቢለቀቁ ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን ስለሚያጠፉብኝ በእስር ላይ ቆይተው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይጨመርልኝ ” ብሏል፡፡ ይህ ከሞላ ጎደል ሰኞ እለት በሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ካቀረበው ጋር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ነው፡፡
የተከሳሾች ጠበቃ ምላሽ
ተከሳሾቹ በሙሉ በጠበቃ ቤተማርያም አለማየሁ የተወከሉ ሲሆን፣ ጠበቃ ቤተማርያም ባለፈው ሰኞ ካቀረበው ክርክር ጋር አንድ አይነት ይዘት ያለው ጭብጥ ሲያቀርብ ዳኛው ጣልቃ ገብተው አቋርጠውታል፡፡ በዳኛው እና በጠበቃው መካከል የነበረው ክርክር በአጭሩ እንደሚከተው ይመስል ነበር፡-
ጠበቃ ቤተማርያም ፡- “ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት መሞከር ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገ ነገር የለም፣ ስድብም ቢሆን የቅጣቱ ጣራ 300 ብር ወይም 3 ወር እስራት ነው፣ ይህ እየታወቀ ፖሊስ  እስረኞቹን ለቤተሰቦቻቸው ጥየቃ በማያመቸው እና  በምርመራ ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች በማይታሰሩበት አባ ሳሙኤል መሆኑ ወጣቶቹን የመበቀል አጀንዳ እንዳለ ያመላክታል፡፡ ተጨማሪ የእስር ጊዜ የሚጠየቀውም ከብቀላ ውጭ ሌላ ምክንያት የለውም…”
ዳኛ፡- ጠበቃ ያቁሙ፡፡ ፖሊስ እየተበቀለ ነው የሚሉት አግባብ አይደለም፡፡ ፖሊስን እንደ ተቋም እየዘለፉ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ቃል እንዳይጠቀሙ፡፡
ጠበቃ ቤተማርያም፡- ባለፈው ቀጠሮ ይህንኑ ስናገር ምንም አላሉኝም ነበር፡፡ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ክልከላ ማድረግ ያስፈለገው? ለማንኛቸውም፣ ያሉት ይሁንና ብቀላ የሚለውን አልጠቀምም፡፡ የፖሊስ ዓላማ እስረኞቹን ማሸት
ነው እንጂ ….
ዳኛ፡- አሁንም ያቁሙ፡፡ ማሸት የሚለውንም ቃል መጠቀም አይችሉም…
ጠበቃ ቤተማርያም፡- ተፅዕኖ እየተደረገብኝ ነው፡፡ እንዴት ነው በዚህ ሁኔታ መከራከር የምችለው?
ዳኛ፡- ከዚህ በኋላ እርስዎ መናገር አይችሉም፡፡ ተከሳሾች በቀጥታ መናገር ትችላላችሁ፡፡
ተከሳሾች፡- እኛ በጠበቃችን በኩል እንጂ ራሳችን መናገር አንችልም፡፡
በዚህ ሁኔታ የችሎቱ ሂደት ተጋግሎ፣ ዳኛው በንዴት በተከሳሾቹ ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥተውባቸዋል፡፡ እኚሁ ዳኛ ፊት የቀረቡት ቀሪዎቹ የባልደራስ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች ደግሞ፣ በወግደረስ ጤናው እና በመአዛ ታደሰ የክስ መዝገብ ስር ጉዳያቸው የታየ ሲሆን፣  ዳኛው ከንዴታቸው በረድ በማለታቸው የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥተውባቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ በሙሉ ግን ክሳቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የፍትህ ስርዓት ይህን ይመስላል፡፡ 
Filed in: Amharic