‘… በቅርቡ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችለንን ፊርማ እናሰባስባለን…!!!”
እስክንድር ነጋ – የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት
* … “የአዲስ አበባ ችግር ሀገራዊ ፖለቲካው የወለደው ችግር ነው። ስለዚህ መፍትሔው ያለው ሀገራዊ ፖለቲካው ውስጥ ነው። ወደ መፍትሔው ለመሄድ የግድ ሀገራዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል። አዲስ አበባ ላይ ብቻ በመደራጀት፤ የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤትን በመቆጣጠር ብቻ መፍታት አይቻልም”
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማደግ የሚያስችለውን የመስራች አባላት ፊርማ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ማሰባሰብ እንደሚጀምር አስታወቀ። ከፊርማ ማሰባሰቡ በኋላ በሚካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረው ባልደራስ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት እንደሚያድግ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በአንድ አሊያም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል ከተባለው ከባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ በፊት ለሚካሄደው የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት፤ ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የትብብር ደብዳቤ አግኝቷል። ምርጫ ቦርድ ለሚመለከታችው አካላት ሁሉ በጻፈው በዚህ ደብዳቤ፤ የፓርቲው ተወካዮች ተጨማሪ የመስራች አባላትን ፊርማ ለማሰባሰብ ወደ ተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ሲንቀሳቀሱ ተገቢው ህጋዊ ትብብር እንዲደረግላቸው ጠይቋል።
ባልደራስ በየትኞቹ ክልሎች ፊርማ ለማሰባሰብ እንዳቀደ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ፕሬዝዳንት “እከሌ እከሌ የምንለው ክልል የለም። በሁሉም ክልል ፊርማ እናመጣለን ብለን ነው ዕቅድ የያዝነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የመስራች አባላትን ፊርማ በተመለከተም “ህጉ ከሚጠይቀው እጥፍ ፊርማ እናመጣለን። ለእሱ ደግሞ መሰረት አለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ እስክንድንር “እጥፍ” ያሉት የመስራች አባላትን ቁጥር በአሃዝ ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚመሰረት ከሆነ 10 ሺህ መስራች አባላት ሊኖሩት እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ይደነግጋል። ከመስራች አባላቱ 40 በመቶ ያህሉ የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው በአዋጁ ተቀምጧል። የተቀሩት መስራች አባላት ደግሞ ቢያንስ በአራት ክልሎች መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል።
አንድ ፓርቲ ከክልላዊ ወደ ሀገራዊ፣ ከሀገራዊ ወደ ክልላዊ ለመቀየር በህግ በግልጽ የተቀመጠ ገደብ አለመኖሩን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ነገር ግን አንድ ክልላዊ ፓርቲ ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ሲቀየር ከአባላት ስብጥር፣ ከፓርቲው ዓላማ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የፓለቲካ ድርጅቱን አወቃቀር የሚቀይረው በመሆኑ ይህንን ለውጡን በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማስወሰን እንደሚኖርበት ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ባልደራስ በቅርቡ በሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ “አነስተኛ መሻሻሎች” እንደሚደረጉ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፓርቲው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን የሁለት ዓመት እንቅስቃሴ እንደሚገመገምም አቶ እስክንድር ነጋ አክለዋል።
በመጋቢት 2012 የተመሰረተው ክልላዊው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል። ፓርቲው አዲስ አበባ በፓርላማ ላላት 23 መቀመጫ እና እንዲሁም ለሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩዎችን በማቅረብ በምርጫው ተወዳድሯል። ባልደራስ በተወዳደረባቸው በአብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ አካባቢዎች፤ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ በመቀጠል ከፍተኛውን የመራጮች ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም።
ፓርቲው በአዲስ አበባ ይህን መሰል የመራጮች ድምጽ ቢያገኝም፤ ከከተማይቱ ተሻግሮ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን ያለውን ዕቅድ ያስታወቀው ምርጫው ከተጠናቀቀ ከመንፈቅ በኋላ ነው። የባልደራስ ፕሬዝዳንት ፓርቲያቸው ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለምን መቀየር እንደፈለገ ሲያስረዱ “እኛ አሁን የምንፈልገው ሀገራዊ አማራጭ መሆን ነው። ለመምራት የተዘጋጀ ፓርቲ መሆን ነው የምንፈልገው። በተቃውሞ ደረጃ ታጥረን መቆየት አንፈልግም” ይላሉ።
ባልደራስ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን የወሰነው በሶስት ምክንያቶች መሆኑን የሚናገሩት አቶ እስክንድር፤ የመጀመሪያው ከአዲስ አበባ “ችግር” ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል። “የአዲስ አበባ ችግር ሀገራዊ ፖለቲካው የወለደው ችግር ነው። ስለዚህ መፍትሔው ያለው ሀገራዊ ፖለቲካው ውስጥ ነው። ወደ መፍትሔው ለመሄድ የግድ ሀገራዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል። አዲስ አበባ ላይ ብቻ በመደራጀት፤ የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤትን በመቆጣጠር ብቻ መፍታት አይቻልም” ሲሉ ለከተማይቱ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ሀገራዊ ፓርቲ መሆን አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
ካለፈው ሰኔ 2013 ምርጫ በኋላ የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖር ችግር ጎልቶ መታየቱን የሚናገሩት አቶ እስክንድር፤ ይህም ባልደራስን ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት እንዲያድግ ያደረገው ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። “በኢትዮጵያ ውስጥ ከገዢው ፓርቲ ውጪ በአቅሙ ትንሽ ፈርጠም ያለ አማራጭ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም። በዚህ ምክንያት ክፍተት አለ። የእኛ ሀገራዊ መሆን ወዲያውኑ ያንን ክፍተት ይሞላዋል” ሲሉ አዲሱ አደረጃጀት ያመጣዋል የሚሉትን ለውጥ አስረድተዋል።
ሶስተኛው የባልደራስ ምክንያት ከፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም ጋር የተያያዘ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ገልጸዋል። የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም ባልደራስ ሀገር አቀፍ ፓርቲ መሆን እንዳለበት እንደሚያስቀምጥ የሚገልጹት አቶ እስክንድር፤ በጊዜ ሂደት ፓርቲው ይህን አደረጃጀት መከተሉ የማይቀር እንደነበር አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር