>

የቅጥፈት ከነአካሉዎች - የቁም ተዝካር! *... ከሸፍጠኞች ምን እንማር? (አሳፍ ሀይሉ)

የቅጥፈት ከነአካሉዎች – የቁም ተዝካር!

አሳፍ ሀይሉ
 

*… ከሸፍጠኞች ምን እንማር?


*…. ለብዙ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ችግሮች ዋነኛ ምንጩ አለማወቅ አይደለም፡፡ ሸፍጥ ነው፡፡ እውነቱን እያወቁ መሸፈጥ፡፡ አፍጥጦ እውነቱን መሰወር፡፡ መካድ፡፡ የሆነውን፣ የተደረገውን፣ አልሆነም፣ አይደለም የሚሉ ሸፍጠኞች መብዛት ነው ዋና ችግራችን፡፡ ፖለቲካችን በሸፍጠኞች የተሞላ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችንን የሚዘውሩት ሸፍጠኞች ናቸው፡፡ ሌላ ቀርቶ አካዳሚክ ተቋማት ዲግሪ በጫኑ እበላ-ባይ ሸፍጠኞች የተሞሉ ሆነው ማየት ከተለመደ ቆየ፡፡
የሚዲያዎቻችን ግን ከሁሉም የተለየ ነው፡፡ ጎራ ይዞ ሸፍጡን የሚነዛ የበዛበት፣ የሸፍጠኞችና የፖለቲካ ምንደኞች ቤት ከሆነ ሰነበተ፡፡ የሰው ልጅ ከነሙሉ አካሉ፣ ከነሙሉ ህሊናው፣ እንዴት ለሌሎች እያለቀለቀ መኖርን እንደሚመርጥ ለመረዳት፣ ዛሬ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ እነ ኢሣትን፣ እነ ፋናን፣ እነ ኢቲቪን አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡ ከአለቅላቂ፣ ከአባይ፣ ከቀጣፊ፣ ከሸፍጠኛ፣ በውሸትና ለተረኛ በማጎብደድ ከሚተዳደር ጅብ-ሰው ይልቅ፣ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ለምኖ የሚበላ ሰው ምንኛ ክብር አለው!
በሌላው ዓለም የሕዝብ ሚዲያ ዋነኛ ተግባር፣ እና ዋናው ጠቀሜታ፣ ሸፍጥንና ሸፍጠኞችን ማጋለጥ ነው፡፡ እውነትን ለሕዝብ ማሳወቅ ነው፡፡ አሉታን በሀቅ መሞገት ነው፡፡ በተለይ መንግሥት ነኝ ባዩ አካል የሚያመርታቸውን ፕሮፓጋንዳዎች አጥልሎ ለህዝቡ እውነተኛ መረጃ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ ማሳወቅ፡፡ ማስተማር፡፡ ለህዝብና ለሀገር የሚበጅ አጀንዳን መፍጠር፡፡ ለእውነትና እውነት ብቻ ታማኝ መሆን ነው የሚዲያ ዋነኛ ተልዕኮው፡፡
በእኛ ሀገር ሚዲያው ራሱ የሸፍጡ አካል ነው፡፡ «ማሽቃበጥ» የሚለው ቃል ትርጉም «ጭራን መቁላት» ብቻ ስለሆነ፣ ኢሣት የሚባለውን የዜና አንባቢዎች ቡድን ወራዳ ተግባር በትክክል አይገልጸውም፡፡ በማሽቃበጥ ላይ እብለት ሲታከልበት፣ ሸፍጥ ሲመረግበት፣ እና ከርስ እንደመፈክር ሲነገብበት – በትክክል ኢሣትን ይመስላል፡፡
ኢሣት የቀደሙ ሸፍጦቹ በሀገር ተጋዳይነት ጭምብል ተሸፍኖ ስለታለፈ፣ የዚህን አሁን የሚታየውን ያህል፣ ያፈጠጠ ሸፍጡ ሳይወጣበት የቀረ፣ አሁን ግን በግላጭ የወጣ፣ በሀገራችን ላይ የምናየውን ሀገራዊ የሚዲያ ሸፍጥ ግንባር-ቀደም ተዋናይነት የሚመራ፣ የፕሮፓጋንዳና የእብለት ፋብሪካ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የፈጣጣነታቸው ደረጃ፣ ከማንም ጋር አይወዳደርም፡፡
ኢሣት፣ ከተረኛው መንግሥት የሚወረወርለትን ጥቅም እየላሰ፣ ከተረኛው ገዢ ጋር የተጣበቀውን ኢዜማ የተባለውን ተለጣፊ ፓርቲ የተለጣፊነት አድርባይ አቋም ለህዝብ እያስተጋባ፣ ያፈጠጡ እውነቶችን አይናቸውን እጥብ አድርገው በሚክዱ ዓይነ-ደረቅ ‹‹ጋዜጠኛ-ተብዬዎች›› የተሞላ ቀጣፊ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡
ህሊና ያለው ሰው በፍፁም የማይደፍራቸው የውሸት ዓይነቶች እኮ አሉ፡፡ አውቆ የተኛ ራሱ ሊሰማቸው፣ ሊያያቸው የሚገቡ ግዙፍ እውነቶች እኮ አሉ፡፡ ኢሣቶች ለጌቶቻቸው ጧት-ማታ ጭራቸውን እየቆሉ፣ እውነቱን ሙልጭ አድርገው ክደው፣ እመኑን የሚሉ፣ አንዳንዶቹ ነጭ ሽበት (የዕድሜ መግፋት ራሱ) የማይበግራቸው፣ ዓይን ያወጡ አውርቶ-አደሮች ስብስብ ናቸው፡፡
ኢሣቶች «ህሊና» የሚባለውን፣ «ይሉኝታ» የሚባለውን የከበረ ኢትዮጵያዊ እሴት፣ ቀቅለው የበሉበት ደረጃ ሲታይ – በእውነት ያስደነግጣል፡፡ ሰብዕናቸውን ቀቅለው በልተውታል፡፡ ህሊናቸውን ለከርስና ለሸፍጥ ሸጠውታል፡፡ የነፍሳቸውን ሀቅ፣ ለአድርባይነት ዘኬ ሸጠውታል፡፡ ይህን ዓይነትን «Perfidy» (ከፍ ያለ የእምነት መክዳት) የፈፀሙ ተራ መደዴ ሰዎች፣ መጨረሻቸው በህዝብ ተንቀው መጣል ነው፡፡
«ሁልጊዜ እየሸፈጥክ ልትኖር አትችልም»! ሁልጊዜ «ጨፍኑ ላሞኛችሁ» ብለህ እስከመጨረሻው እያለቀለቅክ ልትዘልቅ አትችልም፡፡ በመጨረሻ የህዝብ መዘባበቻ መሆን ይመጣል፡፡ በመጨረሻ ተለጣፊ ሆነው ያደገደጉለት አካል፣ እንደ ሸንኮራ መጥጦ ሲያበቃ፣ «በቃኝ፣ በቃችሁኝ፣ ከዚህ በኋላ አታስፈልጉኝም» ብሎ እንደ አሮጌ አህያ አውጥቶ መጣል ይመጣል፡፡
ህሊናቸውን በጨጓራቸው ውስጥ የቀበሩት የኢሣቶች መጨረሻ፣ ከነ ሌጣ ውሸታቸው፣ የሕዝብ መሳቂያ ሆነው መቅረት መሆኑን ብዙዎች አስቀድመው ተናግረዋል፡፡ የኢሣት ሸፍጠኛ ዓይን-አውጣዎች ያጋጠማቸው ይሄው ነው፡፡
የሰው ልጅ ለከርሱ ሲል ዓይኑን አፍጥጦ ውሸትን ለጥቅም እያራገበ፣ በሰው ፊት የመቅረብ እጅግ አስቀያሚ ችሎታ የቱን ያህል ሊያሻቅብ እንደሚችል የለካሁት፣ በእነዚህ ኢሣት በሚባሉ ሆድ-አደር ቀጣፊዎች የተነሳ ነው፡፡
ለወደፊቱ በሀገራችን «የሚዲያ ሰው ነኝ» የሚል የትኛውም ሰው፣ «የሚዲያ ሰው በፍጹም ማድረግ የሌለበትን» ነገሮች ሁሉ፣ የኢሣቶች የሸፍጥና የክህደት አቋሞች፣ እና ላለፉት ሶስት ዓመታት ሙሉ «አንጋለን እንጋታችሁ» ሲሉን የከረሟቸውን የተንሸዋረሩ የሆድ-አደር ዘገባዎች ሁሉ አይቶ፣ ትልቅ ትምህርት ሊወስድ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ ህሊናቸውን በጨጓራቸው ውስጥ የቀበሩ የምላስ-አዳሪዎች ሁሉ፣ መጨረሻቸው ይህ ነው፡፡ ገና ከዚህም የባሰ ውርደት ይገጥማቸዋል፡፡
ቀጣፊነት አስፀያፊ ነው፡፡ ህሊና-ቢስነት ከሰውነት ክብር ዝቅ ያደርጋል፡፡ ያደባባይ ሸፍጠኝነት እጅግ ያስነውራል፡፡

እውነት ነጻ ታወጣለች፡፡

የሸፍጠኞች መጨረሻ የቁም ሞት ነው፡፡

ፈጣሪ ከዚህ ይሰውረን፡፡

Filed in: Amharic