>

''የጥሞና ግዜ----'' (ፊልጶስ)

የጥሞና ግዜ—-”

 

ፊልጶስ


በአንድ ወቅት በጦቢያን መጽሄት ላይ የተጻፈ  መጣጥፍ   ” ወዴየት እየሄድን ነው?”  በሚል ርዕስ፤  በጸጋየ /መድህን አረያ  ነበር።  መጣጥፋን ካነበብኩ በኋላ፤እኒህ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ  አሁን በሕይወት ቢኖሩስ ምን ብለው ይጽፉ ይሆን?”’ ስል አሰብኩ።

 በአቶ ጸጋየ መጣጥፍ ውስጥ አንዲት በግምት የሁለት ወይም ሶስት  ዓመት ዕድሜ ያላት የልጅ ምስል አለ። ልጅቱ ምን አልባትም የእናቷን ቀሚስና ጫማ ለብሳ ለመራመድ ትታገላለች።ጫማዋንም ሆነ ቀሚሱ መሸከም እንዳቃታት፤ ነገር ግን ወደፊት  ለመራመድ እየመከረች  መሆኗን መገመት ይቻላል። ከልጅቱ ምስል ጎን ደግሞ እንዲህ የሚል ጹሁፍ አለ፤  ”እየሄድኩ ነው፤ ግን ወዴት እንደምሄድ አላውቅም።” 

 ርግጥም የተፈጥሮ ህግና ውህደት ነውና  እኛምእየሄድን ነው”  ግን ወዴት እየሄድን ነው?   ይህ ጥያቄ ምን አልባትም የሁላችንም የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ይመስለኛል።አሁን ካለንበት የባሰስ ወዴት ልንሄድ እንችላለን?” ሊባል ይችላል። በርግጥየባሰ አታምጣማለት አይከፋም እንጂ፤ ከወያኔ የባሰ አገዛዝ ይመጣል ብሎ ያሰበ አለ ወይ

/ አብይ አህመድ በገዥው ፓርቲ፤  በእነሱ አጠራር በበልጽግና አንደኛ  መደበኛ ስብሰባ ራሳቸው አስመራጭና ተመራጭ ሆነው የተሰየሙበትንና  ፍጹም አምባገነናዊ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የኦሮሚያው ገዥ ከዓመታት በፊትብልጽግናን ለእኛ ለኦሮሙማ እንዲያመቸን አድርገን ሰርተነዋል። ያሉት በተግባር ስናይ፤ ብሎም የችግራችን መሰረቱ የሚመነጨው ከህግመንግሥቱ  መሆኑ ለዘመናት እንዳልተነገረና ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ቃል እንዳልተገባ ሁሉ፤  ዛሬ  ”አፍንጫችሁን ላሱስንባል፤  በርግጥ ወዴት እየሄድን ይሆን

የሃይማኖት አባት የተባሉት ጳጳስ  ለዓመታት በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲፈጸም የነበረውና እየተፈጸመ ያለው ግድያና የዘር ማጽዳት ሳያሳስባቸው ህገወጥ ጳጳስ መሆናቸው ሳይበቃ፤ ዛሬ ብድግ  ብለው ዘውጋቸውን መዘው የሿሚያቸውቃለአቀባይሆነው ሃይማኖቷ ያለችበትን ሃቅ ሲነግሩን፤ መንፈሳዊነት ወዴት እየሄደ ይሆን?

የአስራ ሁለተኛ ብሔራዊ ፈተና ውጤትራያና ቆቦሆኖ ከተርኞች መንደር የተገኙትን  ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ሲያደርግና፤  ሌላውን ተፈታኝ ዜጋ፤  ፈተናውን  በትክክል ማረምና ውጤቱን ማስተካከል ቀርቶ፤ ጾታየ ተሳስቷላ አስተካክሉልኝ ላለ ተማሪ እንኳንወጤትሽን/ህን አጣርተናል። ነገር ገን ቀድም ሲል ከተገለጸው ውጤት ለውጥ የለውም።ብሎ መልስ የሚሰጥ የትምህርት ሚኒስተር ስናይ፤ ይህ ትውልድ ወዴት እየሄደ ይሆን?

የአዲስ አበባ ወጣቶች ለምን የአድዋንና የካራ ማራን የድል ቀን አከበራችሁ ተብለው  እየታፈሱ ወደ ማጎሪያ መወርወራቸውን  ሳይበቃ በመጸዳጃ ክፍል ውስጥ  ሲታሰሩና፤  የኦሮሚያዊ መሪ  አዲስ አበባን የኦሮሙማ  የማድረጉ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑኑ ሲያረዱን፤ 

ወያኔ ሁለተኛ ዙሩን የወረራ ጦርነት ለማካሄድ ዱብዱብ እያለ እያማሟቀና በጎንደር፣ በወሎና በአፋር የያዘወን ግዛት እያጠናከረ መሆኑን ስንመለከትና፤ ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬምየተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል።ተብሎ ሲነገረን፤ ርግጥ የወያኔና የኦሮሙማ ግንኙነት ወዴት እየሄደ ይሆን

ኦነግ- ሸኔ  ከደፈጣ ተውጊነት ወደ መደበኛ ጦር ማደጉንና ወረዳዎችን ተቆጣጥሮ   የዘር ማጽዳቱን ሥራ ከአለፈው በበለጠ ለመፈጸም ጥንካሪውን ሲያሳይና  በቤተመንግሥት እየተዘወረ ከዚህ ደረጃ መድረሱን የራሳቸው ሰዎች ሲነግሩን፤ በርግጥስ  ወዴት እየሄድን ይሆን?

የሰሜኑና የአፋር ህዝብ  ከቀየውና ከመኖሪያው መፈናቀሉ ሳያንሰው፡ የእለት ጉርስ  እጥቶ በርሃብ አለጋ እየተገረፈ ህጻናት መሞታቸውን እየሰማን፤ እንዲሁም  በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ያለው ወገናቸን በጠኔ እያለቀ፤ ገዥዎቻችን ደግሞ በድግስ ብዛት ዕረፍት አጥተው፤ህዝብ ‘ራቡን ሲችለው ገዥዎቻችን ጥጋቡን አልችለው ሲሉ።ወዴት እየሂድን ይሆን?  

‘’ብሶት፡ ለቅሶና የየየ! ‘’ በሁሉም የጎሳ መንደር ይሰማል። ጨቋኙ ከተጨቋኙ የበለጠ የብሶትና አገር የማተራመስ ከበሮ ይደልቃል። ሁሉም በሚባል ደረጃ የጋራ አገርና የጋራ ማንነት፤ ወደደም ጠላም በጋራ እየኖረ መሆኑ ዘንግቷል። ከፊሉ አዲስ አገር ለመፍጠር በህዝብ ደም ይነግዳል። ከፊሉ  በመንደር ተቧድኖ ይቧቀሳል።

ሁሉም ተበዳይ ሆኗል። ሁሉም ተጨቅኝ ሆኗል። ሁሉም የጎሳው ተቆርቋሮ ሆኗል። ሁሉም ገዳይ ሆኗል። ሁሉም ተገዳይ ሁኗል። ሁሉም ተናጋሪ ነው። እደማጭ ግን የለም።  ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውሉ በጠፋ መንደርተኝነትና ትርምስ ውስጥ ህዝብ  በአገሩ፤ አገር አልባና  መንግስት አልባ ሆኖ የምድርን ፍዳ ሁሉ ይከፍላል። 

ተበደልኩኝ ባዩ፣ ሎሌ – አዳሪው በዝቶ
የችግራችንም፣ .ውል – ማሰሪያው ጠፍቶ፤ 

አሳሪው – ሲታሰር 

ታሳሪው – ሲያስር፤
የሄደው – ሲመጣ፣ የመጣው – ሲሄድ
መውጫና  መውረጃው፣ ሆኖ የአገር መንገድ፤
ብዘራው አይበቅል፣ ቢበቅል አያፈራ
መጠላለፍ ሆኖ፣ ቀረ የ’ኛ ሥራ።——

ፓለቲከኛና ተቆርቋሪ ነኝ  የሚል፤  የጎሳውን ሆነ የኢትዮጵያን ስም እየጠራ፤ የሚታየውና የሚያልመው  ነገር ቢኖር፤ በኢትዮጵያ ህዝብ የሬሳ ከምር ላይ ተረማምዶ፤ ከቻለ ባለሥልጣን ካለያም  ከጦርነትና ከመከራ የተረፈውን ደሃ  ከእፋ ነጥቆ  ለመጉረስ ነው።  

ከምስራቅ እስከ ምዕራብ   ከስሜን እስከ ደቡብ ከመሃል እስከ ዳር፤  የሰው ልጅ  በጦርነት እየተገረፈ፣ በድርቅ እየተመታና  በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ  ባለበት ሰዓት   ባለፈው የሄድንበት ከዚህ አድርሶን፤ አሁንም  ሁሉም በየጎጡ መሽጎ፤ የጦርነት ነርጋሪት እየጎሰመ   ህግናሥርዓት የሚፈጸመው በደካሞች ላይ ብቻ ሆኖ ስናይ፤ወዴት እየሄድን ይሆን ?” ብሎ፤ ቆም ተብሎ የሚታስብበት  ከትላንት ወዲያ ነበር፤  አላደርግነውም። ትላንት ነበር፤ አላደረግነው። ዛሬስ??

ጊኒያዊያንቅርጫት ሙሉ እንቁላል ተሸክመህ አትጨፍር ይላሉ። ከአሁን በኋላ  በያዝነው መቀጠል ከማንችልበት ደረጃ  ድረሰናልና  ”ቅርጫት ሙሉ እንቁላል ተሸክመን እየጨፈርን’’  መሆናችን ለሁላችንም  ፤ ዛሬ እንኳን  በቃ ሊባል  ይገባል። 

 በእውነት በኛ ዘመን ያልተፈጸመ፣ የሴራ፣  የክፋትና የጭካኔ ዓይነት የለም።  ከዚህ በተቃራኒ ያለው  ሰላም፣ አንድነትና ሥልጣኔ ግንርግማን እንበለው ኋላ ቀርነትና ድንቁርና እንደ ጥላ ስንቀርበው እየራቀን  በደምና በአጥንት የተግንባን አገርና ህዝብ  ለማፍረስ ከዚህ ደረጃ ደርሰናል። 

የሚሰማም ሆነ ወደ ልቦነው የሚመለስ ካለ፤  አሁን የቀረንና ያልሞከርነው ነገር ቢኖር፤ ነገር ግን በእጃችን ያለ፣ አሁኑኑ ቃል ገብተን ልናደርገ የሚገባን ነገር ቢኖር፤ ለሁላችንምየጥሞና ግዜመውሰድ ነው።

ለዚህ ምሳሌ የቢልጀሟ ከተማ በሆነችው ቪልቮርድ  የሚገኘው የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው።  በአጭሩ   ቪልቮርድ ከተማ የፉላኒ ደችና የፈረሳይ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት ከተማ ነች። ይሁን እንጅ  ከተማውን ለማስተዳደርና ለማዕከላዊ መንግሥት በሚደረገው  ውክልና የደችና የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለዘመናት መግባባት አቅቷቸው፤ ሁሌ  ‘’በሰለጠነ’’ መንገድ እንደተናቆሩ  ይኖሩ ነበር። በዚህም ምክንያት  የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግስትም  ችግሩን ሊፈተው ባለመቻሉ መጨራሻ ወደ ፍርድ ቤት ሂዱ። ፍርድ ቤቱ ለዘመናት የቆየውን የውክልና አለመግባባት፤  ዓመታት ዶሴ ክፍቶ ሲያከረከር ኖረ። በመጨረሻ ግን ፍርድ ቤቱ ያለፈውንም ታሪክና አሁን ያለውን ትውልድ  ከመጭው ትውልድ ጋር  ሊኖረው ስለሚችለው አንድምታ   ካጠናና ካገናዘበ በኋላ የሰጠው ብያኔ፤  ”  የቪልቮርድ የፍርድ ጉዳይ እንዲቆምና፤ ዶሴው ለአስር ዓመት እንዲዘጋ ወስኖ፣  ለሁለቱም ወገኖች የአሥር ዓመት የጥሞና ዘመን በመስጠት፤ ተሟጋቾቹን አሰናበታቸው።

እኛስ —–መንግሥት ለወያኔ ብቻ  የሚሰጠውን የጥሞና ግዜ ለራሱም ሆነ  የሚመለከተው ሁሉ እንዲወስድ ያደርግ። ጥሞናው ለሁላችንም ያስፈልገናልና። ቅንነቱ ካለ የሚገድ ነገር የለምና፤  ለአገራችንም ሆነ ለወገናችንየጥሞና ግዜእንውሰድና ለመወያየትም ሆነ ለመደማማጥ፤ ራስንም ለመጠይቅ ሆነ ለመጠየቅ፤ ለዛሬውም ሆነ ለመጭው ዘመን ተስፋ እናድርግ፤ ሰላምን እንዝራ። ቅድሱ መጸሃፍም ”–ሰላም ወዳድ ሰዎች፤ ሰላምን ዘርተው የጽድቅን ፍሬ ይሰበስባሉ።—” ይላልና።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic