>

በትግራይ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ በአፋር እና በአማራ ክልሎችም እንዳለ ተዘንግቷል ተባለ! (ባልደራስ)

በትግራይ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ በአፋር እና በአማራ ክልሎችም እንዳለ ተዘንግቷል ተባለ!
ባልደራስ

 

 በሰሜኑ ጦርነት የሞቱት ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መሆኑ ተገምቷል!
በትግራይ ለተከሰተው የሰብዓዊ ቀውስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ለማቅረብ እንዲችል የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰነው የግጭት ማስቆም ውሳኔ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በቀዳሚነት ድጋፋቸውን ከገለፁት መካከል የምዕራባውያውን መንግሥታት ሲሆኑ፣ አንዳቸውም ከትግራይ ባሻገር በአፋር እና በአማራ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ቀውስ አለማንሳታቸው ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በአማራ እና በአፋር ክልል ያሉ ተፈናቃዮች በባልደራስ በኩል ባቀረቡት ቅሬታ፣ በትግራይ ላሉት ተጎጂዎች እርዳታ ለማቅረብ ያለው ርብርብ የሚደገፍ ቢሆንም፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ያሉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አስታዋሽ ማጣታቸው፣ የሰብዓዊ እርዳታም የፖለቲካ ጭቅጭቁ ሰለባ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት ተነፍገናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ ፣ በጦርነቱ ከቀዬያቸው ተፈናቅለው ባዶ እጃቸውን ከመቅረታቸውም ባሻገር፣ አሁን ባሉበት ሁኔታ የምግብ፣ የህክምና እና የመጠለያ ችግር እያሰቃያቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቤልጀየም ውስጥ በሚገኘው ግህነት ዩኒቨርስቲ (Ghent University) በተደረገ ጥናት በሰሜኑ ጦርነት በአማራ እና በአፋር ክልሎች የደረሰው ጉዳት ሳይደመር፣ በትግራይ ብቻ የሚሞተው ቁጥር ከ500.000 በላይ  ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡ በቀጥታ በውጊያ አውድ ላይ የሞቱት ከ50.000 እስከ100.000 ፣ ከ150.000 እስከ 200.000 ከምግብ እጦትና ረሃብ ጋር በተያያዘ፣ ተጨማሪ እስከ 100.000 ከህክምና እጦት  በተያያዘ ነው ተብሎ ተገምቷል፡፡ የአፋርና የአማራ ሲደመር ቁጥሩ በጣም ይጨምራል።
ይህ ሁሉ ጥፋት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ በህወሓት በኩል ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ወታደራዊ ምንጮች አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ በተለይ ወልቃይትና  ጠገዴ ዳግም በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር ለመገናኘት ያለው ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ አይሎ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በያዝነው ሳምንት እንኳን በማይካድራ በኩል ውጊያ ሞክሮ እንደነበር በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወሳል፡፡
Filed in: Amharic