>

ዋስትና የተፈቀደላቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች፣  ውሳኔው  ተሻረባቸው...!!! (ባልደራስ)

ዋስትና የተፈቀደላቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች፣  ውሳኔው  ተሻረባቸው…!!!

ባልደራስ

 

ተጨማሪ 10 ቀናት በእስር ቤት እንዲቆዩ ተወስኗል !!
 ዋስትና የተፈቀደላቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች  የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ ተጨማሪ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በእነ ደረጀ ይበይን መዝገብ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩት የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች ሀሙስ በነበረው የጠዋት ችሎት የ7.000 ሺህ ብር ዋስ  ተፈቅዶላቸው የነበረ ሲሆን፣ ፖሊስ ከሰዓት በኋላ ይግባኝ አቅርቦ፣ ባልተለመደ የብርሃን ፍጥነት ጉዳዩ  ታይቷል፡፡
የፖሊስ ክርክር
ፖሊስ ዛሬ ባቀረበው ክርክር፣ ተከሳሾችን የሚመለከት ምርመራ አለማጠናቀቁን፣ በምርመራ ሂደት ያገኛቸውን ማስረጃዎች በባለሙያዎች እያስተነተነ መሆኑን፣ ይህም ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በሀሙሱ  ችሎት የሰጠው የዋስትና መብት አግባብ አይደለም በማለት ተቃውሟል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች ክርክር 
የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው፣ እስረኞቹ ለ1 ወር የሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ እየተንገላቱ መሆናቸውን፣ ፖሊስ በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ምክንያት ተመሳሳይ መሆኑ ምርመራው ከልብ እየተሰራ አለመሆኑን እንደሚያመላክት፣ የባለሙያ ትንታኔ ያስፈልጋል የተባለው ደግሞ፣ የተከሳሾቹን በእስር መቆየት የማይፈልግ መሆኑን፣ ምስክሮች የተባሉትም ፖሊሶች እንደመሆናቸው መጠን መርማሪዎች በፈቀዱ ጊዜ ከጎናቸው ሊያገኙዋቸው የሚችሉ በመሆኑ የዋስትናው መብት ሊከበር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ብይን
ብዙዎች እንደታዘቡት፣ ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኝ ያለውን ክርክር ጊዜ ወስዶ ሳይመለከት፣ የፖሊስን አቤቱታ በመቀበል፣ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የዋስትና መብት በመሻር፣ ተከሳሾቹ ለተጨማሪ 10 ቀናት እስር ቤት ሆነው ፖሊስ ምርመራውን እንዲያካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
እስረኞቹ ያሉበት ሁኔታ
በአባ ሳሙኤል “የለበስነውን የአድዋን ቲሸርት አናወልቅም” በማለታቸው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የተከለከሉ እስረኞች ቁጥር  ዛሬ ወደ 6 አድጓል፡፡ እንደሚታወሰው፣ ትላንት ማለዳ አራት እስረኞች የአድዋን ቲሸርት በማድረጋቸው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ተከልክለው የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ዳኛቸው ጉደታ /ቻቻ/ እና ዘካሪያስ ቶራ የተባሉ ሁለት የአዲስ አበባ ወጣቶች የአጼ ምኒልክ እና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ያለበትን የአድዋ ክብረ በዓል ቲሸርት ለብሰው ወደ ፍርድ ቤት እንዳይሄዱ ተከልክለዋል፡፡
በዚሁ ምክንያት፣ትላንት ወደ ፍርድ ቤት እንዳይሄዱ ተከልክለው የነበሩት ቢኒያም ታደሰ፣ ሳሙኤል ዲሚትሪ፣ ደረጀ ይበይን እና አስጨናቂ ተስፋዬ ዛሬም ቀጠሮ ስለነበራቸው ትላንት ለብሰውት የነበረውን ቲሸርት ዳግም አድርገው ወደ አውቶብስ ለመሳፈር ሲሞክሩ በፖሊስ እንዲወርዱ ተደርጓል፡፡ 6ቱም ወጣቶች ዛሬ ጠዋት ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ሲሆን፣ ጠበቆቻቸው ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አስረድተው ህገወጡን ክልከላ ባደረጉት ተረኛ ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእስር ላይ ያሉ ተከሳሾችን ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ በማረሚያ ቤቶች ላይ በህግ የተጣለ ኃላፊነት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ታስረው ቢገኙም፣ እያሳዩ ያለው ጽናት እና አይበገሬነት ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በከተማዋ ወጣቶች ዘንድ፣ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ መንፈስ ይታይ የነበረው በኢህአፓ ጊዜ ሲሆን፣ ከቀይ ሽብር በኋላ ስሜቱ ደብዘዝ ብሎ ቆይቷል፡፡

አንሰበርም! አንሸነፍም!

Filed in: Amharic