>

የሕዝብን አንገት ያስደፋው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት አመት ጉዞ ...!!! (ምኒልክ ሳልሳዊ)

የሕዝብን አንገት ያስደፋው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት አመት ጉዞ …!!!

ምኒልክ ሳልሳዊ

ሕዝብ ከሕወሓት አገዛዝ ለመላቀቅ ያደረገውን ትግል ተገን በማድረግ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አራት አመታት እጅግ በሰቆቃ የተሞላ እና የህዝብን አንገት ያስደፋ የአስተዳደር ጊዜያትን አልፈዋል። ዶክተር አብይ ሕዝብን የእርካብና መንበር መጽሃፋቸው ቤተ ሙከራ አድርገውታል። ሁላችንም ቢያንስ የለውጡ ችግር ይቀረፋል በሚል ተስፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብንደግፍም ለውጡን ቀልብሰውት የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ በዕጥፍ አሳድገውት አሳይተውናል። ያለፉ መንግስታት ከቆዩባቸው አስርት አመታቶች በላይ በአብይ የአራት አመት አገዛዝ በአገርና በሕዝብ ላይ የተፈፀሙ ኃጢያቶች እጅግ የበረቱ ናቸው። ሕዝብ በገዛ አገሩ ተዘዋውሮ መስራትና መኖር እንዳይችል የተደረገው በአብይ አስተዳደር ነው።
ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከአሶሳ እስከ መልካጀብዱ፤ ከአማራ እስከ አፋር፤ ከትግራይ እስከ ኮንሶ ፣ ከመተከል እስከ ሃረር …. ወዘተ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያን ላይ በአብይ የአገዛዝ ዘመን ከባባድና መንግስት ኃላፊነቱን ያልተወጣባቸው ችግሮች ተከስተዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል። የመንግስት ተጠያቂነትና ኃላፊነት የጠፋው በዶክተር አብይ አስተዳደር ዘመን መሆኑ እሙን ነው። አገራችን የነበሯትን ታላላቅ መሪዎች ያለአግባብ በስሜታዊነት በማስወገዷ ሌላ የምትከፍለው ዕዳ ያለባት ይመስላል። ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያ ጥሩ መሪ ለማግኘት አልታደልሽምና እርምሽን አውጪ።
በጦርነት፣ በመፈናቀል በሰው ሰራሽ ድርቅና ረሃብ ሃገር የታመሰችው በዚህ ዘመን ነው። የመፍትሄ አካላት ተቀባይነት ያጡት ሆዳምና አስመሳይ ሰዎች ወደ መንግስት የተጠጉት በስፋት የታየው በዚህ አራት አመት ውስጥ ነው። ለሕዝብ ከመጨነቅ ይልቅ በመንግስት ጉያ ተወሽቀው ሌብነትና ሙስናን የተስፋፉት በዚህ አራት አመት ሲሆን በርካታ ባለስልጣናት ከነዘርማንዘራቸው በንግድ አለም ተሰማርተው የኑሮ ውድነትን በመፍጠር የኢኮኖሚ አሻጥር የፈጠሩት ባለፈው አራት አመት ነው።
ያለፉት አራት አመታት ችግር ዋና መነሻው የሕወሓት አባላይ የስልጣን ዘመን ቢሆንም የአብይ አስተዳደር መዋቅሩንና የተራቡ ሌቦችን ይዞ በመቀጠሉ የሌብነት ዋና አመራር በመሆኑ አገርን ለከፋ አደጋ አጋልጣታል። ለውጥ ስለሆነ ያጋጥማል ተብለው የታለፉ በርካታ አደጋዎች ቀጥለውና ተሻሽለው ሕዝብን ወደ ገደል ጨምረዋል ሰው በቁሙ ከመስቀል ጀምሮ እስከ ሰው ማቃጠል ተደርሷል። ምንም መሻሻሎች አልታዩም።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ንግግሮች ተከትሎ የተሻለ ጊዜ መጣልን የተሻለ ሰው ፈጣሪ ላከልን ያለው ሕዝብ በማያውቀውና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የሞትና የመፈናቀል ዋጋ እየከፈለ ነው። የኢሕ አዴግ ቅጥያ የሆነው ብልጽግና ሕዝብን ከማበልጸግ ይልቅ በብልኛ በተካኑ ባለስልጣናቱ በሕዝብ ላይ ተደራራቢ ሰቆቃ እየፈጠረ ነው።
የሕወሓትን ሕጎችና መዋቅሮችን መለወጥ ያልፈለገው የአብይ አስተዳደር ባለፉት አራት አመታት ውሸታም ባለስልጣኖችንና የሃሰት ሪፖርት ተሸክሞ በመጓዝ ሃገርን አረንቋ ውስጥ ከቷታል። ባለፉት አራት አመታት ጥቂት ባለስልጣናትና ካድሬዎቻቸው እንዲሁም የማሕበራዊ ድረገጽ አክቲቪስቶቻቸው የሃገርን ሃብት በመመዝበር መንግስትን በመካብ ሃገርን ወደ ገደል ይዘዋት እየተጓዙ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ አትፈርስም በሚል ሽፋን ላለፉት መቶ አመታት የተገነባን አገረ መንግስት እና ሃገርን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በዚሁ ዘመን ነው። ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። በሚዲያ ጥሩ የሆነ አንድ መልካም ነገር ይነገርና በመሬት ላይ ኝ አንድ ሚሊዮን ጉዳቶችን ስናይና ስንሰማ እንውላለን።
በንግግራቸው ብቻ ያመናቸውን ሕዝብ የዋሹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነባለስልጣኖቻቸው የሚያደርጉትና የሚናገሩት የማይገናኝ የሆነበት ህዝብን ግራ አጋብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት እርካብና መንበር የተሰኘው መጽሃፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማንነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ሕዝቡ የሚፈልገውን እየነገሩት የሚሰሩት ግን የፈለጉትን መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገብትን አንድም ነገር አላደረጉም ። ባለፉት አራት አመታት ለሕዝብ ከተሰሩ ልማቶች ይልቅ በሕዝብ ላይ የተሰሩ ወንጀሎች በመቶ እጥፍ ይበልጣሉ። በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ንጹሐን እየተሳደዱ ይፈናቅሉ፣ ይታሰሩና ይገደሉ ጀመር። የዘረፋውማ ጉዳይ የማይታየውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፤ አገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ሕንፃና መሬት ‘ምን ታመጣላችሁ?’ በሚል ዕብሪት እየተዘረፈ ይገኛል። ላለፉት አራት አመታት ለሕዝብ ጥያቄ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ የአብይ አስተዳደር በበደል ላይ በደል የከሳውን መግደል የሚለውን መርህ በመከተል መልው ኢትዮጵያውያንን አንገት አስደፍቷል። ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ መብትና ነጻነት ወሬ ሆነው ቀርተዋል። ያልጠቀስኩት ጽሁፉን ለማሳጠር በማለት ያልፃፍኩት በርካታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥመቶችን ራሳችሁ ሙሉት ።
Filed in: Amharic