>
5:13 pm - Friday April 19, 5878

ከአስር ሺዎች ሰማዕታት የአንዱ ታሪክ… (ሙሉጌታ ገብረመድህን)

ከአስር ሺዎች ሰማዕታት የአንዱ ታሪክ… 

ሙሉጌታ ገብረመድህን
የወያኔ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ከተዘረጋ ጀምሮ በወልቃይት-ጠገዴ የዐማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ታውጆ ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለዚህም የሰውና የጅምላ መቃብር ምስክሮችን አስረጅ ምሳሌ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ከሁመራ ኤርፖርት ግቢ የጅምላ መቃብር እስከ ማይካድራው ጭፍጨፋ፤ ከደጀናው ባዶ ስድስት ማጎሪያ እስከ “ግህነብ” (ገሃነብ) ዋሻና የምድር ውስጥ እስር ቤቶች በጅምላ ያለቀው ዐማራ በአስር ሺዎች ይገመታል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን በአካባቢው ያደረገውን ጥናት ተከትሎ “ግህነብ” (ገሃነም) ተብሎ የሚጠራውን በተራራ የተከበበ  ድብቅ እስር ቤት ውስጥ በርካታ የጅምላ መቃብሮችን አግንቷል። ዩኒቨርሲቲው በወያኔ የተፈፀሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎችንና የታፈኑ እውነታዎችን በማውጣት ረገድ አቻ የለሽ ምሁራዊ አበርክቶውን በመወጣት ላይ በመሆኑ ለጥናት ቡድኑና ለተቋሙ ምስጋና ይገባቸዋል።
👇    👇   👇
 _________
ይህ ታሪክ የአንድ ግለሰብ ታሪክ ብቻ አይደለም የአስር ሺህዎች ታሪክን ይወክላል፡፡ ወያኔ በተጠና እና በተደራጀ ሁኔታ የወልቃይት-ጠገዴ ዐማራን ዘር የማጥፋት የቀደመ ታሪክ ስለመኖሩ ማመሳካሪያ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች የተገኘ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ወንድም Asfaw Abreha ታሪኩን አጋርቶን ነበር።
***
የባዶ ስድስት ትል ‹ዝንጉራ› እና ፀጋዬ አድማስ አሳዛኝ ፍፃሜ
ዝንጉራ በአካባቢው የሚጠራበት ስም ነው። ይህ ትል ቅንቡርስ ከሚባለው ትል ጋር ይመሳሰላል። የሰውነት ቆዳን በስቶ የሚገባ ትል ነው። በወልቃይት-ጠገዴ በነበሩ ባዶ ስድስት (06) ተብለው በሚታወቁት የወያኔ እስርቤቶች ውስጥ ይህ ትል የዐማራ ተወላጆችን ለማሰቃየት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። እስር ቤቶቹ በተገነቡበት አካባቢዎች በሚገኙ ጫካዎች ውስጥ በብዛት ይገኛል።
ይኼንን ትል ወያኔ፣ የግፍ እስረኛ የሆኑ የዐማራ ተወላጆችን ለማሰቃየት ይጠቀምበት ነበር፡፡ በወልቃይት-ጠገዴ መሬት ውስጥ ‹ግህነብ› እና ‹ደጀና› ከተባሉ ትልልቅ የ06 ማሰቃያ ቤቶች በተጨማሪ በየገጠሩና በየቀበሌው ከመሬት በታች የተቆፈሩ ከ12 በላይ እስር ቤቶች ነበሩ።
ይህ ትል (ዝንጉራ) በማንነታቸው ምክንያት እስረኛ የሆኑ የዐማራ ተወላጆችን ለማሰቃየት (Torture) እንደ አንድ ሁነኛ ዘዴ በሁሉም ማሰቃያ ቤቶች ውስጥ በጥቅም ላይ ውሏል። ትሉ የቆዳ ውስጥ ሕይወቱን ጨርሶ ሲወጣ በሚፈጠረው ቁስል ምክንያት ባክቴሪያል ኢንፌክሽን በሽታ ያስከትላል፡፡  ይህ ትል በጨለማ ቤት የታጎሩ እስረኞች የሰውነት ቆዳ ውስጥ ከገባ በኋላ በሚያደርጋቸው የራሱ እንቅስቃሴዎች ምክንያት እስረኞችን እረፍት አልባ (Restless) ያደርጋቸዋል፤ እንቅልፍ ይነሳቸዋል፡፡
መጀመሪያ ላይ ያሳክካል… ትሉ የቆዳ ውስጥ እድገቱን እየጨረሰ ሲመጣ በጣም ያሰቃያል። በአጠቃላይ በስቃይ በተሞላ ስሜት ውስጥ እረፍት የለሽ ያደርጋል፡፡   በባዶ ስድስት ማሰቃያ ቤቶች ውስጥ ከተገደሉት በርካታ ዐማራዎች የተረፉት፣ የተለያዩ የስቃይ ዓይነቶችን አስተናግደዋል።
ከነዚህ ቶርቸሮች መካከል በዝንጉራ ትል የሰውነት ቆዳቸው እንዲበሳሳ የሆኑና የአእምሮ በሽተኛ ሆነው ቀሪ ህይወታቸውን ያሳለፉ በርካታ ናቸው።  አዳዲስ እስረኞች በመጡ ቁጥር ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች መካከል የተወሰኑት ተመርጠው በአካባቢው ከሚገኘው ጫካ ውስጥ ትሎቹን ለቅመው ያመጣሉ።
ትሎቹን እስረኞቹ  ወደታጎሩበት ቦታ ሌሊት በተኙበት ሰዓት እላያቸው ላይ በተዘጋባቸው ርብራብ ቀዳዳዎች አሾልከው በብዛት ያስገቧቸዋል። ቀጥሎ የሚሆነው ትሎቹ የእስረኛውን ቆዳ በስተው ሲገቡ ለእስረኛው አይታወቀውም። መጠነኛ የማሳከክ ስሜት ብቻ ሊሰማው ይችላል። ህመሙ የሚበረታው ትሉ በእሰረኛው የሰውነት ቆዳ ውስጥ ከገባ በኋላ በሚያደርጋቸው የራሱ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ነው፡፡
በዚህ መንገድ በርካታ የዐማራ ተወላጆች በቃላት ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታ ተሰቃይተው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የጥይትም የትልም ራት ሆነዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የባዶ ስድስት (06) ገዳይ የነበረው አብርሃ ቀትሪ የተሰኘ የህወሓት አመራር ፀጋዬ አድማስ የተባለን አንድ የዐማራ ተወላጅን የገደለበት መንገድ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ይህ ታሪክ በ1980ዎቹ አጋማሻ ላይ ደጀና ውስጥ በነበረ አንድ “የሕዝብ መድረክ” ላይ የተፈፀመ ነው። ጊዜው ወያኔ በጉልበት አካባቢውን የጠቀለለበት ወቅት ነበር፡፡ የወያኔን የግዛት ተስፋፊነት ተከትሎ ገና በ1974 እንቅስቃሴውን ለመግታት የከፋኝ ዐማራ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተጀምሮ ነበር፡፡ ይህ በትጥቅ ትግል የተደገፈ ሕዝባዊ ተቃውሞ በ1980ዎቹም ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር፡፡
ከዚህ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ የታሰረው ፀጋዬ አድማስ፣ ደጀና በሚገኘው የ06 ማጎሪያ ውስጥ እስረኛ ነበር። አብርሃ ቀትሪ የተባለው ሰው በወቅቱ በነበሩት የወያኔ እስርቤቶች እየዞረ ከድርጅቱ አዛዦች በመጣለት የግድያ ትዕዛዝ መሠረት እስረኞችን እየለየ የሚገድልና የሚያስገድል ሰው ነበር። በጨካኝነቱ ይታወቃል።
አብርሃ ቀትሪ ማለት ገና በወያኔ የሽፍትነት ዘመን ጀምሮ የ06 ከፍተኛ ኃላፊዎች ከነበሩትና የግድያ ትዕዛዛቱን ከሚልኩት ከነ ስብሓት ነጋ፣ ፀጋይ በርሄ፣ ከብስራት አማረ እና ከዘአማኑኤል ጋር በቀጥታ ይገናኝ የነበረ ሰው ነው።
የወልቃይት-ጠገዴ አርበኞች የመታገያ ስም የሆነው ‹ከፋኝ› ተብሎ የሚታወቀው በአርበኞች የሚመራው የህዝብ እንቅስቃሴና ተቃውሞ በተጠናከረበት በአንደኛው ቀን ላይ አብርሃ ቀትሪ የደጀናን ህዝብ ለስብሰባ ጠራ። ስብሰባው ህዝቡን ለማሸበርና ለማስፈራራት የተጠራ ነበር። ስብሰባው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች እንደ ቀሩት አብርሃ ቀትሪ እንዲህ አለ…
‹መቼም ፀጋዬን ታውቁታላችሁ አይደል? ግለሰቡ በተደጋጋሚ ተመክሮ አልሰማ ያለ (የከፋኝ ዐማራ ንቅናቄ አካል በመሆኑ) አፈንጋጭ ነው› ካለ በኋላ ወደ ጠባቂዎቹ ዞሮ ፀጋዬን ይዛችሁ አምጡት ብሎ አዘዘ።
ቀድሞውኑ ፀጋዬን የፊጢኝ አስረው የአብርሃን ቀትሪ ትዕዛዝ ሲጠባበቁ የነበሩት የወያኔ ታጣቂዎች ፀጋዬን እያንገላቱ አመጡት። አብርሃ ቀትሪ ቃል ሳይተነፍስ ሽጉጡን በማውጣት ፀጋዬን ጭንቅላቱ ላይ ተኩሶ ከገደለው በኋላ… ‹‹ከመካከላችሁ ምክር አልሰማም የሚል ሰው መጨረሻው እንደ ፀጋዬ ይሆናል›› ሲል ተናገረ፡፡ አዳራሹ ውስጥ ያለው ህዝብ በዐይኑ እየተመለከተ ፀጋዬን ከገደለው በኋላ አስከሬኑ ሳይነሳ እንዲቆይ ተደረገ።
አዎ! ያ ምስኪን ፀጋዬ አድማስ መቀጣጫ እንዲሆን ስለተፈለገ አስከሬኑ የግድ መቆየት ነበረበት። በፊተኛው መደዳ ላይ የተቀመጡት ተሰብሳቢዎች  በራሱ የደም አበላ ተነክሮ በተጋደመው የፀጋዬ አስከሬን ላይ አንድ ነገር አስተዋሉ።
… በዝንጉራ ትል የተበሳሳው የፀጋዬ ሰውነት የለበሰውን የተቀደደ እራፊ ጨርቅ  አልፎ  በግልፅ  ይታይ ነበር…
ይህን መሰል አሰቃቂ የግድያ ታሪክ ወልቃይት ውስጥ መስማት የተለመደ ሆኖ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ዘልቋል፡፡
ይህ የግፍ ታሪክ ፈፅሞ እንዲደገም አንፈቅድም። ተከዜ እንደ ጎላን ኮረብታ ሆኖ የመቀጠሉ እውነታም በዘመን መራር እውነታዎች የተረጋገጠ ሀቅ ነው።
(በፅሁፉ ውስጥ የተዋቀረው ታሪክ ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ከአስፋው አብርሃ የተገኙ መረጃዎችን በማጣመር የቀረበ ነው)

 

Filed in: Amharic