>

አሻጋሪውንም የሚያሻግር ብሔራዊ ሸንጎ ይቋቋም....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አሻጋሪውንም የሚያሻግር ብሔራዊ ሸንጎ ይቋቋም….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

*….. ልክ የዛሬ ሁለት አመት ተኩል የተጻፈ። የለውጥ ሃይሉ መንገዳገድ ሲጀምር እና አያያዙ አላምር ሲለኝ በዚህ አጭር ጽሑፍ ሊመጡ የሚችሉትን አደጋዎች እና አደጋዎቹን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳ መቀነስ የሚቻልበት ሀሳብ በዝርዝር ጠቁሜ ነበር። ከሰጋኋቸው አደጋዎች አብዛኛዎቹን አስተናግደናል። በቀጣይ የሚመጣውን አደጋ ለማስቀረት ድንገት ሰሚ ካለ በሚል ድጋሚ ለመለጠፍ ወደድኩ። አንብቡት፣ ተወያዩበትም…!!!
የአብይ አስተዳደር ቀደም ሲል ቲም ለማ እያልን የምንጠራው እና ለውጡን በአሻጋሪነት እየመራ ያለው ቡድን በጊዜ ክርኑ የዛለ መሆኑን በርካታ ማሳያዎችን እያጣቀስኩ ቀደም ሲል በጻፍኳቸው ዳሰሳዎች ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በመጀመሪያ ባሳለፍነው አመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ አገሪቱ እጅግ በርካታ እና የከፉ አደጋዎችን ብታስተናግድም የዛኑ ያህል በርካታ መልካም ነገሮች መከናወናቸውን አስምሮ ማለፍ ተገቢ ነው። የለውጥ ማዕበል ከግራ ቀኝ የሚያላጋው የአብይ አስተዳደር በአንጻራዊነት አገሪቱ ተጋርዶባት የነበረውን ጥቁር ደመና በከፊልም ቢሆን ለመግፈፍ ሞክሮ ነበር። አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊከቱ ይችሉ የነበሩ ስጋቶችን ባያጠፋቸውም እንኳን እንዲዘገዩ አድርጓል። አደጋዎቹ በመቼውም ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግን በየክልሉ አልፎ አልፎ የሚፈነዱት ግጭቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
በሌላ ጽሑፌ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ህውሃትን ወደ መቀሌ እንድትመሽግ  ካደረገው የለውጥ ዋዜማ የነበረው አገራዊ ሥጋት ምንጩ በሕዝብ እና በአንድ አንባገነናዊ ሥርዓት መካከል በነበረው የአልገዛም እና እንደልቤ ልፈንጭብህ ትንንቅ የመነጨ ነበር። አደጋው አገራዊ መበታተንን የሚያስከትል ቢሆንም አንድም ሕዝብ አሸንፎ ነጻ የሚወጣበት፤ አለያም ህውሃት ክርኑን አፈርጥሞ እና ሕዝብን ደፍጥጦ የአገዛዝ ዘመኑን የሚያድስበት ፍልሚያ ነበር። የህውሃት ክርን ዝሎ ስለነበር ሕዝብ ለማሸነፍ ቻለ።
ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ግን በብዙ መልኩ ከላይ ከጠቀስኩት የተለየ ነው። የአሁኑ ትንንቅ ዘርፈ ብዙ ነው። ህውሃት በብዙ ትናንሽ ጉልበተኞች ተተክታለች። በየክልሉ ክርናቸውን አፈርጥመው አይነኬ የሚመስሉ እና አንዳንዶቹም ሰፊ ድጋፍ ያላቸው አንባገነኖች ተፈጥረዋል። በአብይ የሚመራው የለውጥ አሻጋሪ ኃይል፣ የለውጡ ሂደት ሙሉ በሙሉ ያልተዋጠላቸው ወይም አካሄዱን የማይቀበሉ እና በግማሽ ልብ የለውጥ አጃቢ የሆኑ የክልል መንግስታት፣ በየክልሉ ለውጡ ይውጠኛል ብለው የሰጉ አክራሪ ብሔረተኞች፣ የአስተዳደራዊ ግዛት እና የማንነት ጥያቄ አንግበው የተደራጁ ብሶተኛ ቡድኖች፣ የአብይ አስተዳደር እንዲያሻግራቸው ደጅ እየጠኑ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለውጡን በይፋ የተቃወሙ እና ነፍጥ አንፈታም ያሉ የታጠቁ አካላት፣ ለውጡ ያስወግደናል በሚል ስጋት ቆፈን የያዛቸውና ሰፊ በሆነው የኢህአዴግ መዋቅር ሥር የተሰገሰጉ የድርጅት ተሽሟሚዎች እና ከሥር ያለው ካድሬ፤ እንዲሁም ለውጡን ተከትለው የመጡ አደጋዎች ስጋት ውስጥ የከተቱት ሕዝብ የተፋጠጡበት ወቅት ነው።
የአብይ አስተዳደር የሕዝብ ቅቡልነትን በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማግኘት የቀናውን ያህል በራሱ ድርጅታዊ እና መንግስታዊ መዋቅር ስር የሰገሰጋቸውን አመራሮች እና ስር ድረስ የሚገኘውን ሰፊ የካድሬዎች መዋቅር ማማለል የቻለ አይመስልም። ባለፊት አንድ አመታት በየክልሉ የተከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የመብት ጥሰቶች እና የፖለቲካ ውጥረቶች መነሻቸው በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ከሥር የሚገኙ የመንግስት አካላት ከሚፈጽሟቸው ስህተቶች እና ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። የለውጥ አመራሩ ምንም ቀና ቢሆን እና በጎ ቢመኝም ወደ ሥር ያለው ሰፊ መዋቅር ከተንሸራተተ ወይም በእኩል የቅንነት መንፈስ ለውጡን ተቀብሎ ካልተንቀሳቀሰ የአብይ አስተዳደር የትም ሊደርስ አይችልም። ጭንቅላት እርቆ እያሰበ እና እርቆ እየተለመ እግር ካልተከተለው አንድ ስንዝር ፎቀቅ ማለት አይቻልም። አብይ በራሱ መዋቅር ስር ያለውን የሰው ኃይል በሙሉ ልብ ከጎኖ ለማሰለፍ በተቸገረበት በዚህ ወቅት ቀደም ሲል በሕዝብ ዘንድ ያገኘው ቅቡልነትም ቁልቁል እየተናደ የመጣ ይመስላል። ዛሬ ብዙዎች የአብይን አሻጋሪነት መመርመር እና ጥያቄ ውስጥ መክተት ጀምረዋል።
የአብይ አስተዳደር ከስሩ ባለው ሰፊ ድርጅታዊ መዋቅር ተጠርንፎ የተያዘ ይመስላል። ሕውሃት በዘር እያቧደነች እና የአገሪቱን ምሁራን አሽሽታ በታማኝ ካድሬዎች ያዋቀረችው የመንግስት ቢሮክራሲ ዛሬም እንዳለ እንደደነደነ ነው። የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ለለውጡ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት እና የመንግስት መዋቅሮች ዛሬም በእነዚህ መስሎ አደር የፓርቲ ተሿሚዎች እና ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር ናቸው። እነዚህ አካላት ይህን ለውጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈሩት ይመስላል። ካለባቸ የእውቀት እና የአቅም ማነስ የተነሳ ለውጡ ይተፋናል የሚል ጥልቅ ስጋት እንዳደረባቸው በብዙ መልኩ ይንጸባረቃል። ሁለተኛው ደግሞ ሥርዓቱ ቢያከርመን እንኳ ምርጫን ተከትሎ ከሚመጣው ለውጥ አንድንም የሚል ጥልቅ ስጋት ይንጸባረቃል። ስለዚህ እነዚህ ስጋቶች ለውጡን በሙሉ ልብ ከመቀበል ይልቅ እንዲፈሩት አድርጓቸዋል።
በዚህም ምክንያት ይህ ሰፊውን የመንግስትን መዋቅር የተቆጣጠረው ወደታች የሚገኘው አካል ለውጡን በሁለት መንገግ እየተፈታተነው ይገኛል። የመጀመሪያው ሕዝብን ወደ ከፋ ብሶት ሊዳርጉ የሚችሉ አስተዳደራዊ በደሎችን መፈጸም ነው። ሕዝብ በሄደበት መንግስታዊ ተቋም ሁሉ እንዲማረር እና እንዲሰላች ማድረግ፣ አዳዲስ የክልል እና የማንነት ጥያቄዎችን በይፋ፤ አንዳንዴም ከጀርባ ሆኖ ማራገብ፣ የሕግ የባልይነትን ችላ ማለት እና አለማስከበር፣ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል የሚቻልበት እድል እያለም ሥራውን ችላ በማለት ሕዝብ የጥቃት እና የወንጀል አድራጎቶች ሰለባ እንዲሆን ማድረግ፣ ሕዝብ በአብይ አስተዳደር ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት ከመኖሪያው ማፈናቀል እና በማንነት ላይ ያነጣጠረ መድልዖ በመፈጸም ሥርዓቱ ከአንድ ባለጊዜ ወደ ሌላ ባለጊዜ የተሸጋገረ እንዲመስል እና ሕዝብ በአብይ አስተዳደር ላይ እምነት እንዲያጣ እና እንዲማረር እያደረጉ ይመስላል።
ሁለተኛው ችግር ደግሞ በአንዳንድ ክልሎች በግልጽ እንደሚታየው ወደታች የሚገኘው የመንግስት መዋቅሮች በአክራሪ ብሔረተኞች ተጠልፎ እንዲወድቅ ተደርጓል። ይህ ሁኔታም አክራሪ ብሄረተኞች የአብይን አስተዳደር ለመገዝገዝ የራሱን ድርጅት እንደ መሳሪያ እንዲጠቀሙ እድል የፈጠረላቸው ይመስላል።
በአጭሩ እነዚህ ችግሮች ለውጡን ይመራል በሚል ሕዝብ አደራ የጣለበትን ኃይል በእቅዱ እና ልፋቱ ልክ ወደ ፊት መራመድ እንዳይችል እያደረጉት ይገኛሉ። ይህ ችግር ከወዲሁ በአግባቡ እና በአፋጣኝ መላ ካልተበጀለት እና መፍትሄ ካላገኘ ሁለት አደጋዎች ሊያስከትል የሚችል ይመስለኛል። የመጀመሪያው አደጋ ከታች ወደ ላይ እየገፋ የመጣዊ እውነተኛው ኢህአዴጋዊ/ህውሃታዊ ባህሪ እያደር ከላይ ለውጡን የሚመራውንም ኃይል አቅጣጫ ሊያስት ይችላል። እነ አብይ ከላይ ወደታች ሊያሰርጹት እየሞከሩ ያሉት የለውጥ አካሄድ ከታች ወደላይ እየገፋ በመጣው ተገዳዳሪ ግፊት የመዋጥ አደጋ ሊገጥመው ይችላል። ወይም ባይውጥው እንኳን ለውጡ ፈቅ እንዳይል እና የሽግግሩ ጊዜም እንዲራዘም ምክንያት ሊሆን ይችላል። የሽግግሩ ጊዜ መራዘም ደግሞ አገሪቱ ቶሎ ተረጋግታ ትክክለኛውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እንዳትጀምር እንቅፋት ይሆናል።
ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ለውጡን ይመራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የገዢው ፓርቲ እየደረሰበት ካለው ውጫዊና ውስጣዊ ግፊት የተነሳ ሊበታተን ይችላል። ህውሃት ከወዲሁ አንድ እግሯን ከፓርቲው ውስጥ አውጥታ አንድ እግሯ ብቻ ነው የቀረ የሚመስለው። ሌሎቹም የህውሃትን ዱካ ሊከተሉ የሚችሉበት አደጋ በግልጽ ይታያል። አገሪቱ ባልተረጋጋችበት፣ ጠንካራ መሰረት ያለው እና አገሪቱን ሊረከብ የሚችል የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይል ባልተፈጠረበት በዚህ ወቅት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴት የመበታተን ወይም የመፍረክረክ አደጋ ከገጠመው የለውጥ ሂደቱ ብቻ ሳይሆን የሚደናቀፈው የአገረ ብሔር ግንባታውም ሂደት ይስተጓጎላል። ለውጡም ሌላ መልክ ይይዛል ወይም ነውጥ ይወልዳል።
የመፍትሔ ሃሳብ
፩ኛ/ እንደ እኔ እምነት የአብይ አስተዳደር ይህን ለውጥ ብቻውን በመምራት በተጀመረው ፍጥነት ልክ ወደፊት ገፍቶ ለመሄድ እና አገሪቱን ከገጠማት አስከፊ ፈተና ለመታደግ ይችላል ብዮ አላምንም። ይህ ለውጥ ሳይውል ሳያደር ከአንድ ፓርቲ እጅ ወጥቶ በብሄራዊ አገር አቀፍ ንቅናቂ ሊዘወር ይገባል። አሁን ያለንበት ጊዜ ብሔራዊ ሸንጎ እንዲቋቋም የግድ የሚያስብል ደረጃ ላይ የደረስንበት ይመስለኛል። ብሔራዊ ሸንጎው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያቀፈ እና ይህን የሽግግር ወቅት አገሪቱ በጥንቃቄ እንድትሻገር ለመርዳት የተለመ ይሆናል። የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ፣ የአብይ አስተዳደር እንደ መንግስት፣ የሲቪክ እና የሙያ ማሕበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ አደረጃጀቶች የተካተቱበት ሁሉ አቀፍ ብሄራዊ ሸንጎ ቢቋቋም የተሻለ ይሆናል፤
፪ኛ/ ይህን ብሔራዊ ሸንጎ ለማቋቋም በቅድሚያ ጥናቶች የሚቀርቡበት እና ውይይት የሚካሄድበት ሰፊ አገራዊ የውይይት መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል። ከዛ መድረክ በመነሳት ሸንጎውን ወይም ብሄራዊ የለውጥ አራማጅ ግብረ ኃይል በመፍጠር ተግባራቱን እና ኃላፊነቱን በሕግ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ይቻላል፤
፫ኛ/ የአብይ አስተዳደር መንግስታዊ መዋቅሩን እንደያዘ የሕዝብ አገልግሎቶች እንዳይስተጓጎሉ እና የመንግስት ሥራ እንዳይደናቀፍ እራሱን አገር በማስተዳደሩ ሥራ ላይ ብቻ በመወሰን ለውጡን ለሚመራው ብሔራዊ ሸንጎ ወይም ሌላ ስያሜ ለሚሰጠውን ንቅናቄ ተገቢውን እና በቂ ድጋፍ ያደርጋል፤
፬ኛ/ ከላይ የተዋቀረው ብሔራዊ ሸንጎ አገሪቱ የምትጓዝበትን ፍኖተ ካርታ በጋራ በመንደፍ እና ዝርዝር እቅዶችን በማውጣት ለውጡ በተፋጠነ መልኩ እንዲቀጥል እና ምርጫውም በታሰበለት ጊዜ እንዲካሄድ መንገዶችን የማደላደል ሥራ ሊያከናውን ይችላል። ይህ ሰፊ መሰረት ይዞ የሚነሳው ሁሉ አቀፍ ብሔራዊ ንቅናቄ ለአብይ አስተዳደር ትልቅ አቅም ከመፍጠሩም በላይ ለውጡን እየተገዳደሩ ያሉ ውጫዊ እና ውስጣዊ ኃይሎችን አሸንፎ የመውጣት እድልም ይፈጥሩለታል።
፭ኛ/ ሁሉመ ባለድርሻ አካላት የለውጡ ሂደት ሙሉ ባለቤቶች በሆኑት ልክ ለሚደርሰውም ችግር እና መሰናክል እኩል ኃላፊነት በላያቸው ላይ ስለሚወድቅ የአብይ አስተዳደር ብቻውን ተሸክሞ እየተንገዳገደ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት እኩል ይጋሩታል። አሁን ባለው አካሄድ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች እና ባለ ድርሻ አካላት ልክ እንደ ድግስ ታዳሚ ወይም ተጋባዥ እንግዶች ናቸው። የአብይ አስተዳደር ባቀረበላቸ ልክ ብቻ የሚቋደሱ ታዳሚዎች ሆነዋል። ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በአብይ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም ባለፈ በአገር ግንባታው ሂደት ውስጥ እኩል ኃላፊነት፣ ተጠያቂነት እና የባለቤትነት ስሜት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። የሰሞኑ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና የተቃዋሚ ድርጅቶች እሰጣ ገባም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
ነገሬን በአጭሩ ልቋጭና ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን አስፈሪ አደጋ ለመሻገር እና የተጀመረውም ለውጥ ወደ ታለመለት ጫፍ እንዲደርስ ከተፈለገ ‘እኔ አሻግራችዋለሁ፤ እናንተ ሃሳባችውን በኔ ላይ ጥላችው በቀረበላችው ልክ የዲሞክራሲን ማዕድ ተቋደሱ’ የሚለው የለውጥ ኃይሉ አካሄድ ብዙ እርቀት የሚያስኬ አይደለም። በቅርቡ በሲዳማ ክልል የተከሰተው እልቂት እና በየክልሉ የተዳፈኑ የሚመስሉት እሳቶች ሌላ የከፋ ዋጋ ሳያስከፍሉን በፊት የለውጥ ኃይሉ የተሸከመውን ከባድ ሸክም ሊያግዙት የሚችሉ አጋሮችን በመፍጠር ኃይሉን ማጠናከር ይጠበቅበታል።
ለዚህም በእኔ በኩል እንደ አማራጭ የሚታየኝ የለውጥ ምሪቱ ከአንድ ፓርቲ ከኢህአዴግ እጅ ወጥቶ በብሔራዊ ሸንጎ ወይም ንቅናቄ ሊያዝ ይገባል። ለውጡን ወደታች የሚገፋ ሰፊ የሆነ አገራዊ ንቅናቄ ወይም አደረጃጀት የግድ ይላል። የአብይ አስተዳደር በመንግስት የዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ቢያተኩር አቅም ሊያበጅ ይችላል። ይህ አይነቱ አካሄድ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለውንም ጥያቄ አብሮ ሊመልስ ይችላል። የሽግግር መንግስት ያለውን መንግስት የማፍረስ ሂደት ይጠይቃል። ያ ደግሞ ብዙ መናጋቶችን ይፈጥራል። ያለው መንግስት እንደጸና እና ሥራውንም እያከናወነ የለውጡን ሂደት ግን ብሄራዊ ቅርጽ ማስያዝ ይቻላል። ይህን እድል ሳይዘገይ ለመጠቀም ግን የአብይን አስተዳደርን በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ውሳኔን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ግፊት እና ቁርጠኝነት ይጠይቃል!

በቸር እንሰንብት!!

Filed in: Amharic