>

መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ ነገስቱ በጄኔራል ካኒንግሀም እገዛ ጣሊያንን ከመዲናዋ ያስለቀቁበት ዕለት ...!!! (ታሪክን ወደኋላ)

መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ ነገስቱ በጄኔራል ካኒንግሀም እገዛ ጣሊያንን ከመዲናዋ ያስለቀቁበት ዕለት …!!!
ታሪክን ወደኋላ
 በዛሬዋ ዕለት 

ከ 81 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ዘመን በኋላ በኢትዮጵያ አርበኞች ትግል እና በብሪታኒያዊው የጦር መሪ ጄነራል ውንጌት የፋሺስት የኢጣሊያን ጦር ሠራዊት ድል እየመቱ በሱዳን (ኦሜድላ) በኩል ደብረ ማርቆስ የደረሱበት ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን ጦር እያገዘ በደቡብ አቅጣጫ በሱማሊያ በኩል የዘመተው በእንግሊዙ የጦር መሪው ጄኔራል ካኒንግሀም አማካኝነት አዲስ አበባን በመቆጣጠር ጣሊያንን ከመዲናዋ ከተማ ያስለቀቁበት ዕለት ነበር።
….አንድ ቀን ጠንከር ያለ ሁካታ ያለበት ድምፅ ሰማን ሳጥኗን (ሬድዮን) ቀስ ብዬ ላስተካክላት ሞከርኩ፡፡ ሁካታው ግን እየበረታ መጣ አልፎ አልፎ ኢትዮጲያ ኢትዮጲያ የሚል የብዙ ሺህ ህዝብ ድምፅ ድንፋታ ይሰማል፡፡ ቀጥሎም የሞሶሎኒ ድንፋታ ጀመረ..አርባ አመት ጠብቀናል በቃ አለቀ! ሞሶሎኒ የኢትዮጲያን ስም በጠራ ቁጥር በፓላዞ አደባባይ የተሰበሰበው ህዝብ ይጮሃል፤ በዚያች ሳጥን የሚጮኸው ህዝብ ደስተኛ ይመስላል፡፡ እኔና ወዳጆቼም የሆነ ነገር ይወረን ጀመር፡፡ እየወረረን ያለው ስሜት ግን ደስተኛ አልነበረም፡፡ ወዳጆቼም ዛሬ ትርጓሜ አላስፈለጋቸውም፡፡ ገብቷቸዋል፡፡ ‹‹መጣሁ ማለቱ ነው ይኄ ሙሶሎኒ ›› አሉና ድንገት ብድግ ብለው ወደ ሰፈራቸው ሄዱ፡፡
ኢትዮጲያን ማንም አይረዳትም ብቻዋን ናት፡፡ ሞሶሎኒ ሀሳቡን እንደገና እንዲያይ የሩሲያ የማስፈራሪያ ቃል አላቀመውም፡፡ ምን ያድርግ ፈረንሳዮችና እንግሊዞች አይዞህ ከእግዚአብሔር የተሰጠህ ቅዱስ መብትህ ነው ብለውታል፡፡ አሜሪካም ሳትቀር በተዘዋዋሪ ደግፋዋለች፡፡ አርፈሽ ተቀመጪ ይኼ ነፃነት ነፃነት የምትይው  ትግልና መፈራገጥ ለመላላጥ ነው ብላታለች አይ ኢትዮጲያ!
በደብረ ታቦር ያለሁ ብቸኛ አውሮፓዊ መሆኔ ሲታወቀኝ ሀዘን ተሰማኝ፡፡ ወዲያው ለዚች የተቀደሰች ሀገር ከእነዚህ ምስኪን የገበሬ  ወታደሮች ጎን በታላቅ ድፍረትና ጀግንነት መውደቅ በእግዚአብሔር የሚታደሉት ታላቅ ፀጋ መሆኑን ስረዳ ልቤ በደስታ ተሞላች ከዚች ቅፅበት ጀምሮ ኢትዮጲያዊ ሆኛለሁ፡፡ አዎ! ያ ወጣት እንዳለው የሀገሬን ድንበር ጥሶ የሚመጣን ወራሪ ጦር እንደቆሎ እቆላዋለሁ፡፡ እንደ ሙጃ እዘረጋዋለሁ አጭደዋለሁ……
* አዶልፍ ፓርለሳክ የቼክ ሪፐብሊክ ተወላጅ
– ሃበሽስካ ኦዴሳ (የሀበሻ ጀብዱ)
ትርጉም በተጫኔ  ጀብሬ መኮንን ገፅ  57)
ኢጣሊያ በአድዋ ጦርነት የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል አርባ አመት ሙሉ ጦሯን አደራጅታ በ 1928 ዓ.ም በሞሦሎኒ ትዕዛዝ ዳግመኛ ኢትዮጵያን ወረረች። በወቅቱ ሁሉም  ለሀገሩ ክብር በየዱር ገደሉ ሸፍቶ ዘመናዊ መሣሪያ ካነገተ ዕልፍ ጦር ጋር ገጥሞ አምስት አመት ከተዋጋ በኃላ ሀገር ነፃ ወጣች::
ክብርና ሞገስ ለጀግኖች አርበኞቻችን 🙏
Filed in: Amharic