ትናንት ማታ ከእስክንድር ጋር የተገናኘው ጋዜጠኛ ፋና አለኝ የለኝም የሚለው ጋዜጠኛ መሰለኝ። ለምን መሰለኝ? በምርጫ ክርክሩ ወቅት ጠበቅ ባሉ አጀንዳዎች ዙሪያ ከበድ ካሉ ፖለቲከኞች ጋር ውይይት/ክርክር ሚደረግ ቀን ” moderate” ለማድረግ፣ጥያቄዎችንም ለመሰንዘር የሚሰየመው እሱ ስለሆነ ነው። አሁን እስክንድር ጋ የተገናኘውም በዚሁ እሳቤ መሰለኝ።
ከእስክንድር ጋር ተገናኝቶ ያደረገው ክርክር ይሁን ልብ ማውለቅ ያልለዬ ነገር ምክንያቱ ከጋዜጠኛው የተነሳ አይደለም -ከፋና ዘዋሪ መኳንንት የተነሳ እንጅ! በካድሬው ዓለም እንደ “genius” የሚቆጠረው ጋዜጠኛ ‘ሄደህ አፋጠው’ ተብሎ ነው የተላከው። ለዚህ ነው የሆነውን ሲሆን ያመሸው።
የጋዜጠኛው ልብ ማውለቅ ግን ወዶ ያደረገው ነገር እንዳልሆነ የሚያስታውቀው መሃል ላይ በእስክንድር ገለፃ ምስጥ ጭልጥ ሲል ነው። ስለዚህ በጋዜጠኛው ላይ ብዙ መቆጣት ተገቢ አይመስለኝም። ተገቢው ነገር በጋዜጠኛው ውስጥ የመንግስት ማዲያዎች ያሉበትን እስር ማጤን ነው። ነገሩ ከግለሰብ ጋዜጠኛ ጋር የሚገናኝ አይደለም።
እስክንድር እውነትን በእውቀት እና በጨዋ አንደበት ገልጿል። በበኩሌ ብዙነገሮች ተምሬያለሁ። በተለይ የፖለቲካ ጥያቄ እና መልሱ ከአስተዳደራዊ ጥያቄ እና መልሱ ጋር ያለውን ልዩነት ያስቀመጠበት መንገድ፣የጉልበት ጭፍለቃንና የታሪክ እውነታ ያመጣቸውን ማህበራዊ መወራረሶችን ልዩነቶች ያስቀመጠበት መንገድ ድንቅ ነው!!! በስራ ቋንቋ ፣በብሄራዊ ቋንቋ እና በትምህርት ቋንቋ መካከል ያለውን መስተጋብር ስንሰማው ከወሰነው የካድሬ አደንቋሪ ጩኸት በተለዬ ሁኔታ ያቀረበበት መንገድ ግሩም ነበር። እስክንድር በማንም የት ቢያቀርቡት የማያሳፍር ግንዛቤ ያለው ሰው እንደሆነ በግሌ ድሮም የማውቀው ሃቅ ነው ።
እስክንድር የተናገረውን ሁሉ ሲናገር ፈርጠም ብሎ ግን በትህትና ነበርና እግረ መንገዱንም ትህትና ማለት መልመጥመጥ አለመሆኑን መማር ለሚፈልግ ሁሉ አስተምሯል።