>

የብልጽግናው አካሄድ ወደፊት ኢትዮጲያዊ መልክ ያለውን ከተማ ሙሉ ለሙሉ የማጣት ስጋት ያሳድራል...!!! (ምኒልክ ሳልሳዊ)

የብልጽግናው አካሄድ ወደፊት ኢትዮጲያዊ መልክ ያለውን ከተማ ሙሉ ለሙሉ የማጣት ስጋት ያሳድራል…!!!
ምኒልክ ሳልሳዊ

 

*… የዕውነታው አንዱ ጫፍ … 
 
ወደ አዲስአበባ ከተማ ፍልሰት
፦ከተማዋ በታላቅ የህዝብ ብዛት ተጨናንቃለች።
፦ከአራቱም አቅጣጫ ዜጎች ይጎርፉባታል።
፦በመልካም አስተዳደር ችግር፣በሌብነት፣በዘረኝነት፣በጥላቻ ምክንያት ዜጎች ከኖሩበት ተስፋ በማጣት የሚሸሹባት ከተማ ሆናለች።
፦በልመና፣በቀን ሥራ፣በሴተኛ አዳሪነት፣በስርቆት፣በጎዳና አዳሪነት በመሳሰሉት ፈፅሞ አማራጭ በማጣት ሳይወዱ በግድ ኢትዮጲያዊያን የሚሸሸጉባት ከተማ ሆናለች።
፦በአሁን ሰዓት የትኛውም የኢትዮጲያ ከተማ ያለሥጋት የሚኖሩበት አልሆነም።
ወይም እንደ ዜጋ ሰው ተወዳድሮ በዕውቀቱና በችሎታው ሳይሆን ሥራ የሚያገኘው በዘር ኮታ ወይም በፖለቲካ አጎብዳጅነት ነው።
፦ለመኖር እንኳን በርካታ ከተሞች የዚያ ከተማ ብሔር ተወላጅ ካልሆኑ እንደ ሁለተኛ ሦስተኛ ዜጋ የሚታዩ በመሆናቸው ያለው ምርጫ ፍልሰት ሆኗል።
፦በሌሎች አገሮች የምንሰማውና የምናየው የከተማ ዘራፊዎች፣የማፍያ ቡድኖች ነገ በከተማዋ ላለመፈጠራቸው ምንም ማረጋገጫ የለም።
ዛሬ በአገሪቱ በአንፃራዊነት ሠላም የሰፈነባትና የብሔር ብሔረሰቦች መልክ ያላት ኢትዮጲያዊ ከተማ አዲስአበባ ከተማ ብቻ ናት ቢባል አልተጋነነም።
እሷንም የኦሮሞ ብልፅግናና ሸኔዎች በዲሞክራፊ መንገድ ሁሉም የእኛ በሚል እሳቤ በከተማዋ ከላይ እስከ ታች አንድ ቋንቋ ተናጋሪን እየሰገሰጉ በሌሎች ከተሞች የተመለከትነውን የተበላሸ አሰራርን እያስፋፉ በመሆናቸው ወደፊት ኢትዮጲያዊ መልክ ያለውን ከተማ ሙሉ ለሙሉ የማጣት ስጋት ያሳድራል ።
ያም ሆነ ይህ ዛሬ ከተማዋ አማራጭ ባጡ ዜጎቿ ልትፈነዳ ደርሳለች ከመላው አገሪቱ ወጣቱ ትኩስ ሃይል የሆነው ትውልድ እየተሰደደባት እንጄራ የሚናፍቅባት ሆናለች።
በሞላው አገሪቱ የተንሰራፋው ዘረኝነት፣ሥራን ማግኘት የፖለቲካ አባል ወይም በገንዘብ አልያም በጎሳ መሆኑ የግድ አስፈላጊ በሆነበት ዘመን ዜጎች አማራጭ በማጣት በትንሹም የቀን ሥራ ሠርተው ዳቦ ለመብላት ወደ ከተማዋ በከፍተኛ ቁጥር መፍለሳቸው ነገሩን አስፈሪ ያደርገዋል።
በተለይ ከደቡብ፣ትግራይ፣አማራ፣ሲዳማ፣ኦሮሚያ፣የሚደረገው ስደት በክልሎቹ ያለውን የተበላሸ አሰራርና ኢፍትሐዊነት በግልፅ የሚያሳይ ሲሆን መንግስት ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ መፍትሔ ካላበጀ አደጋው የከፋ ይሆናል የሚል ፍርሃት አለ።
የዕውነታው አንዱ ጫፍ … 
በፖለቲካና የኢኮኖሚ አሸጥር ተብትቦ …. የየትኛው አገር መንግስት ነው የዜጎቹን ሰላም የሚነሳው ? የየትኛው አገር የመንግስት መዋቅር ነው ታጣቂዎችን እያስታጠቀና በሎጀስቲክ እየረዳ የሃገርንና የህዝብን ደሕንነት ዋስትና የሚያሳጣው ? መንግስት ሃገር ማስተዳደር አልቻለም። ባለስልጣናት ሕዝብን ከፖለቲካና ኢኮኖሚ አሻጥር ውጪ እንደ አገልጋይ መምራት አልቻሉም።
መንግስት ከሚያስተዳድረው ይልቅ የማያስተዳድረው የኢትዮጵያ ክፍሎች ይበልጣሉ። በስርዐት አልበኞችና በሕገወጥ ታጣቂዎች ተወረናል። ……. በየትኛው አገር ነው የሕግ የበላይነትን ያላረጋገጠ መንግስት ስለ ሰላምና ልማት የሚሰብከው። ስርዐት አልበኝነትንና ሕገወጥነትን የሚፈጥሩ ባለስልጣናትን ታቅፎ ሕዝብን እያሸበሩ የሚኖሩ ባለስልጣናትን ተሸክሞ የሚያስተዳድረውን አገር የጦርነት ቀጠና ያደረገ መንግስት የለም።
በየቀኑ የምንሰማው ዜናኮ የሕዝብ ሰላምና ደሕንነት መደፍረሱ አገር በተኩስ መናወጡንና የዋጋ ንረት የህዝብ መፈናቀል ብቻ ነው። ሕዝብ ሰላማዊ ዜና መስማት ናፍቆታል። በመንግስት ሚዲያዎች የሚተላለፉ የውሸት ክምሮች የመንግስትን እኩይ ገበና ከማጋለጥ አልዘለሉም። በተራዉ ዜጋና በባለስልጣናት፣ በድሆችና ሐብታሞች መካከል የሚታየዉ እጅግ የሰፋ የኑሮ ተባለጥ ችግረኞች የአመፅና ዘረፋ አማራጭን እንዲያማትሩ እያስገደደ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣዉ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ሕዝቡን ክፉኛ እያስጨነቀ፣ አንዳንዶችን ደግሞ ለተመፅዋችነት እየዳረገ ነዉ። ይህ ችግር የባለስልጣናት የአስተዳደር ውጤት እንጂ ሃገርና ሕዝብ የፈጠረው ችግር አይደለም።
የመንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል እያስታጠቁ ንፁሃንን ከማስገደልና ከማፈናቀል አልበቃ ብሏቸው ወደ ደቡብ ክልል በመግባትም ህዝብን እያስገደሉ እያፈናቀሉና ንብረት እያወደሙ ነው። በመንግስት ባለስልጣናት የሎጀስቲክ አቅርቦት የሚደረግላቸው ታጣቂዎች አንዴ ዞን አንዴ ክልል እንሁን በሚል ህዝብን በታጠቁት መሳሪያ እየፈጁ ነው። ይህ ደግሞ መንግስት የሚከተለው የፖሊሲ ውጤት አንዱ ማሳያ ነው። ደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር ፍላጎት አላቸው የተባሉ ታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ፈፀሙ…. ታጣቂዎች እየተኮሱ ወደ መንደሩ በመዝለቅ ቤቶችን ማቃጥል ሲጀምሩ … በደረሰ ጥቃት ከ32ሺ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ፡፡ የሚል ዘገባ ያደመጥነው ዛሬ ነው። ይህ የመንግስትን የፖሊሲ ደካማነት ያሳያል።
መንግስት ከሚያስተዳድረው ይልቅ የማያስተዳድረው የኢትዮጵያ ክፍሎች ይበልጣሉ። በስርዐት አልበኞችና በሕገወጥ ታጣቂዎች ተወረናል። የሚገርመው የመንግስት መዋቅሩ ከነዚህ ስርዐት አልበኞች ጋር የፈጠረው ኝኑነት ነው ሕዝብን እየጎዳው ያለው። አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ በመግለጫ የሚያወራው መንግስት በተግባር ዘምቶ ስርዐት አልበኝነትንና ሕገወጥነትን የማጥፋትና ዜጎች በሰላም የመኖር መብታቸውን ሊያረጋግጥ ግዴታ አለበት ። ብልጽግና ላይ ነን ! ሃገርን እያቃጠለ ነው !
Filed in: Amharic