>
5:13 pm - Monday April 19, 8100

የሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መታሰቢያ...!!! ልኡል አምደጽዮን

የሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መታሰቢያ…!!!

ልኡል አምደጽዮን

በፀረ-ፋሺስት ትግሉ ወቅት መተኪያ የማይገኝለት የነፃነት ተጋድሎ ያደረጉትና በኋላም በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው አገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉት ጀግናው አርበኛ ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ያረፉት ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት (መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም) ነው፡፡
ጃገማ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም በጅባትና ሜጫ አውራጃ፣ በደንዲ ወረዳ ዮብዶ በተባለ ስፍራ ተወለደ፡፡ አባቱ ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) ሕፃኑ መወለድ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ አሳደረባቸው፡፡ ‹‹ … ለሰባ ዓመታት ሙሉ የጠበቅሁት አንበሳ ይህ ነው … የፈረሴን ስም ሰጥቸዋለሁ›› ብለው ‹‹ጃገማ›› ብለው ስም አወጡለት፡፡ የቤተሰቡ ሁሉ አለቃ አድርገውም ሾሙት፡፡ ጃጋማ በተወለደ በዓመቱ እናቱ ወይዘሮ ደላንዱ በአካባቢው ተከስቶ በነበረ በሽታ ምክንያት በመሞታቸው በአክስቱና በሞግዚት እንዲያድግ አባቱ ወሰኑ፡፡ አክስቱም ጃገማን ከወንድሙ ጋር ፀበል አስጠምቀው፤ቄስ ቀጥረው ዳዊት እንዲማር አደረጉ፡፡ በ1923 ዓ.ም ደግሞ አባቱ ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) አረፉ፡፡
ጃገማ ገና በለጋ እድሜው ‹‹አባቱ የመረጠው›› እየተባለ ለዳኝነት መቀመጥን፣ ፈረስ ግልቢያን፣ ጦር ውርወራን፣ ምክክቶሽን፣ ጋሻ አነጋገብን፣ ረሀብንና ውሃ ጥምን መቋቋምን፣ ውሃ ዋናን … እየተማረ በጥሩ ስነ ምግባር አደገ፡፡ በልጅነት ዘመኑ ስለቅድመ አያቱ ጎዳና ነሞ የጀግንነት ታሪክ በተደጋጋሚ ስለሰማ እርሱም እንደቅድመ አያቱ ጀግና መሆንን ያልም ነበር፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ጃገማ አርበኛ ሆኖ የፋሺስትን ጦር ለመፋለም ወሰነ፡፡ ከአጎቱን ልጅ አሰፋ አባ ዶዮ ጋር ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እህቱና ወንድሞቹም ተከተሉት፡፡ ገበሬዎች፣ ወታደሮች፣ ሾፌሮች … ከጃገማ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ አሰፋ አባ ዶዮን ጨምሮ መጀመሪያ ከጃገማ ጋር ለአርበኝነት የወጡ ብዙ ወጣቶች በቤተሰቦቻቸው ተግሳፅ አማካኝነት ከጫካ ወጥተው ወደ መንደራቸው ቢመለሱም የ15 ዓመቱ ጃገማ ከእርሱ በእድሜም ሆነ በሌሎች ነገሮች የሚበልጡ በርካታ ሰዎችን በስሩ ማሰለፍ ቻለ፡፡
የጃጋማ አባት በአካባቢው ዘንድ ይወደዱና ይከበሩ ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በታዳጊው ጃገማ የሚመሩትን አርበኞች በልዩ ልዩ መንገዶች ያግዝ ነበር፡፡ አርበኞቹም በፋሺስት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ጦሩን መፈተን ጀመሩ፡፡ ፋሺስቶች ጥይት የሚጭኑባቸውን እንስሳት በመምታት ፋሺስቶችና ባንዳዎች ሲሸሹ አርበኞቹ መሳሪያና ጥይት እየሰበሰቡ ማከማቸት ቀጠሉ፡፡ ጣሊያኖችም ጃገማንና ተከታዮቹን ለመደምሰስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡
አርበኞቹ በጊንጪና አካባቢው በነበረው የፋሺስት ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘራቸው ጣሊያኖች በጊንጪና በአካባቢው ጠንካራ ምሽግ ሰርተውና ጦራቸውን ጠምደው ተቀመጡ፡፡ ሐሮታና ጀልዱ የነበረው የጠላት ጦር ግንኙነት ፈጥሮ ስለነበር አርበኞቹ መተላለፊያ መስመሩን ለመቁረጥ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ ከጥቃቱ ባገኙት መሳሪያም ትጥቃቸውን አጠናከሩ፡፡ የጃገማ ተከታዮች ቁጥራቸው ጨመረ፡፡ ፋሺስቶች ተጨማሪ ምሽጎችን ለመገንባት ቢያስቡም ቀድመው በገነቧቸው ምሽጎች ውስጥም እንደልባቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ አርበኞቹ በሚያዝያ ወር 1931 ዓ.ም ሐሮታና ጀልዱ የነበረውን የጠላት ጦር ግንኙነት ለመበጣጠስ የወሰዷቸው እርምጃዎች አዲስ አበባ ድረስ ተሰሙ፤ብዙ የነፃነት ተዋጊዎችም እነጃገማ ያሉበት ድረስ ሄደው ተቀላቀሉ፡፡
በአንድ ወቅት ጃገማ ከጭልሞ ወደ አሬራ ሲሄድ ጊንጪ ገበያ ውለው ወደ ጭልሞ ሲሄዱ የነበሩ ገበሬዎች በሽፍቶች ሲዘረፉ ተመለከተ፡፡ ጃገማ ተወርውሮ ሄዶ ዘራፊዎቹን በማባረር የገበሬዎቹን ንብረት አስመለሰ፡፡ በወቅቱ ጃገማን ያዩት ፋሺስቶችና ባንዳዎችም በጃገማ ላይ አደጋ ለመጣል ሞክረው የጃገማ አስደናቂ አፀፋ ለቁስለኛነትና ለሽሽት ዳረጋቸው፡፡ በአካባቢው የነበረው የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ስለሁኔታው ሰምቶ ለጃገማ ደብዳቤ ፃፈለት፡፡ የደብዳቤው ይዘትም ጃገማ የገበሬዎቹን ንብረት ማስመለሱ መልካም እንደሆነ፣ ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ የኢጣሊያ መንግሥት እንደማይጠይቀውና ምኅረት ስለተደረገለት በአካባቢው ለሚገኘው የኢጣሊያ ጦር እጁን እንዲሰጥ የሚገልፅ ነበር፡፡ ጃገማም ደብዳቤውን ተመልክቶ ‹‹ … ከሰው አገር ላይ መጥቶ፤የሰው መሬት ወስዶ … ‹ሙሉ ምኅረት ተደርጎልሃልና ግባ› አለኝ፡፡ አነዚህ ደፋሮችና ግፈኞች አገሬን ለቀው እስካልሄዱ ድረስ አይማረኝ ብምራቸው›› አለ ለጓደኞቹ፡፡ ‹‹እኔ የማውቀው ምኅረት ሰጪ አንድ ፈጣሪን ነው፡፡ ሰው ምኅረት የሚሰጥ ከሆነ ግን ምኅረት ሰጪው አገር የወረረ ሳይሆን አገሩ የተወረረበት እኔ ነኝ›› ብሎ የመልስ ደብዳቤ ላከ፡፡
በጃገማ የሚመራው የአርበኞች ጦር ምዕራብ ሸዋ በነበረው የኢጣሊያ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ብዙ ጉዳቶችን አደረሰበት፡፡ አርበኞቹ ድንገተኛ ጥቃቶችን ሰንዝሮ በፍጥነት ከአካባቢው በመሰወር የጠላት ጦር ጥይት እንዲያባክን በማድረግ፣ የአካባቢው ሰው ከፋሺስት ወታደሮችና ከባንዳዎች ላይ ጥይት እንዲገዛ በማስተባበርና ጥይት በጫኑ እንስሳት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ጥይቱን በመውሰድ የመሳሪያ ክምችታቸውን ያጠናክሩ ነበር፡፡
በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማን ለማጥቃት ወደ ሰንጎታ ተራራ የሄደው 350 የፋሺስት ጦር ጃገማ በሚመራቸው 17 አርበኞች ተሸነፈ፡፡ የጃገማ አርበኞች ብዙ የጠላት ወታደሮችን ገደሉ፤ባንዳዎች የዘረፉትን ንብረት አስመለሱ፤ወታደሮችንና መሳሪያ ማረኩ፡፡ የጃገማ ጀግንነትም እየገዘፈ ሄደ፡፡ የአካባቢው ሕዝብም የጃገማን ጀግንነት ከቅድመ አያቱ ጀግንነት ጋር እያነፃፀረ በማውራት በጠላት ጦር ካምፕ ውስጥ ፍርሃቱ እንዲጨምር አደረገ፡፡ ወደ ወሊሶ ሄዶ በአካባቢው ከፋሺስት ጦር ጋር ሲዋጉ ወደነበሩት ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዘንድ ሄደ፡፡ የፋሺስት ጦር በደጃዝማች ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ ስለነበር ጃገማም በውጊያው ላይ ተሳትፎ የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ፡፡ ደጃዝማች ገረሱም ‹‹ … አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ …›› ብለው ጃገማን አመሰገኑት፡፡
ወለንኮሚ ላይ የተደረገው ጦርነት ጃገማ እጅግ አስገራሚ የውጊያ ብቃቱን ያሳየበት ሌላው ውጊያ ነበር፡፡ ከጠላት በኩል አንድ ሺ 500 እግረኛና 800 ፈረሰኛ የተሳተፈበት ጦርነት ቀኑን ሙሉ ተካሂዶ በነጃገማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከወለንኮሚ ጦርነት በኋላ ፋሺስቶች ጃገማንና አርበኞቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እስከ 15ሺ የሚደርስ ጦር አሰማራ፡፡ ጃገማንና አርበኞቹን ፍለጋው ቀጠለ … ግን አልተሳካም፡፡ የፋሺስት ጦር በፍለጋው ተሰላችቶ በተቀመጠበት ሰዓት ጃገማና አርበኞቹ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው የፋሺስትን ጦር አስደነገጡት፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውጊያ ሰንብተው ከ15 ቀናት በኋላ አርበኞች የጠላትን ጦር እስከ ግንደበረት ድረስ ሳቡት፡፡ አርበኞቹ የፋሺስትን ጦር በዘዴ አስቸጋሪ መልዕክዓምድር ላይ መስደው ተኩስ ከፈቱበት፡፡ ከሞት የተረፈው የጠላት ጦር ሸሸ፡፡
ጃገማ በአንድ ውጊያ ላይ የማረከውን የኢጣሊያ ወታደር እንዳይገደል አድርጎ ስለአርበኞቹ ኃይል እንዲሁም ስለፋሺስቶች ፈሪነትና አረመኔነት ከነገረው በኋላ ‹‹ከምርኮኝነት ነፃ የምትወጣው ለጥይት መግዣ የሚሆነኝን 10ሺ ሊሬ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው›› አለው፡፡ በአንድ ኢጣሊያዊ መልዕክተኛ አማካኝነት ጃገማ 10ሺ ሊሬ ተቀብሎ ምርኮኛውን ፈታው፡፡ ምርኮኛውም ወደጦር ሰፈሩ ሄዶ ስለጃገማ ጀግንነት ለአለቆቹ ሲነግራቸው ደስ ባለመሰኘታቸው ወደ ሌላ ስፍራ አዛውረውታል፡፡
ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ጃገማ ደጃዝማች ገረሱን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት ‹‹ … ጃገማ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና …›› የሚል መልዕክት ከስመ ጥሯ የውስጥ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው፡፡ ጃገማም በፍጥነት ወደ አዲስ ዓለም አቅንቶ የምሽግ ሰበራው የጦር አዝማች ሆነ፡፡ ጥቃቱን አፈፃፀም የሚያሳይ መመሪያ ለባልደረቦቹ አስረድቶ የሥምሪት ትዕዛዞችን ሰጠ፡፡ ራሱ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ ቦምብና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለስልጣናትን ገድሎ የመሳሪያ ዝርፊያው እንዲፈጸም አደረገ፤እስረኞችንም አስፈታ፡፡ በዘመቻው ላይ ከአርበኞቹ ወገን የሞቱት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ከጠላት ወገን ግን ከ100 በላይ ጣሊያናውያንና ጠባቂዎቻቸው ተገድለዋል፡፡
በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማ የጭልሞን ምሽግ ከቦ በፋሺስት ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ፡፡ ‹‹እጃችሁን ካልሰጣችሁ አንላቀቅም!›› የሚል መልዕክትም አስተላለፈ፡፡ ‹‹እንደራደርና እጅ እንሰጣለን›› ካሉ በኋላ አዘናግተው ሊያመልጡ ሲሉ ከአርበኞቹ ተኩስ ተከፈተባቸውና 13 የኢጣሊያ ወታደሮችና አንድ ሺ 500 ባንዳዎች ተማረኩ፡፡ ጊንጪ በጃገማ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ ወዲያውኑም ጃገማ የኢጣሊያ ጦር የሚተማመንበት የሐሮታ ምሽግ ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዘዘ፡፡ የጠላት ጦር አንድ ጊዜ እየሸሸ፤ሌላ ጊዜ እያጠቃ መፋለሙን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ጃገማ ብቻውን ሆኖ ቦታ እየቀያየረ መድፍ ሲተኩስ የፋሺስት ጦር ተስፋ ቆርጦ ለመጨረሻ ጊዜ ሸሸ፤ከሞት የተረፈውም ተማረከ፡፡ የጃገማ ጦር በድል አዲስ ዓለም ገባ፡፡ ሆለታንም በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀልዱ ላይ ምሽጉን አጠናክሮ ለቀናት ሲዋጋ የነበረው የፋሺስት ጦር ‹‹የጦሩ መሪ ‹ጃገማ ኬሎ ካልመጣ እዚሁ እናልቃለን እንጂ እጃችንን አንሰጥም› ተብሏል›› ስተባለ ጃገማ ወደ ጀልዱ ሄዶ የኢጣሊያ ወታደሮችንና ባንዳዎችን ማርኮ ወደ ጊንጪ ተመለሰ፡፡ የአካባቢው ሽማግሌዎችም ‹‹አምስት ዓመታት ሙሉ መርተህ፣ ተዋግተህና አዋግተህ ለነፃነት አብቅተኸናልና እንድንሾምህ ፍቀድልን›› ሲሉት ‹‹አልፈልግም! የምፈልገው ሆኗል፡፡ ስራዬ በስሜ ከተጠራ ይበቃኛል›› ብሎ መለሰ፡፡
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስደት ተመልሰው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ጅማና አካባቢው በፋሺስቶች ቁጥጥር ስር ስለነበር ጦሩን የሚወጋ ኃይል ተፈለገ፡፡ ደጃዝማች ገረሱ ጃገማ እንዲጨመርላቸው ለንጉሰ ነገሥቱ ተናገሩ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱም ለጃገማ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ጃገማ ግን ትዕዛዙን መቀበል አልፈለገም ነበር፡፡ እጅ ሊነሱ ወደ አዲስ አበባ ሄደው የነበሩት የውስጥ አርበኛዋ ወይዘሮ ሸዋረገድ ስለጃገማ ለንጉሰ ነገሥቱ ነገሯቸው፡፡ ወይዘሮ ሸዋረገድ ለጃገማ ጀግንነት ትልቅ አድናቆት ነበራቸው፡፡ ጃገማ ከሚያደንቋቸው አርበኞች መካል ወይዘሮ ሸዋረገድ አንዷ ናቸው፡፡
ንጉሰ ነገሥቱ በሰኔ ወር 1933 ዓ.ም ጊንጪን በጎበኙበት ወቅት ጃገማ ንጉሰ ነገሥቱ የሚቆሙበት ሰገነት አሰርቶ ጠበቃቸው፤አርበኞቹን አሰልፎ አቀባበል አደረገላቸው፡፡ ወደ አዲስ አበባም ይዘውት ሄደው ገበርዲን ሙሉ ልብስ፣ የወርቅ ሰዓትና 16ሺ ብር ሸለሙት፡፡ ከዚያም ወደ ጅማ ሄዶ በጀኔራል ጋዚራ የሚመራው ጦር እንዲማረክ አደረገ፡፡ ወደ አጋሮ በመሄድም ለሦስት ቀናት ያህል ከፋሺስቶች ጋር ከተዋጋ በኋላ 500 ጣሊያናውያንንና አንድ ሺ 500 የባንዳ ወታደሮችን ከነአዛዣቸው ማረከ፡፡
በጅማና አካባቢው ስለፈጸመው የጀግንነት ተግባርም ንጉሰ ነገሥቱ አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን ገልጸው ወደ ጎሬ እንዲዘምት ባዘዙት መሰረት ወደቦታው ዘምቶ ከራስ መስፍን ጦር ጋር በመሆን በአካባቢው የነበረውን የጠላት ጦር ደመሰሱት፡፡ አርበኞች የያዟቸውን አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ እያስጠበቁ እንዲያስተዳድሩ ትዕዛዝ ተላልፎ ስለነበር ጃገማ ጌራን፣ ጉማይን፣ በደሌንና አጋሮን ማስተዳደር ጀመረ፡፡
በመስከረም ወር 1934 ዓ.ም ጃገማ ታሞ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት ንጉሰ ነገሥቱ ከተኛበት ጎጆ ድረስ ሄደው ጠይቀውታል፡፡ በወቅቱ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ይመለከተው የነበረው የሥልጣን ሽኩቻና የመኳንንት ባህርይ ለጃገማ ምቾት የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ጃገማ ለአምስት ዓመታት ያህል በዱር በገደሉ፤በቀንና በሌሊት፣ በዝናብና በፀሐይ … አብረውት ሲዋጉ የነበሩት አርበኞቹ ቋሚ መተዳደሪያ እንዲያገኙ ለንጉሰ ነገሥቱ ጥያቄ አቅርቦ ጥያቄው ተፈፅሞለታል፡፡
ከግንቦት 1934 ዓ.ም ጀምሮ ሆለታ ገነት ጦር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት የውትድርና ስልጠና አጠናቆ የሻለቃነት ማዕረግ አገኘ፡፡ ከዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል በአምቦና በቢሾፍቱ ተመድቦ አገልግሏል፡፡ ከዚያም በአምባላጌና በራያ አዘቦ በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ባሳየው ብቃት በሜጀር ጀኔራል አበበ ዳምጠው ተመስክሮለት ሻለቃ ጃገማ የብርጌድ አዛዥ ሆኖ ተሾመ፡፡ የሻለቃ ጃገማ ጀግንነት በአልጋ ወራሽ ልዑል አስፋወሰን ኃይለሥላሴና በጦር ሚኒስትሩ በራስ አበበ አረጋይ ጭምር የታወቀና የተመሰከረለት ነበር፡፡ ሻላቃ ጃገማ የስድስተኛ ብርጌድ አዛዥ ሆኖ ተሹሞ ወደ ደሴ ተዛወረ፡፡ ሕዝባዊ ጦር፣ መደበኛ ጦር እና የኢትዮጵያ ጦር የተባሉት የጦር ክፍሎች በጦር ሚኒስቴር ስር ሆነው ሲቀላቀሉ የአምስተኛ ብርጌድ አዛዥ ሆኖ ተሾመ፡፡
በ1947 ዓ.ም የሌተናንት ኮሎኔልነት ማዕረግን አገኘ፡፡ የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ማርሻል ቲቶ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የተደረገላቸውን የክብር ሰልፍ የመሩት ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ነበሩ፡፡ ዩጎዝላቪያን ጎብኝተውም ነበር፡፡ በ1940 ዓ.ም የሰባተኛ ብርጌድ አዛዥ ሆነው ወደ አዲግራት ተላኩ፡፡ በቦታውም የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማሰራት ሰራዊቱ አካሉንና አዕምሮውን በስፖርት እንዲገነባ አድርገዋል፡፡ እርሳቸውም በኢላማ ተኩስ፣ በዝላይና በጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች በማሸነፋቸው ሽልማቶችን ከንጉሰ ነገሥቱ እጅ ተቀብለዋል፡፡ ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ የሰባተኛ ብርጌድ አዛዥ በነበሩበት ወቅት በእንግሊዞች ቁጥጥር ስር የነበረችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ብርቱ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡
በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ለማክሸፍ ለጥቃት የተንቀሳቀሰው ኃይል አዛዥ ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ኬሎ ነበሩ፡፡ በ1954 ዓ.ም በብርጋዴር ጀኔራል ማዕረግ የአራተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሆነው ተሾሙ፡፡ በወቅቱ ውሃ ዋና የሚችሉ ወታደሮችን መርጠው እንዲሰለጥኑ በማድረግ ክፍለ ጦራቸው በውሃ ዋና ውድድር ባሕር ኃይልን አሸንፎ ዋንጫ ባለቤት እንዲሆን ያደርጉ ነበር፡፡ የመቻል ስፖርት ክለብ ፕሬዝደንት፣ የጦር ኃይሎች ስፖርት መሪ እንዲሁም እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የመኮንኖች ክለብ ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1958 ዓ.ም የሜጀር ጀኔራልነት ማዕረግን አግኝተዋል፡፡
በ1962 ዓ.ም በባሌ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን አመፅ ለማረጋጋት ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ ታዘዙ፡፡ ሜጀር ጀኔራል ጃገማም አካባቢውን አረጋግተው የአመፁ መሪዎች ምኅረት እንዲያገኙ አደረጉ፡፡ አካባቢውን የማረጋጋት ስራቸው ከግምት ውስጥ ገብቶ የባሌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ተሹመውም አገልግለዋል፡፡ የሌተናል ጀኔራልነት ማዕረግን ያገኙት በ1963 ዓ.ም ሲሆን  በ1965 ዓ.ም ደግሞ የብሔራዊ ጦር አዛዥ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከዙፋናቸው አውርዶ ስልጣን በጨበጠው ደርግ ደስተኛ አልሆኑም፡፡ ደርግ የሕዝብ ደህንነት ኃላፊ ወይም የሲዳሞ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ያቀረበላቸውን ጥያቄም ውድቅ አደረጉት፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላ ስለንብ እርባታ ተምረው ለብዙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዘመናዊ ቀፎዎችን ሰርተውላቸዋል፡፡ በጊንጪ ዘመናዊ የከብት እርባታ ማዕከል አቋቁመዋል፡፡
ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ የኢትዮጵያን አንድነት በሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳታፊና ከፍተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ድርጅት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆንም ሠርተዋል፡፡ ለስራዎቻቸውም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡
በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ ዳማ›› የሚባሉት፣ ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ጀግናው ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው እሑድ፣ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ገሮ ጎዳና ነሞ
የኢትዮጵያ ኩራት!
Filed in: Amharic