>

"ሶላት ለመስገድ የሞከሩ የአዲስ አበባ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ለድብደባ እና ለእስር ተዳረጉ !!!" (ባልደራስ)

ሶላት ለመስገድ የሞከሩ የአዲስ አበባ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ለድብደባ እና ለእስር ተዳረጉ !!!”
ባልደራስ

የሙስሊም አባቶች የታሰሩትን አስፈትተዋል፣ ውዝግቡ ግን ቀጥሏል !!!
አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች የፀሎት ቦታዎች እና ሙስሊም እህቶቻችን የሚያደርጉት ሂጃብ መከልከላቸው አግባብ አይደለም የሚል ተቃውሞ እየተነሳ ነው፡፡ በያዝነው የረመዳን ጾም ወቅት፣ የሙስሊም ተማሪዎች በትምህርት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ለመስገድ ሞክረው በትምህርት ቤት አስተዳደሮች መከልከላቸው የሴኪውላሪዝምን መርህ በትክክል ካለመረዳት ነው የሚል ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ባለ አንድ ትምህርት ቤት በተነሳ ተቃውሞ ተማሪዎች እና ወላጆች ታስረው፣ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዘደንት ሸህ ሱልጣን እና ኡስታዝ መሀመድ አባተ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው አስፈትተዋቸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ዘገባ የሰራው ሃሩን ሚዲያ እንዳለው ከሆነ፣ በለሚ ኩራ ባለ ትምህርት ቤት  ከሶላት ጋር በተገናኘ በተፈጠረ ችግር በተማሪዎች ላይ እስር እና ድብደባ፣ በወላጆች ላይ የተኩስ እሩምታ ተፈጽሟል፡፡ ተማሪዎቹ “ወደ አዳራሽ ገብታችሁ እንወያይ” ከተባሉ በኋላ የጠበቃቸው እስር መሆኑን የተረዱት ወላጆቻቸው፣ “ልጆቻችን በጾመኛ አንጀታቸው ለእስር ሊዳረጉ አይገባም፣ ሶላት እንስገድ ማለታቸው ብቻ እንደ ወንጀል ሊታይ አይገባም” የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው፣ እነሱም ለእስር እና ለድብደባ እንደተዳረጉ ጣቢያው ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና በአስኮ በሚገኝ ትምህርት ቤትም የሙስሊም ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሲሰግዱ ተገኝተዋል በሚል፣ “ድጋሚ ሲሰግድ የተገኘ ተማሪ፣ ከትምህርት ቤት ይባረራል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ሲል ሃሩን ሚዲያ ዛሬ ዘግቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ አንዳንድ ተማሪዎች  በትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ሃይማኖትን መሠረት ባደረጉ እንቅቃሴዎች ለመሳተፍ ሙከራ የማድረግ አዝማሚያ ማሳየታቸው፣ ከውጭ ሆነው ተማሪዎቹን ወደ አላስፈላጊ ቦታዎች የሚገፉ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት መኖራቸውን አመላክቷል ብሏል፡፡ ይህ አባባሉ፣ መስተዳድሩ ከሁሉ ነገር በስተጀርባ ሴራ አለ እያለ የህዝብን ጥያቄ መግፋት የለመደ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ጥያቄው ትክክለኛ ህዝባዊ መሠረት እንዳለው ተቀብሎ ምላሽ መስጠት እንደሚገባው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
Filed in: Amharic