>
10:31 am - Tuesday March 21, 2023

ከጅምላ እስራችን በስተጀርባ ያለው የሴራ ፖለቲካ....!!! (ሰለሞን አለምኔ፣ የህሊና እስረኛ፣ ከአባ ሳሙኤል እስር ቤት!)

ከጅምላ እስራችን በስተጀርባ ያለው የሴራ ፖለቲካ….!!!

ሰለሞን አለምኔ፣ የህሊና እስረኛ፣
ከአባ ሳሙኤል እስር ቤት!

መግቢያ
44ኛውን የካራማራ የድል በዓል በፓርቲያችን ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ መሪነት ስናከብር በግፍ የታፍሰን ወጣቶች፣ ከካቲት 26 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ21 ቀናት በተረኛው ስርዓት  መታሰራችን ይታወቃል፡፡ በፌድራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሥር በሚገኘውና ልዩ ስሙ “አባ ሳሙኤል” ተብሎ በሚጠራው እስር ቤት እንገኛለን፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዓለማው ታፍሠን ከመታሠራችን ጀርባ ያለውን የሴራ ፖለቲካ ለመዳሰስ ነው፡፡
በግፍ ከታሠርነው የባልደራስ አባላቶች መካከል 4ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ 31 ወንዶች ነን፡፡ ከእኛ በተጨማሪ፣ በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ኦህዴድ/ብልፅግና በተለያዩ የአዲስ አበባ እስር ቤቶች ውስጥ አጉሯቸው ይገኛል፡፡ እኔም ከሌሎች የትግል ጓደኞቼ ጋር በኦህዴድ ብልፅግና እስር ቤቶች (ልደታ ፖሊስ መምሪያ፣5ተኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ ማዕከላዊና አባ ሳሙኤል) በታሠርኩበት ጊዜ ያስተዋልኩት ነገር፣ የእስሩ ዓላማ የታቀደና የተጠና መሆኑን ነው፡፡ በአብነት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮቹን ላንሳ፡-
የኃይማኖት ተፅእኖ ፦
ተረኞቹ የተለያዩ እስር ቤቶች ያሰሯቸውን ንፁሃን ወጣቶች የአንገታቸውን ማህተብ አስጥለዋቸዋል፡፡ እኔም የዚህ ሰለባ ለመሆን ተቃርቤ ነበር፡፡ ከአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ማዕከላዊ የተዘዋወርን ቀን፣ የፖሊሶች አዛዥ /ስሙን ያልጠቀስኩት በምክንያት ነው/ “የአንገት ማህተብህን ፍታ” ብሎኝ ዱላ ቀረሽ ክርክር እና ጭቅጭቅ ካደረግን በኋላ፣ በገላጋይ ማህተቤን ሳልፈታ ቀርቻለሁ፡፡ ነገር ግን በስድብ፣ በማመናጨቅ፣ በድብደባ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ማህተባቸውን በጥሰዋል፡፡
ይህንን ፅሁፍ በማዘጋጅበት በአሁኗ ሰዓት፣ ከምሽቱ 4፡00 ወዳጄ ነብየልዑል ይልማ በቤተሰቦቹ አማካኝነት ማህተቦችን አስመጥቶ፣ ከጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ጋር በመሆን ማህተባቸውን አስረዋል፡፡ እግዚአብሔር ያክብራችሁ፡-
ማንነትን መሰረት ያደረገው እስር ፦
እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት፣ 85% ታሳሪ የአዲስ አበባ ተወላጅ ነው፡፡ አዲስ አበቤ ከመቼውም በላይ ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ የአሁኑን እስር እንኳን ብንመለከት፣ መታሰራቸው ሳያንስ የታሰሩበት ቦታ ርቀት፣ ሁኔታና ሌሎች ነገሮች፣ ይህ ህዝብ በከታማው የመታሰር መብት እንኳን የሌለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በቤተሰቡ የመጠየቅ፣ በንፁህ እስር ቤት  የመታሰር፣ በቂ ንፁህ ውሀ የማግኘት፣ በቂ ምግብ የማግኘት መብት እንደሌለው ማሳያ ነው፡፡
ብቸኛው ተቃዋሚ ባልደራስ ፦
ገዢው ስርዓት በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ሙሉ እምነት የሚጣልበት ሰርዓት አይደለም፡፡ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው፣ ባልደራስ መርሆችና ዓላማዎቹ በግልፅ ይታወቃሉ፡፡ መታወቅ ብቻ አይደለም ላለፉት 2 ዓመታት በተግባር አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የህዝብን ጥያቄ ይዞ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለው ብቸኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ባልደራስ ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ መታገሉን ትተውታል፡፡ ይህ ለኦህዴድ ራስ ምታት ሆኖበታል፡፡
አጀንዳ መስጠት ፦
ኦህዴድ ብልፅግና የኢትዮጵያን ታሪክ አፍርሶ የሚፈልጋትንና ኢትዮጵያ (ኦሮሙማ – ኢትዮጵያ) ለመስራት ላለፉት 4 ዓመታት ላይ ታች እያሉ ይገኛል፡፡ ዛሬም እየሠራ ነው፡፡ ይህንን ተረኛ ስርዓት በልኩ ገልፆ ሴራውን ለህዝብ እያጋለጠ ያለው ብቸኛው ፓርቲ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህም፣ የባልደራስ መሪዎችና አባላቶችን አስሮ አጀንዳ በመስጠት፣ ትኩረታችንን በአባላት እስር ላይ እንድናደርግ ስለፈለገ ነው፡፡
የሀገር ሉዓላዊነት ፦
 እንደሚታወቀው፣ ህወሓትም ሆነ ኦህዴድ ብልፅግና ለኢትዮጵያ ፀር ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ሁለቱን ዘርኛ ሰብሰቦች የምንታገልበት ጊዜ፣ ቦታ፣ የመታገያ መንገዶች ይለያያሉ፡፡  በህወሓት እና ኦህዴድ መካከል ድርድር እየተካሄደና መስማማት ላይ መደረሱን ከዚህም ከዚያም የሚመጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሁለቱ ሲስማሙ ደግሞ፣ በሉዓላዊነት ላይ ቁርጠኛ አቋም ያለውን ባልደራስንና መሰል ድርጅቶችን በጠላትነት ፈርጀው በአንድነት መዝመታቸው አይቀርም፡፡ የእኛ እስር የዚያ ምልክት ነው፡፡ የነገ ማሳያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ ህወሓትንም ሆነ ኦህዴድ ስል፣ ከትግራይ እና ከኦሮሞ ህዝብ የመጡ ቡድኖች እንጂ፣ ሙሉ የትግራይ እና የኦሮሞ ህዝብ አይወክሉም፡፡
የከሸፈ ፖለቲካ ፦
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በዲሞክራሲ፣ በሀገር ሉዓላዊነት አመርቂ ሥራ መሥራት አልቻሉም፡፡ የህዝብ ጥያቄዎችን አልመለሱም፡፡ በደህንነት፣ በውጭ ዲፕሎማሲ፣በኃይማኖት እና በሌሎች ስኬታማ አልሆኑም፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ደስተኛ አይደለም፡፡ የህዝብን  ጥያቄ እና ችግር ይዞ እየተሟገተ ያለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞከራሲ ፓርቲ ብቻ በመሆኑ ለእስር ተዳርገናል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡንና ትግሉን ከድተዋል፡፡ የተፈለገው እኛም ህዝቡንና ትግሉን እንድንከዳ ነው፡፡
መውጫ ፦
እርግጥ ነው ይህ እስር እኔን ጨምሮ በርካቶቻችንን ከሥራ ገበታችን አባሮናል፣ ችግሮች ገጥመውናል፣ ቤተሰቦችን ተሰቃይተውብናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ከኢትዮጵያ በታች ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ሀገራችን ሁሉም ነገር ቢከፈል ያንሳል እንጂ አይበዛም፡፡ ትግላችንን የሚያስናክል ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ እስረኞች ነን፡፡ ፖለቲካው አስሮናል፣ ፖለቲካው ይፈታናል፡፡ ምንም ቢሆን አንሰበርም! አንሸነፍም!
ሰለሞን አላምኔ፣ ከአባ ሳሙኤል
ድል ኢትዮጵያ!!
ድል ለዲሞክራሲ!
Filed in: Amharic