>

በወያኔ ጊዜ ተጀምሮ የነበረውን የአዲስ አበባን ድንበር ማካለል ጉዳይ ጨርሰነዋል! (ሽመልስ አብዲሳ)

አዲስ አበባን ከኦሮሚያ አይደለም የምናካልላት…!!!

ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ
ዮሀንስ መኮንን
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከኦቢኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ በኦሮምኛ የሰጡትን ማብራሪያ ብዙዎች እየተቀባበሉት ነው። እኔም አድምጬዋለሁ።
አዲስ አበባንም ሆነ የተቀሩትን የሀገሪቱን ፖለቲካ የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደ ክልሉ መንግሥት ባለሥልጣን በኦሮምኛ ማብራሪያ መሰጠታቸው ተገቢ እና መብትም ጭምር ነው። ነገር ግን ጉዳዩ ቋንቋውን የማይሰሙ ሌሎች ዜጎችን በቀጥታ የሚመለከት ሲሆን በአማርኛም (በሌሎችም ተጨማሪ ቋንቋዎች) ጭምር ቢነገሩ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም እድል ይሰጠናል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በንግግራቸው ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ይገኙበታል።
– በወያኔ ጊዜ ተጀምሮ የነበረውን የአዲስ አበባን ድንበር ማካለል ጉዳይ ጨርሰነዋል፤
– “የድንበር ማካለሉ አልቋል ቻዎ ቻዎ” እንድንባባል የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። እንዲህ ዓየነት ጨዋታ ውስጥ አንገባም። እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ስህተት ውስጥም አንገባም፤
– አዲስ አበባን ከኦሮሚያ አይደለም የምናካልላት። ልክ አዳማን ወይንም ቦሰት ወረዳን እንደምናካልለው ነው የምናካልላት።
– አዲስ አበባ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ ሠፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
– የዛሬ ሦስት ዓመት በዋቆ ጉቱ እና በታደሠ ብሩ ስም ትምህርት ቤቶች ከፍተን የሚማርልን ተማሪ አጣን። ስለዚህ ተማሪ ከቡራዩ እየጫንን እናመጣ ነበር።
– አምና ጠቅላይ ሚንስትሩ የተከበሩ ዶ/ር ዐብይ በሰጡት ውሳኔ መሠረት በሁሉም ትምህርት ቤቶች አስጀመርን። ከ56,000 በላይ ተማሪ ነው የተመዘገበው። ከየት መጣ ?
– ከ5,700 በላይ መምህራን አዲስ አበባ ውስጥ አስገብተናል።
– ብዙ ነገር እየሠራን ነው። በሀብት ይዞታ ላይ፣ በውኃ፣ በመንገድ ብዙ እየሠራን ነው።
– አዲስ አበባ ውስጥ ለኦሮሚያ ገበሬዎች አሥር የገበያ ማዕከላትን እየገነባን ነው። ለአርሶ አደራችን!
Filed in: Amharic