>

የእስካሁኑ ጥፋት ይብቃ፤ ከአሁን በኋላ ችግሮቻችንን በምክክር እንፍታ...!!!" (ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ)

የእስካሁኑ ጥፋት ይብቃ፤ ከአሁን በኋላ ችግሮቻችንን በምክክር እንፍታ…!!!” 
   
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ

እስካሁን የጠፋው ጥፋት ይብቃ ከአሁን በኋላ ችግሮቻችንን በምክክርና በውይይት እንፍታ ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ገለፁ። ተቀዳሚ ሙፍቲው አገርን ለማስቀጠል የአገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ እስካሁን የጠፋው ጥፋት ይበቃል በማለት ፊትን ወደ ሰላም ማዞር ይገባል።
አገርን ለማስቀጠል የአገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ምክክሩ እኩልነት በሰፈነበት፤ በእውነትና በአንድነት መንገድ የሚከወን ከሆነ ለአገራችን አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
መመካከርና መወያየት የቆየ የኢትዮጵያውያን ትወፊት እንደሆነ ያወሱት ሃጂ ዑመር፤ በመመካከርና በመወያየት ችግራችንን ልንፈታ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲው አገራዊ ምክክሩ ወደታች ወርዶ ተፈፃሚ እንዲሆን እንዲሁም አገር ወደ ሰላማዊ ሁኔታዋ እንድትመለስ ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
ሕዝቡ ጥፋተኛን ለይቶ በማውጣትና የጥፋት መንገዶችን በመዝጋት የአገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ኮሚሽኑም ከኢትዮጵያውያን ጋር በመማከር በጋራ ችግሮች የሚስተካከሉበትንና ወደ ሰላም የሚገቡበትን ዕድል መፍጠር እንደሚገባው ጠቁመዋል።
አገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ጠበቅ ያለ መመሪያና ሕግ ሊኖር እንደሚገባ የጠቆሙት ሃጂ ዑመር፤ አገራዊ ምክክሩ በአገሪቱ የጠፋውን ሰላም ለመመለስና በዘላቂነት አብሮ ለመኖር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲው ገለፃ፤ ከዚህ ቀደም በጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች የጠፋው ጥፋት ጠፍቷል፣ በደረሰው ውድመት የወደመው ወድሟል፣ የተፈናቀለው ተፈናቅሏል፣ አሁን ግን የጠፋው ጥፋት ይበቃል በማለት እርስ በእርስ መቋሰልን ትቶ ፊትን ወደ ሰላም ማዞር ይገባል።
እንደ ሃይማኖት አባትነቴ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም መጋደልና መጫረስ እንዲበቃ እማጸናለሁ ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲው፤ አገራዊ ችግሮችን በንግግር በውይይት መፍታት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ንግግር፤ የሰው ልጅ ሰላም ምንጩ ፈጣሪውን መፍራት መቻሉ ነው፤ ፈጣሪውን መፍራት የቻለ ሰው ደግሞ የራሱን ሰላምና መብት አክብሮ የሌሎችን ሰዎችንም መብትና ሰላም ያስከብራል።
Filed in: Amharic