>
5:13 pm - Sunday April 19, 3074

" እኛ አዲስ አበቤዎች እስሩ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ተረድተናል...!!! " (ናትናኤል ያለምዘውድ  የፖለቲካ  እስረኛ - ከአባሳሙኤል እስር ቤት)

” እኛ አዲስ አበቤዎች እስሩ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ተረድተናል…!!! “
ናትናኤል ያለምዘውድ 
የፖለቲካ  እስረኛ – ከአባሳሙኤል እስር ቤት

ከወር በፊት የአድዋን በአል በደማቅ ሁኔታ በማክበራችን በጅምላ ከታፈስነው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት በተጨማሪ፣ ብዛት ያላቸው አዲስ አበቤዎች እንገኝበታለን። ካሳለፍነው ወር ጀምሮ እየተወሰደ ካለው የጅምላ እስር ጀርባ በእነ አዳነች አበቤ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር የተደበቀ ሴራ እንዳለ ያስታውቃል።
ይህ ድርጊት ከፖለቲካ ሴራ በተጨማሪ፣ የመንግስት የፀጥታ መዋቅር የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ባለስልጣናትን በመጠቀም የአዲስ አበባን ልጆች ቂም መወጣጫ መሆኑን ያሳያል።
በዚህ እስር  ከታሰርን የአዲስ አበቤዎች መካከል አብዛኛዎቻችን አራት የተለያዩ የክ/ከተማ ፍርድ ቤቶች  የቀረብን ሲሆን፣ በዋስ አሰናብተውን ነበር። ሆኖም ክሱ በዛው ቀጥሎ አሁን የምንቀርብበት የአራዳ ምድብ ችሎት ፍርድ ቤት ለ 5ኛ ጊዜ የቀረብን ሲሆን፣ የፍትህ ስርአቱ በመንግስት ስር ላሉ ግለሰቦች እጅ መውደቁን መመልከት ችለናል።
የአዲስ አበባ ህዝብ በጉልበተኞች ታፍኖ ተይዞ ነፃነቱን ተነፍጎ ህግና ዳኝነት በትዕዛዝ የሚፈፀምበት በመሆኑ፣ ህግ አስከባሪዎች የኦሆዴድ/ብልፅግና ሎሌዎች መሆናቸውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ላይ ሁሉም ነገር በጉልበተኛው ኦሆዴድ/ብልፅግና ባለስልጣናት ቁጥጥር ስር እየዋለ መምጣቱ በሚደረገው የተረኝነት አካሄድ ማረጋገጥ ይቻላል።
ለታሰርነው አዲስ አበቤዎች፣ እስሩ የፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነና አንዳንድ የኦሆዴድ ባለስልጣናት የአድዋ በአል በድምቀት በመከበሩ ደስተኛ ባለመሆናቸው ያስተላለፉት የፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነ ግልፅ ነው።
ሌላው፣ በእስራችን ላይ ካጋጠሙን ፈታኝ ችግሮች፣ አብዛኛውን የግፍ እስረኞች ከተለያዩ አካባቢዎች እንደመያዛቸው መጠን፣ ወደተያዙባቸው ወይም የሀሰት ትርክት የሆነ ክስ ወደተመሠረተባቸው ፖሊስ መምሪያዎች ነበር የሚሄዱት። ከስልሳ በላይ የሚሆኑ የግፍ እስረኞች በግፍ መታሰራቸው ሳያንስ፣ አንገታቸው ላይ ያለውን ማህተብ እንዲበጥሱ ተደርጓል። በተለይም ይህ ድርጊት የተፈፀመባቸው ፖሊስ መምሪያዎች ወረዳ 9፣ ወረዳ 2፣ ልደታ ፖሊስ መምሪያ እና በተለያዩ ፖሊስ መምሪያ ይህ ኦርቶዶክስ ጠል ድርጊት ተፈፅሟል።
ይህን ኦርቶዶክስ ጠል ድርጊት መፈፀሙን ሊጎበኙን ለመጡት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ወኪሎች ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች ጋር በማገናኘት እንዲያጣሩ አቤቱታ አቅርበናል። በተጨማሪም እንደዚህ አይነት አስነዋሪ ድርጊት መፈፀሙን ለፍርድ ቤት ተናግረናል። ሆኖም ምላሽ አልተሰጠበትም።
ይህ ኦርቶዶክስ ጠል ድርጊት ሊቆም ይገባል የሚል ፅኑ አቋም ልንይዝ እንደሚገባ የሚደረገው ድርጊት ማሳያ ነው።
ፍርድና አቤቱታ
የምንቀርብባቸው ፍርድ ቤቶች በተፅእኖ ውስጥ እንደወደቁ ብዙ ማሳያዎች እየተመለከትን ነው። ብዙ አቤቱታዎችን እንድናቀርብ አይፈለገም። በተለይ ፍርድ ቤቱ መስማት ያልፈለገው እና የናቀው አቤቱታ ብዙ ቢሆንም፣ ለማሳያ ያክል ሁለቱን ብቻ እጠቅሳለው። ይህን አቤቱታ ሳቀርብ ተከሳሾቹም ሊቆጡኝ ሞክረዋል። ግን ሁኔታዎቹንና ለምን እንደተያዙ ስለማውቀው በንግግር መፍታት ችለናል።
ከአቤቱታዎቹም ፦
በተለያየ የፍትህ ተቋማት ስገባ፣ “ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው” የሚል መሪ ቃል እመለከታለሁ፤ ይህ ቃል ግን ለአዲስ አበቤ ሲሆን አይፈፀምም። ምክንያቱን ሳስረዳም፣ በአባ ሳሙኤል እስር ቤት አብረውን ከታሰሩት መካከል የህውሃትና የኦነግ ሸኔ አባላት ይገኙበታል። አብዛኛዎቹ በብር ዋስና በመታወቂያ ዋስ ይለቀቃሉ።
እኔን የገረመኝ መለቀቃቸው ሳይሆን ፈፅመዋል ተብለው የታሰሩበት ድርጊት ነው። ከክሱም ውስጥ ባህር ዳርን በሮኬት ያስመታ፣ ሳምሪ የሚባሉ ወጣቶችን በማደራጀት በፋይናንስ ይደግፋል የተባለ ግለሰብ፣ በተጨማሪም ለኦነግ ሸኔ የሚሰራን “ለኦሮሚያ የሚጠቅም ወታደር ነው” ተብሎ በመታወቂያ ዋስና በገንዘብ ሲለቀቅ፣ እኛ የአባቶቻችንን ታሪክ በአል ስላከበርን ታስረን እንዴት ዋስትና እንከለከላለን? የሚል አቤቱታ ሳቀርብ፣ በየመሃሉ ለአራት ጊዜ የሚሆን ማስጠንቀቂያ እየተሰጠኝ አቤቱታዬን ለመጨረስ አስተጓጉለውኛል።
ሁለተኛውና ፍርድቤቱን ያስቆጣው አቤቱታ ፦
 “መንግስት ምንም ዓይነት ወንጀል እና ረብሻ አለመፈፀሙን እያወቀ ነው፤ በዓሉ በድምቀት በመከበሩ የተናደዱ ግለሰቦች ናቸው እንድንታሰር ያደረጉን። ስለዚህ ይቅርታ ይጠይቁን…” በማለት ሳልጨርስ፣ ፍርድ ቤቱ “በቃህ” በማለት ቁጣና ምክር ሲለግሰኝ፣ እኔም ጠበቆቼን ቤተማርያምንና ሄኖክን ለማግኘት ብዬ ቀጠሮዬን ይዤ ወደ አባ ሳሙኤል ማረፊያ ተመልሻለሁ።
አዲስ አበባ ፖሊስ ፦
አዲስ አበባ ፖሊስ እራሱን የቻለ ትልቅ ተቋምና መንግስት መሆኑን አሳይቶናል። የአዲስ አበባ ፖሊስ  ትእዛዝና ፍርድ ቤትን እንደማይቀበል በአባ ሳሙኤል የመጣ የእስረኛ አስተዳደር ረ/ኢኒስፔክተር ጎሳዬ በግልፅ ነግሮናል ። ይህ ኮሚሽን ጉልበተኛነቱን እና ለህዝብ መቆሙን ትቶ የገዢው መንግስትን ጉዳይ አስፈፃሚ እንደሆነ መመልከት ችለናል።
ፍትህ ለአዲስ አበባ ፖሊስ‼
ፍትህ ለፍትህ ተቋማት‼
ፍትህ ለአዲስ አበቤዎች‼
Filed in: Amharic