አሳፍ ሀይሉ
የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊውን የሀገሮች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርት አውጥቷል። በኢትዮጵያችን ላይ የቀረበው ሪፖርት የሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት አስደንጋጭ በሚባል ደረጃ እጅግ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑንና፣ ያንንም የሚከላከልና የፖለቲካ መሪዎቹን ያልተገራ ሥልጣን የሚገድብ ህግም ሆነ ሥርዓት እንደሌለ ነው።
ከሪፖርቱ በጣም የገረሙኝ ሶስት ነገሮች አሉ። አንደኛው በሚሊየኖችና በመቶ ሺህዎች ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ስለተፈናቀለውና ስለተጨፈጨፈው ብሔረ አማራ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካው ሪፖርት እንዳልተፈጠረ ዘሎታል። የቅማንቶችን ሞት ግን በበቂ ዝርዝር ዘግቦታል። የአሜሪካኖቹ የተንሸዋረረ ፀረ-አማራ አስተሳሰብ ከ40 እና 50 ዓመታት በኋላ ዛሬም ላይ ያለመለዘቡን ነገር አስደንጋጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሁለተኛው የገረመኝ የአሜሪካኖቹ ሪፖርት በኢትዮጵያ ያለው ሕገመንግሥት ክልሎች ዘርን (ብሔርን) መሠረት አድርገው ክልልሎች እንዲዋቀሩ እንዳደረገ ይገልፅና የሀገሪቱ ፖለቲካ ኃይሎችም – ከሁለት ፓርቲዎች በስተቀር – በዘር-ተኮር የብሔር ፖለቲካ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይገልጻል።
በሳቅ የገደለኝ ነገር የአሜሪካ መንግሥት ከብሔር ውጪ በሆነ መንገድ ተደራጀ ብሎ የገለፀው አንደኛው ፓርቲ በአብይ አህመድ የሚመራውን ብልፅግና ፓርቲን መሆኑ ነው። ዋናውን የብሔር ፖለቲካ ድፍድፍ አውጪ ከብሔር ፖለቲካ ውጭ የተደራጀና የሚንቀሳቀስ ብሎት እርፍ ብሏል። ይህን ሪፖርት የፃፈው ሰው ወይ የለየለት ደደብ፣ ወይም ስለማያውቀው ነገር የሚዘባርቅ ፍፁም ጨዋ፣ አሊያም ዓይኑን በጨው ያጠበ ቀላማጅ መሆን አለበት መቼም!
ሌላኛው ከብሔር-ነፃ የተባለው በሪፖርቱ በተቃዋሚነት የተገለፀው ኢዜማ ነው። ይህም በሁለት መልኩ ስህተት ይመስለኛል።
አንደኛ ነገር ሪፖርቱ በሸፈነው ያለፈው የፈረንጆች ዓመት ውስጥ ሌሎችም ከብሔር ውጭ የሆነ ፖለቲካ የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።
ሁለተኛ ነገር ከገዢው ፓርቲ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ፣ ሥልጣን ተቀራምቶ፣ የብሔር ፖለቲካውን ከሚያራምድ መንግሥት ጋር የሚሠራ ፓርቲ እንዴት “ተቃዋሚ” ተብሎ ይጠራል? በምንስ መለኪያ ነው የብሔር ፖለቲካውን ተቀብሎ እየሠራ ያለ ኃይል ከብሔር ፖለቲካ ውጭ የሚሠራ ለመሰኘት የሚበቃው? በአባላት ምልመላ መሆን አለበት። ይሁን ብለን እንቀበለውና ወደመጨረሻው ነጥቤ ልሻገር!
ሌላው ሶስተኛውና የመጨረሻው አስቂኝ የሪፖርቱ ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩን (አብይ አህመድን) በሪፖርቱ በመከላከያው ሠራዊት ተፈፀሙ ለተባሉ ብዛት ያላቸው የሰብዓዊ ጥሰቶችና ወንጀሎች የተነሳ ለወደፊት ከሚመጣ ተጠያቂነት ካሁኑ ነፃ ለማውጣትና ለመከላከል የሄደበት ርቀት ነው። ብዙውን white washing ትቼ አንዱን ብቻ ጠቅሼ እሰናበታለሁ።
ይሄው የአሜሪካ ሪፖርት የሀገሪቱን ፌዴራል ፖሊስ በበላይነት የሚያዘው ጠሚው አብይ አህመድ ነው በማለት ይገልፅና፣ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ግን ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ነው በማለት የአብይ አህመድ እጅ ከደሙ ንፁህ መሆኑን እግረመንገዳዊ ቡራኬውን ይቸረዋል።
አሜሪካኖች አሳቁኝ በጣም! አሜሪካኖቹ በሪፖርታቸው በገለፁት ህገመንግሥት ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ ማነው ይላል? ጠሚው እውን የፖሊስ አዛዥ ብቻ ነው? ኧረ ለብሶት ለሚዞረው የሚሊቴሪ ፋቲግ ራሱ እዘኑለት?
በተረፈ በአጠቃላይ ሲታይ ሪፖርቱ ሀገራችን የደረሰችበትን የሰብዓዊ አያያዝ አሳሳቢ ግሽበት፣ እና በዜጎቻችን ላይ ከህግ ውጭ እየተፈፀመ ያለውን አስከፊ የመብት ጥሰት ለዓለም ሕዝብ ያሳየ ሪፖርት ነው።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን በመሠለ የወረደ ደረጃ ሀገሬ በአስቀያሚና አሳፋሪ የሰብዓዊ ሁኔታና የሥርዓት ብልሽት ላይ መገኘቷ አንገት የሚያስደፋ፣ ልብን የሚሰብር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።